የዘንድሮውን የአውሮፓ እግርኳስን በዝውውር ሊያደምቁ የሚችሉ 9 ተጫዋቾች

May 20, 2013

ከይርጋ አበበ
የአውሮፓ ሊጎች የውስጥ ውድድሮች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ ከሚጠበቁት ታላቅ የእግር ኳስ ዜናዎች መካከል ክለቦች የሚያደርጉት የተጫዋቾች ዝውውር አንዱ ነው። ውጤት ፊቱን ያዞረባቸው ታሪካቸውን ለመቀየር ውጤት እና እድል አብራቸው የከረመች ደግሞ ክብራቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ክለባችንን እና ኪሳችንን ይመጥናሉ ያሏቸውን ተጫዋቾች ወደ ክለባቸው ለማዘዋወር ይንቀሳቀሳሉ። ለዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን ምንጭ የሆኑን የእንግሊዞቹ ዘሰን፣ ዘኢንዲፔንደንት፣ ቢቢሲ እና የስፔኑ አስ ጋዜጦች የዝውውር መስኮቱን ሊያደምቁ ይችላሉ ያሏቸውን ተጫዋቾች ያስነበቡ ሲሆን እኛም ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አዘጋጅተንላችኋል።
1. ዋይኒ ማርክ ሩኒ
እንግሊዛዊው አጥቂ በክለቡ እያሳለፈ ያለውን ሁኔታ ያልወደደው ሲሆን ከቀድሞው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጋር የፈጠረው አለመግባባት ወደ ውጪ እንዲመለከት ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል። የዋዛን ሁኔታ በቅርብ ርቀት የሚከታተሉት የፈረንሳይ ሻምፒዮኖቹ ፓሪሴንት ጄርሜኖዎች እንግሊዛዊውን ወደ ክለባቸው ወስደው ከዝላታን ኢብራሞቪች ጋር ለማጣመር ፍላጎታቸውን መደበቅ ተስኗቸው ካሁኑ የማንቸስተርን በር ማንኳኳት ጀምረዋል። ሌሎቹ የልጁ ፈላጊ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ስፔናውያኑ ግዙፎቹ ባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ ናቸው።
2.ኔይማር
ብራዚላዊው ወጣት ከባርሴሎና ጋር ቅድመ ስምምነት ላይ ደርሷል ቢባልም ሌላኛው የስፔን ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ የተጫዋቹ ፈላጊ መሆኑን በመግለፅ ወደ ጨረታው ገብቷል። እንደ ስፔኑ አስ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ የፍሎሬንቲኖ ፔሬዙ ክለብ ኔይማርን ከባላንጣቸው እጅ ላይ በመንጠቅ ለብራዚሉ ክለብ ለዝውውር የሰባ ሚሊዮን ፓውንድ ቼክ ይዘው መፈተን ጀምረዋል። ኔይማር የማድሪድን ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ሳንቲያጎ ቤርናባው የሚሄድ ከሆነ ከሀገሩ ልጆች ካካ እና ማርሴሎ ደማቅ አቀባበል እንደሚጠብቀው ተጫዋቾቹ በመናገር ላይ ናቸው። የብራዚላዊው ለማድሪድ መፈረም ማድሪድ በመሐል ሜዳ ላይ የኳስ ፈጣሪ ተጫዋች እጥረቱን ይቀርፍለታል ተብሎ ይታሰባል።
3.ጃክ ዌልሸር
