በህዳሴ ግድብ አሞላል እና አገልግሎት ዙሪያ ባለፉት ስንምት አመታት ውይይት የተደረገበትና አወዛጋቢው የኢትዮጵያ ፡ የግብፅ እና የሱዳን ድርድር እልባት ሳያገኝ ቆይቶ በዛሬው ቀን ዋሽንግተን ውስጥ ንግግሩ እንደሚቀጥል ተነግሯል ፡፡
ብዙ ጊዜ ያወዛገበውን ያአገር ጥቅም አሰከባሪ ድርድር በአንድ ጀንበር አጠናቆ መለያየቱ ጎጂ መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ተደራዳሪዎች በይዋል ይደር ሁኔታዎችን እያጠኑ እስካሁን በጥንቃቄ መጓዛቸው እጅግ የሚያሰመሰግን ነው፡፡ በቀጣይም እጅግ የተወሳሰቡ እና አከራካሪ የሆኑ የግብፅ ድብቅ አጀንዳዎች ስለሚታዩ ተጨማሪ ጊዜ ሰቶ ውሉ ከመፈረሙ በፊት በሃገርም በውጭ ሃገርም ከሚገኙ የውሃ ሃብት ባለሙያዎችና የዓለም አቀፍ የህግ ምሁራን ጋር ሰፋ ያለ ምክክር ቢደረግበት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል
ምናልባትም የአሜሪካንን እና የዓለም ባንክን አደራዳሪዎች ላለማሳፈር ከተፈለገ እና ጉዳዩን ለማዘግየት ጥረት ከተደረገ አሁን በኢትዮጲያ ውስጥ የሚታየውን ውስብስብ የፖለቲካ ውጥረት በማንሳትና ለጊዜው ውሉ በፓርላማ ሙሉ ድምፅ ያልፀደቀ መሆኑን እንደምክንያት በማቅረብ በቅርቡ የሚደረገው አገራዊ ምርጫ እስከሚጠናቀቅ ጊዜ ይሰጠን ብሎ ማሰገንዘቡ ተመራጭ ይሆናል ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ምስቅልቅል እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ግብፅ በግርግር ፊርማው እንዲፈፀም በውጭ ኃይሎች በመረዳት በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ላይ ጫና እያደረገች መሆኑ ይሰማል ፡፡ ሰለዚህም ኢትዮጲያን ኃላፊነት ወሥዶ ከጉዳት ለማዳን የሚችለው አሁን በስልጣን ላይ ያለው የክቡር ጠቅላይ ሚንሰትር አብይ አህመድ መንግስት እና እሳቸው በተቀዳሚነት የሚመሩት ፓርላማ ነው ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር አገራችንን የሚጎዳ ውል ከሆነ አንፈርምም ማልታቸው ይታወሳል ፤ ይህ አስደሳች የሆነ ቃል ሲሰማ የተደሰተው መላው የኢትዮጲያ ተወላጅ መሆኑ ግልፅ ነው ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የድርድሩን መንፈስ ሲያስረዱ መግባቢያው “ልጠቀምን እና እንዳልጎዳን” የሚያስታርቅ መሆኑን ተናገረዋል ፡፡ ስለዚህም አሁን ግብፅ የያዘችው ሰበብ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ስለሆነ የጠቅላይ ሚንስትር አብይን ቃል ግብፅ የማታስተጋባ ከሆነ “ዜሮ ለዜሮ” መውጣቱን በተመለከተ የድርድሩ ሚዛን አዘንቢሎ አድሎአዊ እንዳይሆን ያሳስባል፡፡ ቀደም ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚንሰትሩ ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውኃ ሃብት ሚንስትሩ ክቡር ዶክተር ስለሺ በቀለ ሲያስተጋቡ የቆዩትም ይህንኑ የአገር ጥቅም አሰከባሪነት ጠንካራ አቋም ነው፡፡ በቀጣዩ እነዚህ የዲፕሎማሲ ብቃትና የቴክኒካል ችሎታ ያላቸው መሪዎች የኃገራቸውን ጥቅም ሙሉ በሙሉ እንዲያስከብሩ አደራና ተስፋ ይጣልባቸዋል ፡፡
