ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ግንባር ያመራው የፋኖ ሠራዊት በንፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪዎች አቀባበል እና ሽኝት ተደርጎለታል፡፡ ሠራዊቱም በታላቅ ወኔ ወደ ግንባር አምርቷል፡፡
በሽኝት መርኃግብሩ ላይ ኮሎኔል አለበል አማረ ባደረጉት ንግግር “አብረን ወደ ፊት እንሄዳለን፤ አብረን የጀግንነት ሥራ እንሠራለን” ሲሉ ለፋኖ ሠራዊት ተናግረዋል፡፡
አማራን በማዳከም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ግብ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት ኮሎኔሉ ይሄንን በጀግንነት ቀልብሰን የአማራን ታሪክ እናድሳለን፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊት እናስከብራለን ብለዋል፡፡
ፋኖ ቤዛዊት አያሌው በህልውና ዘመቻው ከተቀላቀሉ ወጣቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ “ፋኖዎች ትግሉን አስበንበት እና ቆርጠን ወጥተናል፤ ጠላት የገባበት ገብተን እንደመስሰዋለን፡፡ ትግሉ ሴት ወንድ ብሎ አይለይም፤ የሁሉም ጉዳይ ነው” ብላለች፡፡
ፋኖ ደረጀ በላይ በበኩሉ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኀይልና ከሚሊሻ ጋር በቅንጅት ጠላትን ድል ለመምታት መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
ዘጋቢ:- ቢኒያም መስፍን
AMC