ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.
ርዕሰ ዜና
የሳኡዲ መንግስት ኢትዮጵያውያንን አሰረ
በሜዲትራኒያን ባህር ለወደቀው የግብጽ አውሮፕላን ምክንያት በአውሮፕላን ውስጥ የተቀጣጠለ እሳት ነው ተባለ
የዚምባብዊ አርበኞች ማህበር የፕሬዚዳንት ሙጋቤን መንግስት አወግዞ ድጋፍ እንደማይሰጥ ገለጸ
የብሩንዲ ባለስልጣን የሆኑንት ሴት የገደሉ ሰዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የኮንጎ ፕሬዚዳንት የምህረት አዋጅ አወጁ
(ፎቶ ከፋይል)
ዝርዝር ዜናዎች
የሳኡዲ መንግስት ሕገ ወጥ ስራ ሲሰሩ ነበር ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ያሰረ መሆኑ ታውቋል።
አሲር በሚባለው ቦታ ላይ የወያን ጠጅና የአልኮል መጠጥ ሲሰሩ ነበር የተባሉ ሶስት ኢትዮጵያውያን
የተያዙ ሲሆን ዑሁድ ራፊዳ ከተባለው ቦታ ደግሞ አንድ ኢትዮጵያዊ አውቶማቲክ መሳሪያ ከነጥይቱ
ተገኝቶበታል በማለት ከሌሎች ስድስት ኢትዮጵያውያን ጋር በቁጥTር ስር የተደረጉ መሆናቸው
ተነግሯል። የሳኡዲ ባለስጣኖች የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠሩ ኢትዮጵያውያን ሲያሰቃዩ
መቆየታቸው ይታወቃል።
ባለፈው ግንቦት ወር ከፓሪስ ወደ ካይሮ ሲጓዝ ከአየር ላይ ወድቆ በሜዲትራኒያን ባህር የሰጠመው
የግብጽ መጓጓዣ አውሮፕላን ጥቁር ሳጥኖች ተገኝተው እየተመረመሩ መሆናቸው ከዚህ በፊት
የተዘገበ ሲሆን ምርመራውን ከሚያደርጉት ክፍሎች ከተገኘ ምንጭ አውሮፕላኑ የወደቀው
አብራሪዎቹ ከሚቀመጡበት አጠገብ ተነስቶ በተቀጣጠለ እሳት መሆኑን ተነግሯል። እሳቱ
ሊቀጣጠል የቻለው በቴክኒካል ጉድለት ይሁን ወይም በሽብር ተግባር በተሰማሩ ሰዎች ለማረጋገጥ
ያልተቻለ መሆኑን በምርመራው አካባቢው ያሉ ምንጮች ገልጸዋል። የግብጽ አየር መንገድ
አውሮፕላን 56 መንገደኞችና 10 የአውሮፕላኑ ሰራተኞችን አሳፍሮ የነብረና በአደጋው ሁሉም
ህይወታቸውን ማጣቸው ይታወቃል።
የዚምባዌ ብሄራዊ የአርበኞች ማህበር የተባለ ድርጅት የፕሬዚዳንት ሙጋቤን አስተዳደር ማውገዙ
ታወቀ። ቀድም ብሎ ለፕሬዚዳንት ሙጋቤ ሙሉ ድጋፉን ሲሰጥ የነበረውና በዚምባብዌ ዜጎች
ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠው የአርበኞቹ ማህበር ባሰራጨው መግለጫ የፕሬዚዳንት ሙጋቢ
አምባገነናዊ አስተዳደር ዚምባብዌን ነጻ ለማድረግ ተጋድሎ ከተደረገበት ዓላማ የራቀ መሆኑን
በመግለጽ አውግዞ ከእንግዲህ ፕሬዚዳንቱን ለምርጫ እንደማይደግፍ ገልጿል። የዚምባብዌ
መንግስት አርበኞቹ ማህበር ያሰራጨውን መግለጫ ሕገ ወጥና በወንጀል የሚያስከሥ ነው ካለ
በኋላ የመግለጫውን ምንጭ ለማጣራት ምርመራ እንደሚያካሂድ አስታውቋል። በሌላ በኩል
ሙቭመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ (MDC) የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ ባሰራጨው ዘገባ የሙጋቤ
አምባገነን የሚፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት የአርበኞች ማህበር በመጨረሻ ሊረዳ በመቻሉ የተደሰተ
መሆኑን ገልጾ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ጊዜ ያለፈባቸው አምባገነን በመሆናቸው ባስቸኳይ ስልጣን
መልቀቅ አለባቸው ብሏል።
ከአስር ቀን በፊት በብሩንዲ ዋና ከተማ በቡጁምቡራ የቀድሞ ሚኒስትር እና የፓርላማ አባል
ባልታወቁ ሰዎች መገደላችው የተዘገበ ሲሆን ሐሙስ ሐምሌ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ገዳዮች ናቸው
ተብለው ሶስት ሰዎች መያዛቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ገልጿል። የሰዎቹ ማንነት ያልተገለጸ ሲሆን
የተቃዋሚ ክፍሎች አባሎች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ተገምቷል።
የኮንጎ ፕሬዚዳንት ሚስተር ካቢላ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኘውን ከፍተኛ የፖሊቲካ ውጥረት ለማላላት
አጠቃላይ የሆነ የምህረት አዋጅ ያወጁ መሆናቸው ተነግሯል። ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር
አይችሉም በማለት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው በቅርቡ የታሰሩት ዜጎች በሙሉ እንዲፈቱ ያዘዙ
ሲሆን በሌሎች እስረኞችም ላይ የቅጣት ለውጥ እንዲደረግ አውጀዋል። በሞት እንዲቀጡ
የተፈረደባችው በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ፤ በእድሜ ልክ እስራት የተቀጡት ደግሞ
ቅጣታቸው በሃያ አመት እስራት እንዲሆን አድርገዋል። ሴቶች፤ ከስድሳ አምስት በላይ የሆኑ
አዛውንቶችና ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ከአጭር ጊዜ እስር በኋላ እንዲፈቱ አውጀዋል።
ሚስተር ካቢላ አዋጁን ያወጁት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ዋና ኃላፊ
ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተገናኝተው የዜጎች የንግግር ነጻነት መገደቡ የሚያሳስባቸው መሆኑን ከገለጹላቸው
በኋላ ነው ተብሏል።