የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የክስ መዝገብ ፍርድ ቤት የቀረቡ 21 ተከሳሾች የጠየቁትን የዋስትና መብት ውድቅ አደረገ፡፡
ችሎቱ በእነ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የክስ መዝገብ ለዛሬ ይዞት በነበረው ቀጠሮ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡
በደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የክስ መዝገብ 58 ግለሰቦች እና አራት ድርጅቶች በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡ከእነዚህ መካከል ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረው ችሎት ከተከሳሾቹ 21ዱ በአካል ቀርበው ክስ የተነበበላቸው ሲሆን የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸውም አመልክተዋል፡፡
በተከሾቹ ላይ የተመሰረተባቸው ክስ ዋስትና የሚያስከለክል በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ዝርዝር ሀሳቦችን በማንሳት መከራከሩም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ችሎቱ በሁለቱ ወገኖች ክርክር ላይ ለዛሬ ትዕዛዝ ለመስጠት በያዘው ቀጠሮ መሰረት ተከሳሾች ችሎት መምጣት ሳይጠበቅባቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነው ትዕዛዙን እንዲጠብቁ በማለት ነበር ችሎቱ ለዛሬ የቀጠረው፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች የዋስትና ጥያቄ ክርክር መርምሮ ዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በማረሚያ ቤት በኩል ለተከሳሾች እንዲደርሳቸው ሲል ችሎቱ አዟል፡፡
በችሎቱ በአካል ያልተገኙት እነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ጌታቸው ረዳ፣ ሊያ ካሳ እና ሌሎች ተከሳሾች እንዲሁም የአራቱ ድርጅቶች ተወካዮች የፌዴራል ፖሊስ ባሉበት ይዞ እንዲያቀርብ እና ውጤቱንም ለመጠባበቅ ለጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል፡፡
በጥላሁን ካሣ
EBC