የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ ሠራዊቱ ኢትዮጵያን የማዳን ተልዕኮውን በጀግንነትና በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ትናንት በደሴ ግንባር አሸባሪው ቡድን ቀድሞ ባስገባቸው ሰርጎ ገቦችና ሲቪል ለብሰው ከተማዋ ውስጥ በነበሩ ባንዳዎች አማካኝነት ሠራዊቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩን ገልፀዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የተከፈተበትን ጥቃት በከፍተኛ ተጋድሎ መክቶ የማጥቃት ዘመቻ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ትናንት በደሴ ግንባር ታላቅ ተጋድሎ መፈጸሙን እና ሕዝቡም ደጀንነቱን በተግባር ማስመስከሩን ነው የገለጹት።
የመከላከያ ሠራዊቱ በጭፍራ፣ በጋሸና እና በሌሎች ግንባሮች እያደረገ በሚገኘው ተጋድሎ ይዞታውን በማስፋት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
መንግሥት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አስመልክቶ ፈፅሞ የተዛባ እና ህዝብን የሚያደናግሩ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን ከእንግዲህ እንደማይታገስም ገልጸዋል፡፡
መከላከያ የሚወስዳቸውን ስልታዊ እርምጃዎች በተሳሳተ መንገድ በመገንዘብም ሆነ ህዝብን ለማደናገጥ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ የህዝብ አንቂዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
ENA/FANA