ስለ ዓባይ ውሐ ግብጽና ኢትዮጵያ ማወቅ ያለባቸው – ፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ

February 15, 2020

ፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ

ማንም ሀገር በዓለም ላይ፥ በተለየ ከጎረቤቱ ጋር በሰላም ለመኖር ይጥራል እንጂ፥ ከጥቅሙ አንዲት ፍሬ አያካፍልም። ኢትዮጵያ የዓባይን ውሐ አጠቃቀም በተመለከተ ያላት አቋም እንደዚህ መሆን አለበት። በዓባይ ውሐ ስትጠቀም “ይኸን ባደርግ ግብጽ ትጎዳለች” የሚል አስተሳሰብ አእምሮዋ ውስጥ መግባት የለበትም። የግብጽም ሆነ የማንም ሀገር ጥቅም የኢትዮጵያን አይገዳትም። ለግብጽ ጥቅም የምትጨነቅ ግብጽ፥ ግፋ ቢል ዘመዶቿ ብቻ ናቸው።

ኢትዮጵያ ካላት ሀብቶች ዋናው ውሐ ነው። ያውም ሆኖ ሕዝቧ ብዙ ጊዜ በውሐ ጥም ያልቃል። “የዓባይን ልጅ ውሐ ጠማው” የሚባለው የጥንት አነጋገር ነው። የኢትዮጵያ ውሐ ከኢትዮጵያ እየወጣ ጎረቤትን ሲያረካ እኛ እንዳንጠቀምበት አቅሙና ዘዴው አልነበረንም። በአቅመ ቢስነታችን ጊዜ (በዘመነ ኢያእምሮ) ሌሎች ቢጠቀሙበት (ደግሞም ተጠቅነመውበታል) እኛን አያገደንም። ዳቦው ምንም የኔ ቢሆን፥ እኔ ካልበላሁት ሌላ ሰው ቢበላው ጥያቄም አላነሣም።

ኢትዮጵያ በውሐ ሀብቷ መጠቀምና አንድ ሰው በባንክ ባስቀመጠው ገንዘብ መጠቀም መቶ በመቶ ይመሳሰላሉ። ሰውየው በባንክ ካስቀመጠው ገንዘቡ ላይ የፈለገውን ያህል የሚያወጣው ከጎረቤቱ ጋር እየተማከረና እያስፈቀደ አይደለም። በግል ገንዘብ ጎረቤት አያገባውም። የዓባይ ወንዝ የያዘው ውሐ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለ ድረስ የኢትዮጵያ ሀብት ነው።  ውሐ በሚሰጠው ጥቅም ሁሉ ኢትዮጵያ ማንንም ሳታማክር ትጠቀንበታለች፤ መብቷ ነው። ማንንም ሳታማክር ትጠጣዋለች፥ ትታጠብበታለች፥ ትገድበዋለች፥ መስኖ ላይ ታውለዋለች። የግል ንብረት ለድርድ አይቀርብም። ማንም ሰው በግል ንብረቱ  ለመጠቀም የተደራዳሪ ቡድንም ሆነ አደራዳሪ አያስፈልጉም። የኢትዮጵያ አቋም ከዚህ መለየት የለበትም።

ኢትዮጵያ በዓባይ ውሐ መጠቀም ስትጀምር በሰው ሀገር ውሐ ትኖር የነበረች ግብጽ ልትሠጋ ይገባታል። ድቡሽት ላይ የተሠራች ቤት ናት። ድቡሽት ላይ የተሠራ ቤት መሬቱ ሲነቃነቅ ይፈርሳል። ማንም የመሬትን መነቃነቅ ሊያቆም እንደማይችል፥ ግብጽም ኢትዮጵያን በሀብቷ መጠቀምን ልታቆም አትችልም። ሁኔታው ይህ መሆኑን ግብጽም ኢትዮጵያም መረዳት አለባቸው። ይህ ከሆነ (አይደለም የሚል ካለ ይምጣና ይከራከረኝ) ለግብጽ የሚበጃት ምንድን ነው? ይኸን ጥያቄ ለመመለስ ባለጉዳዮቹ ይጨነቁበት። የኢትዮጵያ ግዴታ (ያውም የሞራል) አንድ ብቻ ነው። በዓባይ ውሐ የአለመጠቀሟ ጊዜ ማለፉንና የመጠቀሚያዋ ዘመን መደረሱን ለግብጽ ትንገራት። ግብጽ በበኩሏ ምድረ በዳ ሆና መጥፋት ካልፈለገች፥ ውሐ ማጠራቀም፥ ከመሬት ውሐ ማውጣት፥ የሕዝብ እድገቷን መቈጣጠር፥ ውሐ ከኢትዮጵያ መግዛት ትችላለች። ኢትዮጵያ ለግብጽ የምትሸጠው ውሐ ለጥቅሟ ከምታውለው ቀንሳ ስለሚሆን ጉዳቱ በክፍያው ይካካሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ አስተያየት – ዶ/ር ንጉሴ ነጋ

Next Story

እሳት አቃጠለኝ! – በላይነህ አባተ

Go toTop