ከይርጋ አበበ
ትናንት በአሥር ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽንስ ዋንጫ ጨዋታ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የግብጹን ኢ.ኤን. ፒ.ፒ. አይ ( Enginering and Petrolium Processing Industry) ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን አመቻቸ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በግብጹ ኃያል ክለብ ዛማሌክ ከሜዳ ውጪ ብዙ ባገባ በሚል ሕግ ከአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የተሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሌላኛው የአህጉራዊ ውድድር የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሌላውን የግብጹን ክለብ በሜዳውና በደጋፊዎቹ ፊት ሁለት ለባዶ በማሸነፍ በዛማሌክ የደረሰበትን የውጤት ማጣት ፀፀት መመለስ ችሏል።
ጨዋታው በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ከያሬድ ዝናቡ የተሻገረችለትን ኳስ ከኢ.ኤን.ፒ. ፒ.አይ ተከላካዮች ሾልኮ በመግባት የጊዮርጊሶችን የመጀመሪያ ግብ አስቆጠረ። ሽመልስ ያስቆጠራት ግብ ባለፉት አራት ተከታታይ የክለቡ ጨዋታዎች ሦስተኛ ግቡ ሆና ተመዝግባለታለች። ትንሹ ልጅ ግብ ከማስቆጠሩም በላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነበር ያመሸው።
ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተጋጣሚዎቻቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲመላለሱ ቢታዩም በ26ኛው ደቂቃ ተከላካዩ አበባው ቡጣቆ ሁለተኛዋን ግብ እስካስቆጠረበት ደቂቃ ድረስ ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም ነበር። ወጣቱ አጥቂ ዮናታን ብርሃኔ ከማዕዘን ያሻገረለትን ኳስ ከአስራ ስምንት ክልል ውጪ ወደ ግቡ መስመር አክርሮ በመምታት አበባው ቡጣቆ ሁለተኛዋንና የጨዋታውን የመጨረሻ ግብ ማስቆጠር ቻለ።
ሁለት ወጣት የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ በስታዲየም የጋብቻ ሥነ-ሥርዓታቸውን በመፈፀም ለክለቡ ያላቸውን ፍቅር በገለጹበት ጨዋታ፣ ፈረሰኞቹ ብዙ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን ሲያመክኑ አምሽተዋል። በተለይ ሁለተኛዋ ግብ ከተቆጠረች ሦስት ደቂቃ በኋላ አማካዩ ዊሊያምስ አክርሮ የመታትና የኢ.ኤን.ፒ.ፒ.አዩ ግብ ጠባቂ የመለሰበት ኳስ ተመልካቾችን ያስቆጨች ነበረች፡፡
ከዕረፍት በኋላ ተዳክመው ያመሹት ኢትዮጵያውያኑ በግብጻውያን አቻዎቻቸው የጨዋታ ብልጫ የተወሠደባቸው ሲሆን እንግዳው ቡድንም ሁለት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።
ከሰባት ዓመት በፊት ሁለቱ ክለቦች በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተገናኝተው ካይሮ ላይ ዜሮ ለዜሮ ሲለያዩ በአዲስ አበባ ቢኒያም አሰፋ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋ ይታወሳል።
የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢ.ኤን.ፒ.ፒ.አይ የመልስ ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በኋላ በግብጿ ዋና ከተማ ካይሮ ላይ ይደረጋል።