በሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ የኮሬ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት 13 መምህራን ፋኖ ታጣቂዎች ናቸው ባሏቸው ታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ገለጹ።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን በይፋ እንዳንጠቅስ የጠየቁን የታጋች ቤተሰቦች ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በአካባቢው ትምህርት ከተከፈተ አንድ ወር እንዳለፈው ገልጸው ባለፈው ዕረቡ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ትምህርት ቤቱ የሄዱ መምሕራንን ታጣቂዎቹ አግተው ወደ በርሃ ይዘዋቸው እንደሄዱ መስማታቸውን ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ መምህራንን ሥራ እንዳይጀምሩ ማስጠንቀቃቸውን እና ሥራ ለመጀመር ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ መምሕራንን በማገት እስከ 50 ሺሕ ብር አስከፍለው እንደሚለቁ ተናግረዋል።
በሰሜን ጎጃም ጎንጂ ቆለላ ወረዳ 13 መምህራን በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን ቤተሰቦች ተናገሩ
በሰሜን ጎጃም ጎንጂ ቆለላ ወረዳ 13 መምህራን በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን ቤተሰቦች ተናገሩ
በአሁኑ ሰዓት ወረዳው በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት “መምህራኑን ሥራ ጀምሩ ጥበቃ ይደረግላችኋል” ብለዋቸው እንደነበርም አክለዋል።
የኮሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተረፈ አበጀ በስልክ አግኝተናቸው መምህራኑ መታገታቸውን አምነው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
ለጎንጂ ቆለላ ወረዳ አስተዳዳሪ ለአቶ ጌታቸው ደገፋው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ ከተባሉ የፋኖ ታጣቂዎች ምላሽ ለማግኘትም ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
VOA Amharic