(ዘ-ሐበሻ) ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁትን እና ለዓለም ዋንጫ ለማለፍም ከማጣሪያ አድርሰውት የነበሩትን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ያሰናበተው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን የ57 ዓመቱ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ዋልያዎቹን በዋና አሰልጣኝነት ለማሰልጠን መቅጠሩን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀ ባሬቶ ከፊሊፖቪች እና ላርስ ኦሎፍ ከተባሉ አሰልጣኞች ጋር የተወዳደሩ ሲሆን፤ ባሬቶ ም በመጪዉ እሁድ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ፖርቱጋላዊው ባሬቶ ምክትል አሰልጣኝ በተመለከተ ከኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ጋር እሰራለሁ ሲሉ የተሰማሙ ሲሆን የትኛው አሰልጣኝ በሚለው ላይም ምርጫዉን እራሱ ባሬቶ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የስፖርት ተንታኞች ገልጸዋል።
በወር በ15 ሺህ ዶላር (280 ሺህ 500 ብር) ወርሀዊ ክፍያ ዋሊያዎቹን ለማሰልጠን የተዋዋሉት ፖርቱጋላዊው ባሬቶ ከዚህ በፊት የጋናን ብሄራዊ ቡድን፣ የሩሲያውን ኩባን ክራስኖዳን እና ዳይናሞ ሞስኮ ክለብን እንዲሁም የዱባዩን አልናስር ክለብ አሰልጥነዋል።
ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ኢትዮጵያ የውጭ ሃገር አሰልጣኝ በመቅጠሯ ብቻ ውጤት ታመጣለች ብሎ እንደማያምን የገለጸበትን አስተያየት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