ሦስቱ ሃገራት ለስምምነት ተቀራርበውበት ነበር የተባለዉ ነጥብ እንደሚያመለክተዉ ግድቡ ከሃምሌ እስከ ነሐሴ ቢያስፈልግም እስከ መስከረም ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ይሞላ የሚል እንደነበረ ይነገራል፡፡ ይህ በክረምት ጊዜ ይሞላ የሚለዉ ስምምነት ሁሉንም የሚያካክስ ከሆነ ጉዳት አይኖረዉም 80 በመቶ የሚሆነዉ ዝናብ ከሀምሌ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ባለዉ ጊዜ ስለሆነ ግድቡን በተወሰነ ጊዜ ለመሙላት ለኢትዮጵያ አዳጋች አይሆንባት ይሆናል፡፡
ያለፉትን 30 ዓመትት የአባይን ተረተር የዝናብ አጣጣል ታሪክ የሚያሳዩ ጥናታዊ አመለካከቶች የህዳሴ ግድብ አሞላል አመቺ ስምምነት ከተደረሰበት ግድቡን ለመሙላት ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል በዓመት የምታገኘው 1184 mm/yr ዝናብ በቂ ይሆናል ፡፡ይህም
1ኛ- አዲስ አበባ ላይ በተድገው ውይይት የኢትዮጲያን ጥቅም የሚስክብሩ ተደራዳሪዎች ግድቡን ለመሙላት የተወሰኑ የዓመታት ገደብ ያስፈልጋል የሚለውን አቋም ሳይለውጡ ከተደራደሩ ብቻ ነው፡፡
2ኛ-ግድቡን ከ7 ዓመት ባነሰ የጊዜ ገደብ ለመሙላት የደለሉን፤ የጎርፉን እንዲሁም በሙቀት እየተነነ የሚባክነውን የውሃ መጠን አቻችሎ በክረምትም ስለሚሆን የድርቅ ሰበብ ሳይነሣ ኢትዮጲያ ከ12 ቢሊዬን ኪዩቢክ ሚትር ውሃ እስከ 13 ቢሊዬን ኪውቢክ ሜትር አመታዊ የውሃ ክምችት እንደሚያስፍልጋት ጥናቶች ያመላክታሉ ስለዚህም አሁን በፊርማ ለመፅደቅ የቀረበው ውል ለኢትዮጲያ ጥቅም የሚሰጠው ይህንም ከአስከበረ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የመሙያው ጊዜ ስለሚያራዘም ጎጅ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
3ኛ-በድርድሩ መሠረት ምንአልባትም ድርቅ ከተከሰተ የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን ቢቀንስ ድርቅን ሰበብ በማድርግ ውሃ ከህዳሴ ግድብ ይለቀቅልኝ አያለች ግብፅ በየጊዜው ማስቸገሯ የማይቀር ነው፡፡ ሰለዚህም የህዳሴ ግድቡና የአስዋን ግድብ ይናበቡ ከተባለ የህዳሴ ግድብ አሞላልና አገልግሎት የጊዜ ገደብ ሰለሚረዝም ይህንን በውሉ ውስጥ ማካተቱ ኢትዮጲያን አይጠቅማትም፡፡
4ኛ- ቢያስፈልግም እስከ መስከረም የሚለው በንዑስ ሐረግ በድርድሩ ላይ የሚሰፍረው አሻሚ ቃል ተለውጦ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ መሰከረም 30 ቀን በሚል የማያሻማ ውል ካልተገለፀ ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ይሆናል፡፡
5ኛ- ግብፅ ለድርድር በመቅረቧ ብቻ በዓለም ባንክ በኩል ለጊዜው በዓሃዝ ያልተተመነ ለምግብ ዋስትና የሚውል የበጀት ማገዣ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚሰጣት ተነግሯል፡፡ ይህን በተመለከተ ኢትዮጲያ ካቀደችው የ7 አመት የሕዳሴ አሞላል አልፎ ለምሳሌም እስከ 10 አመታት ሙሉ በሙሉ አጠናቃ የኃይሉን ምርት በሺያጭ ለጎረቤት አገራት ከላቀረበችና የሐገሯን ውስጥም እጅግ አፋጣኝ የሀይል ስርጭት በጊዜው ባለ ማግኘቷ ብቻ ጥናቶች እንደ ሚያመለክቱት ከ $5.5 ቢሊዮን አስከ $7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ሊደርስባት ይችላል፡፡ ስለዚህም ለዚህ ዓይነት ኪሣራ ማካካሻ ይሆን ዘንድ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ለአዳራዳሪው ቀንደኛ ተዋናይ ለክቡር ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሕዳሴ ግድብ የአገልግሎት ጊዜ ከተራዘም የሚያደርሰውን ኪሳራ በደብዳቤ አሳስበው ለግድቡ በጅት መደጎሚያ ለግብፅ እንደሚደረገው ሁሉ ለኢትዮጵያም ቢደረግ አጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህም ጥያቄ የሚገኝ የገነዘብ እርዳታ ሊያገለግል የሚችለው እኛ ባልናችሁ ተሰማሙ ከሚለው ጫና ነፃ ከሆን ብቻ ነው ፡፡ ከዚህም በማያያዝ ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ለመፈለግ ለስነ ምህዳር እና ለአካባቢ ጥበቃ ይረዳ ዘንድ ግብፅ እና ሱዳን የተጠቃሚ ቀረጥ እንዲከፍሉ መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡
በቅርቡ የሕዳሴ ግድብን ሲጎበኙ ዶክተር አብይ እንደተናገሩት ከሕዳሴ እስከ ሆለታ ድረስ የተዘረጋዉ ትራንስሚሽን ግልጋሎት ሳይሰጥ ቆሞ በመቅረቱ ኢትዮጵያ በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንዳጣች ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አብይ አገላለፅ ፕሮጀክቱ የዛሬ ሶስት ኣመት ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ በሚገኘዉ 3 ቢሊዮን ዶላር ለግንባታ ያወጣነዉን ወጭ ግማሹን መሸፈን እንችል ነበር የሚለው ትክክለኛ ግምት ነው ፡፡
ይህ ቀደም ሲል በተጠቀሰዉ የ 7 ዓመት የጊዜ ገደብ የሚከናወን ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የህዳሴን ግድብ በጉብኝት ላይ እንዳሉ ፈገግ ባለ ገጽ እና ቁርጠኝነት በተመላበት የመሪ ቃል እንዳስረዱት ሁለቱ ተርባይን በሚመጣዉ ዓመት ሥራ እንደሚጀምሩና ጠቅላላዉ የ 13 ተርባይን አገልግሎት ደግሞ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2023 እንደሚጠናቀቅ ነዉ፡፡ ሆኖም ይህ እጅግ የተፋጠነ የጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይ እቅድ ሊሳካ የሚችለዉና በ 3 ዓመታት የሕዳሴ ሐይቅ ሞልቶ ማምረት የሚጀምረዉና ሕዳሴ በድርቅ ሰበብ ከአስዋን ግድብ ጋር እንዲናበብ ሳይደረግ እና የዉሃ ግብር ከፋይ ሳይሆን ቢያንስ ቢያንስ ከ24 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር (በሶስት ዓመታት ደለሉን ጨምሮ 72 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ) ማጠራቀም ከቻለ ብቻ ነዉ፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር ሕዳሴ ዉስጥ የተጠራቀመዉ ዉሃ እየተቀነሰ ወደ አስዋን ግድብ እንዲፈስ የሚለዉ የግብፅ የእጅ ጥምዘዛ አቋም በመጀመሪያ ያቀረበችዉን ከ 15 እስከ 21 ዓመት የመሙያ ጊዜ በእጅ አዙር መልሳ በማምጣት በክረምት ይሞላ የሚለዉን የመሸንገያ ቃል በመጠቀምና በድርቅ ጊዜ ይለቀቃል የሚለዉን ካርታ በመምዘዝ አዲስ ጨዋታ መጀመሯን የሚያሳይ ሙከራ ይታያል፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች እንደማይቀቡለት ብዙዎች ተስፋ የጣሉበት ነዉ፡፡ የግብፅን ፊላጎት ማሟላት እስከአሁን ኢትዮጵያ ያገኘችዉን ዉጤት ወደ ኋላ የሚቀለብስ ይሆናል፡፡
