የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ባህርዳር አማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የ10 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጣቸዉ፡፡ መርማሪ ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ጀነራል ተፈራ ማሞ ላይ የቀሩኝ የማሰባስባቸው ማስረጃዎች አሉኝ ሲል የ14 ቀናት ቀን ጠይቆ ነበር። የጀነራሉ ጠበቃ በበኩላቸው ቀሩ የተባሉ ማስረጃዎች ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጣ ሊያጠፋቸውና ሊያገኛቸው የሚችሉ ባለመሆናቸው ደንበኛቸው ከፖሊስ ጣቢያ በዋስ ተለቅቀው እንዲከራከሩ ጠይቀዋል፡፡ ጠበቃ ሸጋው አለበልን ከችሎት በኋላ የዶይቼ ቬሌ ዓለምነዉ መኮንን አነጋግሯቸው ነበር፡፡
የሁለቱንም አካላት ክርክር ያዳመጠው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ ዛሬም ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት በመጡበት ወቅት ቁጥሩ በዛ ያለ የፀጥታ ኃይል ከፍተኛ ጥበቃ ሲደርግ ነበር፡፡ ብርጋዴር ተፈራ ማሞ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረር መልዕክቶችን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲያስተላልፉ ነበር በሚል ተጠርጥረው በመንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉት ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ነበር፡፡
ዘገባ ፤ዓለምነዉ መኮንን DW ከባህር ዳር/ DW