የራያ የወሰንና የማንነት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚመለስ የፌዴሬሽን ም/ቤት ገለጸ

March 29, 2022
የራያ የወሰንና የማንነት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚመለስ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የራያ ሕዝብ ተወካዮች ላቀረቡት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ የራያ ሕዝብ ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ታይቶ ውሳኔ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የራያ ሕዝብ ተወካዮች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የራያ ሕዝብ የማንነት እና የወሰን ጥያቄን በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀረቡ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ ምላሽ ሳያገኝ እንደቆየ አውስተዋል፡፡
አያይዘውም÷ የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ሞትን ጨምሮ ሌሎች በደሎች በራያ ሕዝብ ላይ ሲፈፀም የቆየ እንደነበረና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የራያ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ እና ንብረታቸውም ሲወድም እንደነበረ ተወካዮቹ በአካል ቀርበው አስረድተዋል፡፡ ጥያቄያችን ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ተወካዮቹ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ጥያቄውን ላቀረበው ኮሚቴ በሰጡት ምላሽ÷ የራያ ሕዝብ ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ታይቶ ውሳኔ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡
እንደ ከዚህ በፊቱ የሕዝብን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚደረግ አላስፈላጊ ጫና ከሕገ መንግስቱ የሚቃረን ስለሆነ ተቀባይነት እንደሌለው የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፥ የሕዝብ ጥያቄ ሕግን መሠረት በማድረግ ምላሽ በመስጠት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል በማለት ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በድጋሜ መሰማት ያለበት: የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባዔ

Next Story

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚሰጥ የአበል ክፍያ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ቅሬታ ገለፁ

Go toTop