የአስዋን ዳም 196 ሜት ከፍታ ያለዉ 168 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ የሚያጠረቅም ግድብ ነዉ፡፡ ይህም ማለት የሕዳሴ ግድብን የዉሃ ማጠራቀሚያ ከእጥፍ በላይ ይበልጠዋል፡፡ ስለዚህም በድርቅ ጊዜ የሕዳሴ ግድብ የአስዋን ግድብ ማካካሻ ግብር መክፈል አለበት የሚለዉ የግብፅ ጥያቄ በሙሉ ከተካተተ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግደብን ለመሙላት ለምታደርገዉ ጥረት እጅግ የተጓተተ ዓመታት ይፈጅባታል፡፡ ግብፅ በዓባይ ወንዝ መጠቀም የሲናይ በረሃን ሙሉ በሙሉ ለማልማት ለያዘችዉ እቅድ ዉሃዉ የሚለቀቀዉ ከናስር ሃይቅ ነዉ ስለዚህም የአስዋን ግድብ በድርቅ ሰበብ ጎሎብናል ዉሃ ይለቀቅልኝ እያለች ኢትዮጵያን ማስቸገሯ በየጊዜዉ የማይቀረወ ነዉ፡፡
እ.ኢ.አ. በ1929 ዓ.ም በእንገሊዞች የተደነገገው ውል ለግብፅ 85 ከመቶ የሚሆነውን ውኃ እንድታገኝ ያደርጋል በተጨማሪም ከላይኛው ተፋሳሽ አገሮች የሚመነጨውን የተፋሳሽ ሃይል ግብፅ እንድትቆጣጠር የበላይነት ስልጣን በቅኝ ገዢዎች ተሰጥቷታል፡፡ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ለራሳቸው እንዲስማማ አድርገው የደነገጉትን የዓባይ ውሃ ክፍፍል እንዲሁም በ1959 ዓ/ም እ ኤ አ በግብፅ እና በሱዳን (ኢትዮጵያን ሳይጨምር) በተፈረመው ውል መሰረት ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ሱዳን ደግሞ 12 ቢሊዎን ኪውቢክ ሜትር ውሃ እንዲያግኙ ደንግጓል፡፡ እንግዲህ እንደዚህ አይነቱ መቀራመት ኢትዮጵያ ለእድገት የምታደርገውን ጥረት ያሰናከላል በእውነቱ ግብፅ በሲናይ በርሃና በካይሮ የምታባክነውን እና የምትበክለው ውሃ በቁጠባ እና በንፅህና ቢያዝ የውሃ እጥረት ድርቅ እንደ አደራዳሪ ነጥብ ሆኖ ባልቀረበም ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ የግብፅ እንዝላልነት ለአደራዳሪዎች በግልፅ ተቀምጦ ኢትዮጵያ ግብፅ ለምታባከነው ውሃ ማካካሻ ማግኘት ይኖርባታል፡፡
ግብፅ በየጊዜው አዲስ የመደራደሪያ ካርታ እየሳበች የምታደርገው ጫወታ በእጅ አዙር ከቅኝ ገዢዎች የወረሰችው ዓባይ የግሌ ብቻ የሚልውን ግትር አቋም ለማጠናከር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር ከልብ ሚዛናዊ በሆነ ክፍፍል ለመዋዋል አይመስልም፡፡ ድርድሩ ለመሰማማት የሚያቀራርብ ቢሆን ኖሮ የድርቅ ነገር ሳይነሳ ህዳሴ በክረምት ጊዜ ይሞላ የሚለው ቃል በስምምነት የሚያቀራርብ በሆነም ነበር፡፡ እዚህ ላይ ግብፅ ድርቅን እንደሰበብ በክረምት ይሞላ የሚለውን ደግሞ እንደ ሽፋን አድርጋ ያቀረበችው የተሸረበ ስልት እንደመሆኑ መጠን ግብፅ እንዳቀረበችው ውሉ የሚፈረም ከሆነ ኢትዮጵያን ወደ ማትወጣው ኪሳራ ይከታታል፡፡ ይህ ደሞ በአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን በሚምጣው ትውልድም ጠባሳ አሻራ ጥሎ የሚሄድ እዳ ነው ፡፡
ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስራዉ በሚቀጥለው ዓመት በሁለቱ ተርባይን ይጀመራል ብለው እንዲሁም 2023 እ.ኢ.አ. የህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ብለው “ማለም ብቻ ሳይሆን መከወንም እንደምንችል አረጋግጠናል” በማለት በኩራት ሲናገሩ የግብፅን መሰናክል ያለ አንዳች የውጭ ተፅኖ ለመውጣት የቆርጡ ይመስላል፡፡
