ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፣ እውነትና ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ ዕርቅ እንዲወርድ የሚሠራ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ሐሙስ ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀረበ።
ኮሚሽኑን ለማቋቋም ያስፈለገው በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌሎች በደሎች ተጠቂ የሆኑ ወይም ተጠቂ ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች፣ በደላቸውን የሚናገሩበትና በደል ያደረሱ ዜጎች ላደረሱት በደል በግልጽ በማውጣት ይቅርታ የሚጠይቁበት መንገድ በማበጀትና ዕርቀ ሰላም በማውረድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መሆኑን ረቂቁ ይገልጻል።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ የሚሾሙ ሲሆን፣ ኮሚሽኑም ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም እንደሚደረግና በኃላፊነት የሚቆየውም ለሦስት ዓመታት እንደሚሆን ረቂቁ ያስረዳል።
ፓርላማው ረቂቁን ከተመለከተ በኋላ በደል የፈጸመ እንዴት በበጎ ፈቃድ ሊገኝ ይችላል? ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ ሥልጣናት ጋር አይጋጭም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በዝርዝር እንዲታዩ ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተመሳሳይ የማንነትና የወሰን አስተዳደር ኮሚሽን ለማቋቋም ሌላ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀርቧል። የፓርላማው አባላት በዚህ ረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በዋነኝነት ያነሱት ጥያቄ፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ጋር ይቃረናል የሚል ነው፡፡ ይህም አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
Source: Reporter Newspaper