ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በአንድ ወርቅ፣ በአንድ ብር እና በሁለት የነሃስ ሜዳሊያዎች (በድምሩ በ4 ሜዳሊያዎች) ከዓለም 56ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 5ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች።
በሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10ሺህ ሜትር ፍፃሜ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ሲያስገኝ፤ ለሜቻ ግርማ ደግሞ በ3ሺህ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ለአገሩ ማስገኘት ችሏል።
በአሎምፒኩ የመዝግያ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ የሚያውለበልበው አትሌት ሰለሞን ባረጋ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በኦሎምፒኩ ኢትዮጵያን በ4 ስፖርቶች የወከሉት 38 ስፖርተኞች ሲሆኑ በአትሌቲክሱ ሶስት አትሌቶች አራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሮቻቸውን አጠናቀዋል።
በአትሌቲክሱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 3ኛ ከዓለም ደግሞ 14ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።
ከ205 አገራት የተውጣጡ፣ ከ11ሺህ በላይ ስፖርተኞች፣ በ33 አይነት የስፖርት ውድድሮች በተሳተፉበት በ32ኛው ኦሎምፒክ 118 አገራት ምንም ሜዳሊያ አላገኙም።
ኦሎምፒኩ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝም አሜሪካ በ113 ሜዳሊያ ከዓለም 1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ቻይና እና ጃፓን በ88 እና በ58 ሜዳሊያዎች 2ኛ እና 3ኛ ሆነው ያጠናቀቁ ሲሆን ባጠቃላይ 93 አገራት አንድ እና ከአንድ በላይ ሜዳልያ ለማግኘት ችለዋል።
በ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ መዝግያ ስነ-ስርዓት ላይም ከ50 አትሌቶች በላይ የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው ያውለበልባሉ ተብሏል።
EBC