ድርቅ ግብፅን አዘዉትሮ የተቆራኛት የተፈጥሮ ባላንጣዋ ስለሆነ በድርቅ ጊዜ ኢትዮጵያ ለግብፅ ዉሃ መልቀቅ አለባት የሚለዉ አንቀጽ በዉል ከፀደቀ የሕዳሴ ግድብን አሞላል ከታቀደው ጊዜ በጣም ያራዘመዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ፈጥኖ ለመጠቀም ያላትን እቅድ የሚያሰናክልና ለግብፅ ገደብ የሌለዉ ጥቅም ለኢትዮጵያ ደግሞ ገደብ የሌለዉ ጉዳት እንደሚያስከትል ግንዛቤ ዉስጥ መግባት ያለበት እሳቤ ነዉ፡፡ በዓመት እጅግ አነስተኛ የዝናብ ዉሃ እያገኘች ድርቅ የሚያጠቃትን ምድረ ግብፅ ዉሃ እየለቀቅን እንመግባለን የሚል ዉል ከተገባ ተመልሶ በቅኝ ገዥዎች ዘመን የተደረገዉን 55.5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የግብፅ ድርሻ በፊርማ እንደ ማፅድቅ ይቆጠራል ፡፡ እስከአሁንም የተገኘዉን ድል የሚንድ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር እሰከ አሁን በህዳሴ ግድብ ያደረገችዉ ድርድር እልባት ባይደረግለትም ሁለት ቋሚ ነገሮችን አስፈፅማለች፡፡
1ኛ ኢትዮጵያ ለዘመናት በቅኝ ገዥዎች ፍርድ የተነጠቀችዉን የዓባይ ባለቤትና የጥቅም መብት ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያን የዓባይ ቁንጮ መሠረት መሆኗን አምነዉ ነጋሪት ሳይጎሸም ፣ ክተት ሣይታወጅ ጦር ሰይሰበቅ እልቂትም ሳይካሄድ በሠላም መቀበላቸዉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስደሳች ዜና ነዉ፡፡
ግብፅና ሱዳን ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኖ እንደማይቀጥል የተረዱት ይመስላል፡፡ ግብፅ በአመት የ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ የኔ ድርሻ ስለሆነ እንኳንስ በቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ትማኒ በጭልፋስ አባይን ማን ይደፍራል የሚለዉን አቋሟን አለሳልሳ ለድርድር መቅረቧ ለኢትዮጵያ ትልቅ ግኝት ሆኖ ሳል ድርድሩ የሚሰክነው የኢትዮጵያን መብት እና የጥቅም ተካፋይ ሲያሰከብር ብቻ ነው ፡፡
2ኛ ሌላዉ በአገር ዉስጥ የተገኘዉ ዉጤት ነዉ፡፡ የህዳሴ ግድብ መገንባት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተቀነባበረ ዝርፊያ ሲካሄድበት የነበረና እንደ ጥገት ሲታለብ የዘገዬ ፕሮጀክት ነዉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን በመጡበት ጥቂት ወራት ተስተካክሎ ግንባታዉ እንዲቀጥል ተደርጎ አሁን ወደ ፍፃሜ መድረሱ ይነገራል፡፡ አሁን አገሪቷ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ውጥረት ሳያግዳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የህዳሴን ግድብ ለማሰጨረስ የሚያደርጉት ታላቅ የመሪነት ጥረት የሚሰመሰግን ነው፡፡ ይህ የሰዉ ሕይወት የተቀጨበት፤ የበርሃ ሃሩር የለሊት ቁር ሳያሳለቻቸዉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ላባቸዉን አንጠፍጠዉ የገነቡት፤ እናቶች ከመነቀነታቸዉ ፈተዉ አባዎራዎች ከቤተሰቦቸዉ አፍ ነጥቀዉ፤ በተወሰነ የመንግስት ደሞዝ ተዳዳሪዎች እና በውትድርና የሚያገለግሉ ዜጎች ቀበቶአቸዉን አጥብቀዉ ገበሬዎችና ነጋዴዎች እጃቸዉን ዘርግተዉ በሕብረት መዋጮ የተሰራ ግድብ ባክኖ ሳይቀር መጠናቀቁ በትዕግስትና በተስፋ አለመቁረጥ እተፈላጊዉ ግብ መድረስ የሚቻል መሆኑን የሚያገናዝብ ዉጤት ነዉ፡፡
