ከወልቃይት ተፈናቅለው ለፌዴራል መንግት ባለስልጣናት አቤቱታ ለማቅረብ አዲስ አበባ የሚገኙት ግለሰቦች በፖሊስ ተከበናል አሉ፡፡ ዛሬ ለንባብ የበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው እነዚህ ‹‹የአማራ የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል›› ተብለው ከቀዬአቸው ተባረው አዲስ አበባ ከተማ የመጡት 180 ሰዎች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ በፖሊስ መታገታቸውን ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ አቤቱታቸው ከትውልድ ቄዬአቸው በመባረራቸው ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታና ዕገዛ እንዲደረግላቸው ለማመልከት፣ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ከተማ መምጣታቸውን እንደሚያብራራ ጋዜጣው አስረድቷል፡፡ ግለሰቦቹ አዲስ አበባ ከተማ ሲገቡ ስለመሸባቸውና ማደሪያ በማጣታቸው፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በተባለ የፖለቲካ ድርጅት የተከራየው ቢሮ ግቢ ውስጥ እንዲያድሩ ተፈቅዶላቸው እንደገቡ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊሶች፣ ግለሰቦቹ በገቡበት አጥር ዙሪያ በመቆም ወደ የትኛውም ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ያገዷቸው መሆኑንና ዘጠኝ ቀናት (እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) እንደሆናቸውም ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል፡፡ እንደሪፖርተር ዘገባ ግለሰቦቹ አቤቱታቸውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ለማቅረብ ካለመቻላቸውም በተጨማሪ፣ በከፍተኛ ረሃብና ብርድ እየተሰቃዩ መሆኑን ጠበቃው በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡ አካባቢውም ሽታ ያለበት በመሆኑ ለበሽታ እየተጋለጡና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብታቸው የተጣሰ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ግለሰቦቹ አቤቱታቸውን ለመንግሥት እንዳያቀርቡና ሕዝብ ዓይቷቸው ዕርዳታ እንዳያገኙ በፖሊስ መገደባቸውን ጠቁመው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ተደንግጎ የሚገኘው የመዘዋወር መብታቸው መገደቡንም አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸውን ከተመለከተው በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ ነገ ጥቅምት 29 ቀን ከጠዋቱ 5 ሰአት ላይ ቀርበው ስለሁኔታው እንዲያስረዱ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ከቀዬአቸው ስለተባረሩ፣ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታ ለመጠየቅና ወደ ቀዬአቸው እንዲመልሳቸው አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ የመጡትን የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች፣ ፖሊስ ለምን እንዳገታቸው ወይም እንዳይንቀሳቀሱ እንደገደባቸው ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ፣ ‹‹ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው በሠልፍ መንቀሳቀስ የለባቸውም›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን በተወካይ ከአምስት እስከ 20 እየሆኑ ለሚመለከተው አካል ጥያቄያቸውን እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ግለሰቦቹ እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ሳይሆን ፖሊስ ለእነሱም ደኅንነት ጥበቃ ማድረግ ስላለበት፣ ጥበቃ እያደረገላቸው እንጂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል›› ብለዋል፡፡ ሁሉም በሠልፍ ሆነው ሁከት እንዳይፈጥሩ እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ ሜጀር ጄኔራል ደግፌ ማስረዳታቸውን ሪፖርተር ጨምሮ አትቷል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=LCftg3owFj4&t=4s