የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አርብ መጋቢት 08/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ምርጫ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መምረጡ ተነገረ።
አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ የሚቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በህወሓት መመረጣቸውን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ከወራት በፊት በፕሪቶሪያ በተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም በተደረሰው ስምምነት መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ተወስኗል።
ህወሃት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ካዋቀረ በኋላ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በፌዴራል መንግሥት መጽደቅ አለበት።
በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖርን ውክልናን በተመለከተ 30 በመቶ ለህወሓት፣ 25 በመቶ ለትግራይ ሠራዊት፣ 15 በመቶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ቀሪው ለምሁራንና ለሲቪክ ማህበራት እንደሚሰጥም ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።
ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሰላም ስምምነቱ ተደራዳሪ ከነበሩ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው የሚታወስ ነው።
የፌደራሉ መንግሥት ዋነኛ ተደራዳሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የህወሓት ተደራዳሪ እና ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በተነጋገሩበትም ወቅት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረት የስምምነቱ ቁልፍ ተግባር አድርገው ማየታቸው ተጠቅሷል።
በዚህ ውይይትም ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነቱ እንዴት እየሄደ እንደሆነ የተገመገመ ሲሆን፣ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ መስማማታቸው ተገልጿል።
ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጋር ስለነበራቸውም ቆይታ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ “ለሰላም ያለንን የማያወላውል ቁርጠኝነት አረጋግጠናል። ሰላሙን ለማደፍረስ የተነሱ ኃይሎችን ጨምሮ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ያሉትን እንቅፋቶችን ለመፍታት ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረትን ጨምሮ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን” በማለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ጋር ተያይዞ ምሥረታውን ለማካሄድ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ከትግራይ ተቃዋሚዎች በኩል ተቃውሞ እንደተነሳበት መገለጹ ይታወሳል።
ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲዎች በኮሚቴው ላይ የገለልተኝነት እና የአሳታፊነት ጥያቄ በማንሳት ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።
bbc