ነገር ግን ፍሬያማ ውጤት አስገኘ ተብሎ በልበ ሙሉነት የሚነገረው ህዳሴ ተጠናቆ በ 13 ተርባየን ሙሉ ስራ ሲጀምር እና ምርቱም አሁን በሃገር ውስጥ ያለውን የመብራት እና የሃይል ፍላጎት አጥግቦ ለጎረቤት ሃገሮች ኃይል በማሰራጨት ገቢ ሲያስገኝ ነው ፡፡
የሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ 6,000 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመርት ከሆነ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሮች ከምታቀርበዉ የመብራት ሃይል ሽያጭ በዓመት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር እንደምታገኝ ይገመታል፡፡ ይህም ማለት ለግንባታ ያወጣችዉ 5 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ወደፊትም የመስመር ዝርጋታዉን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጋትን ከ 2 ቢሊየን ዶላር ያላነሰ ወጭ ለመመለስ ከስምንት ዓመት ያላነሰ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ የዉጭ ገቢ ማጣት ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ ዉስጥ ባለዉ የሃይል ስርጭት እጦት የተነሳ ፋብሪካዎች ያለማቋረጥ እየሰሩ ዉጤታማ ምርት ማምረት አለመቻላቸዉ ይነገራል፡፡ስለዚህም የህዳሴ መጓተት ኢትዮጵያን አያሌ ኪሣራ ያጋጥማታል፡፡
በመጨረሻም ይህ በዘመናችን የሚታየው የውሃ ውዝግብ በሰው ሰራሽ ህግ እና ድርድር እንደ መሆኑ መጠን አድሎ ያለው መደምደሚያ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጊዜው ይርዘም እንጂ ሰው ሰራሽ ህግን ፍጥረት ሰራሽ ህግ ይሽረዋል ፡፡ አሁን ያለው 112 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ በሚቀጥለው 20 ዓመታት በእጥፍ አድጎ በ2050 ወደ 188 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ይተመናል፡፡ ሰለዚህም የምግብ እጥረት፤ የቦታ ጥበት፤ የውሃ ፍላጎት፤ ያካባቢ ግለት በሚያሰከትለው ለውጥ የኢትዮጵያ ህዝብ መፈናፈኛ ሲያጣ በየአካባቢው ያሉትን የአባይ ገባር ወንዞች እነ ወለቃን ፤ የሹምን ፤ጃማን ወዘተ እየጠለፈ መጠቀሙ አስገዳጅ የመኖር እና አለመኖር ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህም ለዓባይ ተፋሰሽ አገሮች በተለይም ለግብፅ ሊረዳ የሚችለው የወደፊቱን በመገምገም በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከፀሃይ ሙቀት፤ ከመሬት እንፋሎት፤ ከንፋስ ግፊት እንዲሁም ከኒኩለር ኃይል የሚገኙ የሃይል አማራጮችን ፈልጎ ማዳበር ነው ፡፡ ከዚህም በማያያዝ ግብፅ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ተባብርው የአባይን ሸለቆን ስነ ምህዳር በልምላሜ መጠበቅ ነው
_____________________________________________________________________________________________________________
የዚህ አስተያየት አቅራቢ ዶክተር ንጉሴ ነጋ በዩናይትድ ስቴት የአካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ከ20 ዓመታት በላይ በተቀዳሚ አማካሪነት የሰራና ከዚያም በፊት የዋሽንግተን ከተማ ማዘጋጃ ቤት የዕቅድና የፕሮጀክት ሓላፊ ሆኖ የሰራ ነው፡፡