የኦነግን አቀባበል ተከትሎ በአዲስ አበባ ቡራዩና አካባቢው ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘና በሽብርተኝነት የተከሰሱት የአዲስ አበባ ወጣቶች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ከቀናት በፊት 17 ያህል በተመሳሳይ ክስ የቀረቡ የከተማው ወጣቶችን ክስ ፍርድ ቤቱ ወደግድያ ወንጀል እንደቀየረው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት 33 ተጠርጣሪዎች የቀረቡ ሲሆን መርማሪ ፖሊስም ያቀረበው ክስ ሽብርተኝነት ነበር፡፡ በዚህ መሰረት መርማሪ ፖሊስ በወቅቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሙሉ ምስክርነት ቃል ለመቀበል እንዲሁም ተጎጅዎችን በአካል ማነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት 28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው እያቀረባቸው ያለው ሀሳቦች ተደጋጋሚና የተከሳሾችን የዋስትና መብት የሚጋፋ በመሆኑ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ወይም ደግሞ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ጥያቅ ውድቅ በማድረግ ተከሳሾ በ15 ሺ ብር ዋስ እንዲፈቱ ትእዛዝ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም መርማሪውና አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቃቸው የዋስትናው ትእዛዝ ታግዷል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=YJYMYnduprQ&t=125s