ይህ የሚሆን ይመስላችኋል?የአርሰናሉ ታዳጊ ከለንደኑ ክለብ ይለቃል ተብሎ ባይታሰብም አዲሱ የባየር ሙኒክ አሰልጣኝ ጆሴፕ ጋርዲዮላ ተደጋጋሚ ጥያቄዎቹን ይዞ ወደ እንግሊዙ ክለብ መመላለሱ የጃክ ቀጣይ ክለብ ባየር ሙኒክ ሊሆን ይችላል ሲል ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል። አርሰን ቬንገር የቀጣዩ የውድድር ዓመት የክለባቸው አምበል ያደርጉታል ተብሎ የሚጠበቀው እንግሊዛዊው ወጣት የእኔና የአርሴናል ጋብቻ በቀላሉ አይፈርስም ብሎ መናገሩ ምናልባት ለጋርዲዮላ ፈተና ሊሆንበት ይችላል። ጋርዲዮላ ተሳክቶለት ጃክን ወደ ክለቡ ካዘዋወረ ትልቅ ዝውውር ይሆንለታል።
4.ካሪም ቤንዜማ
አሌክስ ፈርጉሰንን ተክተው ወደ ኦልድትራፎርድ የተዘዋወሩት ስኮትላንዳዊው ዴቪድ ሞይስ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በክለባቸው ሊመለከቱት የሚፈልጉት ተጫዋች ቢኖር በሳንቲያጎ ቤርናባው ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የተሳነውን ካሪም ቤንዜማ ነው። ይህንን ፈረንሳያዊ ወደ ማንቸስተር አምጥተው የእግር ኳስ ህይወቱን ሊታደጉለት ይፈልጋሉ። ለስፔኑ ክለብ የ30ሚሊዮን ፓውንድ ቼክ ይዘው የቀረቡት ሞይስ ቤንዜማን ወደ ማንቸስተር ማዘዋወር ከቻሉ አስፈሪ የአጥቂ መስመር መገንባት እንደሚችሉ ዘኢንዲፔንደንት በዘገባው ጠቅሷል። ዘገባው የካሪም ዝውውር የዝውውር ገበያውን ያደምቃል ያስባለውም የልጁ ብቃት መሆኑን ጨምሮ አመልክቷል።
5.ማሩዋን ፌይላኒ
ፌይላኒን በኤቨርተን ጠንቅቀው የሚያቁት ዴቪድ ሞይስ ወደ ኦልድትራፎርድ አብሯቸው እንዲጓዝ ይፈልጋሉ። ላለፉት ጥቂት ዓመታት ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኤቨርተን ሲገናኙ በቀያይ ሰይጣኖቹ ላይ የበላይነቱን ሲወስድ የነበረው ቤልጄማዊ ጉልበተኛ የቀድሞ አሰልጣኙን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ላንክሻዬር ዝውውር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የግሌዘር ቤተሰቦች ቤልጄማዊውን ሁለገብ ተጫዋች ወደ ክለባቸው ለማዘዋወር የ24 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ መፈፀም እንዳለባቸው የተነገራቸው ሲሆን፤ ዴቪድ ሞይስም ግድ የለም በእኔ ይሁንባችሁ ማሩዋንን ለማግኘት የፈለገውን መስዋዕትነት መክፈል አለብን ሲሉ ለአዲሶቹ ቀጣሪዎቻቸው ተናግረዋል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።
6.ሌይተን ቤይንስ
የቀድሞው የዊጋን አትሌቲክ የግራ መስመር ተከላካይ ላለፉት ሁለት ዓመታት የፈርጉሰንን ትኩረት መሳብ የቻለ ተጫዋች ነበር። በማጥቃት ላይ የተመሰረተ መከላከልን የሚመርጠው እንግሊዛዊ በአርሴናል፣ ቼልሲ፣ ባየር ሙኒክ እና ባርሴሎና ቢፈለግም የቀድሞ አሠልጣኙን ተከትሎ ቀዩን ማሊያ ይለብሳል የሚለው ግምት የበዛ ሆኗል። የ15 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣለት ቢሆንም እድሜው እንደሚፈልገው እንዳይጫወት ያደረገውን ፓትሪስ ኢቭራን ለመተካት ብቸኛው ተጫዋች መሆኑን የተረዱት የማን ዩናይትድ ኃላፊዎች የገንዘቡን ነገር ተውት ብቻ ልጁን ስጡን በማለት የመርሲሳይዱን ክለብ መወትወት ጀምረዋል።
