በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና በኦሮሚያ አዋሳኝ ሊሙ ወረዳ አርቁምቤ በሚባል አካባቢ በታጣቂዎች የተገደሉ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በአምቦ ከተማ ሽኝት ተደረገላቸው።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና በኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዋች ቢያንስ 35 የኦሮሚያ ፖሊስና የኦሮሚያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ የለም:: ከዚህ ቀደም በቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ወታደሮች ህጻናትን ጭምር በክልሉ ለጦርነት እያሰለጠኑ መሆኑንና ከስልጠና ላይ ጭምር ወታደሮች መያዛቸውን መንግስት ሲገልጽ ቢቆይም ማን እንዳስታጠቃቸውና ከጀርባቸው እንዳለ የተገለጸ ነገር የለም::
በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች በአካባቢው ነዋሪዎች እና በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ላይ አሰቃቂ ወንጀል መፈጸሙን የሚገልጹ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በግጭቱ ህይወታቸው ያለፈ እና የተጎዱ ሰዎች ቁጥር በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል::
ጨምረውም “በግጭቱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስክሬን በትናንትናው እለት ነቀምቴ ከተማ ሲገባ ህዝቡ ሰልፍ በመውጣት ስሜታዊ በመሆኑ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል::: በምእራብ ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት የክልሉን እና የሀገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ እንዲሁም አሁን በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ አካላት ናቸው” ያሉት አቶ ደሬሳ የእነዚህ አካላት እቅድም እንደ ኦሮሚያ ክልል እና እንደ ሀገር እየመጣ ያለውን ለውጥ ማደናቀፍ ስለሆኑ ህዝቡ ከስሜታዊነት በመውጣት መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚወስደውን እርምጃ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል::
ይህን ተከትሎም በዛሬው ዕለት ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ፥ በክልሎች ወሰን አካባቢ የሚፈጠሩ ግጭቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልድና የጧፍ ማብራት ስነሥርዓት በነቀምት, በሻምቡ እና በምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞች ሲካሄዱ ውለዋል:: መንግስት ዜጎችን ከሞትና ከመፈናቀል ሊያስቆም ይገባል የሚሉት ሰልፈኞቹ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ሲሉም ጠይቀዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ዙሪያ በዶ/ር አብይ አህመድ እና ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል::
አቶ አዲሱ አረጋ እንዳስታወቁት ማዕከላዊ ኮሚቴው በኦሮሚያ ክልል የሰላም ሁኔታ ላይ ጠንካራ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል:: ውሳኔው እንደደረሰልን እናቀርባለን::
አክቲቭስት ጀዋር መሐመድ ባለፈው ሳምንት ሕወሓቱ ጌታቸው አሰፋ በአስቸኳይ ካልታሰረ በስተቀር በየክልሎች ዳግም ብጥብጦችን ሊያስነሳ እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል:: ጌታቸው አሰፋም የ እስር ማዘዣ ከወጣበት ቢቆይም እስካሁን በቁጥጥር ሥር አልዋለም::
https://www.youtube.com/watch?v=_Ed6iA2v558&t=91s