7. ክርስቲያን ኤሪክሰን
ቤልጂየማዊው የ21 ዓመት ወጣት አጥቂ በሊቨርፑል በጥብቅ ይፈለጋል። ወጣቱ ቤልጂየማዊ ግን የሀገሩ ልጆች በብዛት የሚገኙበትን ፕሪሚየር ሊግ ችላ ብሎ ወደ ቡንደስሊጋው መዘዋወርን መርጧል። ከውድድር ዓመቱ መጠናቀቅ በኋላ ፖላንዳዊውን ግብ አዳኝ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ የማጣት ስጋት የተጋረጠባቸው ቦሩሲያ ዶርትመንዶች የክርስቲያን ኤሪክሰን ማረፊያ ለመሆን ተቃርበዋል። ማሪዮ ጉትዝን ለባባሪያኑ ባየር ሙኒክ አሳልፈው የሰጡትና ሌዋንዶውስኪንም ላለማጣታቸው ዋስትና የሌላቸው ጀርመናውያኑ ኤሪክሰንን ከአያክስ አምስተርዳም ለመግዛት ከሊቨርፑል ከባድ ፈተና ቢጠብቃቸውም የልጁ ምርጫ በመሆናቸው የዝውውር መስኮቱ እንደተከፈተ ወደ ክለባቸው ያዘዋውሩታል ተብሎ ይጠበቃል።
8. ፊል ጃግዬልካ
በአርሴናሉ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በጥብቅ የሚፈለገው የ30 ዓመቱ ጃግዬልካ ዴቪድ ሞይስን ተከትሎ ከመርሲሳይዱ ክለብ የሚለቅ ተጫዋች ይሆናል ሲል ዘሰን ጋዜጣ አስነብቧል። የአስር ሚሊዮን ዋጋ የተቆረጠለት ቢሆንም ሪዮ ፈርዲናንድን የሚያጣው እና የኒማኒያ ቪዲችን የተሟላ አገልግሎት ማግኘት የማይችለው ማንቸስተር ዩናይትድ የሰላሳ ዓመቱን ተከላካይ ለማዘዋወር ፍላጎቱን በአዲሱ አሰልጣኙ በኩል ገልጿል። እንግሊዛዊው የኤቨርተን ሁለተኛ አምበል ወደ ዩናይትድ የሚያደርገው ዝውውር የተጫዋቾችን የዝውውር ገበያ ከሚያደምቁ ተጫዋቾች አንዱ ይሆናል ሲል ጋዜጣው ጨምሮ ገልጿል።
9. ጋሪ ሁፐር
በሴልቲክ ስኬታማ የውድድር ዘመን ያሳለፈውን የ25 ዓመት ወጣት ለማግኘት ከፕሪሚየር ሊጉ የወረዱት የኪው ፒ አር አሰልጣኝ ሃሪ ሬድናፕ ፍላጎት እንዳላቸው ዘኢንዲፔንደንት ገልጿል። የገንዘብ ችግር የሌለበት ኪው ፒ አር የውል ዘመኑ ሊጠናቀቅ የ6 ወር እድሜ ብቻ የሚቀረውን አጥቂ ለማዘዋወር 2ነጥብ 4 ሚሊዮን ፓውንድ የመደቡ ሲሆን ተጫዋቹን በተጠቀሰው ዋጋ አዘዋውረው በሻምፒዮን ሺፑ ያጫውቱታል ተብሎ አይጠበቅም። ነገር ግን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሃያ ዘጠኝ ግቦችን ለስኮትላንዱ ክለብ ያስቆጠረውን እንግሊዛዊ በፕሪሚየር ሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ሊያዘዋውሩት እንደሚችሉ ይጠበቃል። ልጁ ካለው ችሎታ አንጻር የዝውውር መስኮቱን ያደምቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ተጫዋቾች አንዱ ሊሆን ችሏል።

Previous Story

የሚኒሶታው መድሃኔዓለም ሁለቱ ሲኖዶሶች እስከሚታረቁ በገልተኛነቱ ሊቆይ ይገባል

Next Story

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸነፈ

Go toTop