ሕይወት ሽንኩርት ናት:: ስትላጥ ብታስለቅስም ስትበስል ግን ትጣፍጣለች:: ከሕይወት ስንክሳሮች መካከል ደግሞ አንዱ ስደት ነው:: የሰው ልጅ የተሻለ ኑሮን ወይንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ሲሰደድ እንደሽንኩርቷ በችግር ሲላጥ አልቅሶ; የተፈተነበት ውጤት ሲያልፍ ደስተኛ ይሆናል:: የዛሬዋ እንግዳችን በሚኒሶታ ብቸኛዋ የታክሲ ሹፌር የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ቅድስትም በሕይወት ስንክሳር ብዙ ተፈትና ዛሬ እዚህ ደርሳለች:: የዚህችን ሴት ታሪክ ሰማንና የጋዜጣችን እንግዳ ለማድረግ ወደ ስልኳ በተደጋጋሚ ደወልን:: ከስልኳ የምናገኘው you have reached the voicemail of…. የሚለውን አናዳጅ ምላሽ ነበር:: ሆኖም ግን በነዚህ ቃላት መካከል “ኪኪ” የሚል ድምጽ ስናገኝ ስልኳ የእርሷ መሆኑን አረጋግጠን ድወላችንን ቀጠልን:: ምላሽ ስናጣም የድምጽ መልዕክት አስቀመጥን; ቅድስት ወይም ኪኪ ወዲያውኑ ስልካችንን መለሰች:: ከዛም የሚከተለውን እዛው የምትሠራበት ፖስት ሮድ ተቀጣጥረን የታክሲዋን መስኮት ከፍተን አወራን::
ዘ-ሐበሻ:- ተጀመረ!
ቅድስት:- ምኑ?
ዘ-ሐበሻ:- ቃለ ምልልሱ!
ቅድስት:- (ሳቅ…)
ዘ-ሐበሻ:- ምነው? አልተዘጋጀሽበትም እንዴ?
ቅድስት:- ኸረ እንደውም!
ዘ-ሐበሻ:- የፈራሽ ትመስያለሽ?…
ቅድስት:- እንዴ እኔ ለኢንተርቪው አዲስ አይደለሁም እኮ!… ድሮ እኔም ራሴው ኢንተርቪው አደርግ ነበር::
ዘ-ሐበሻ:- ኦው! ጥሩ:: ታዲያ ራስሽም ቃለ-ምልልስ ታደርጊ ከነበረ; እንዲሁም ብዙ ሰው ቃለ-ምልልስ ሲደረግለት አይተሻልና ጋዜጠኞች ብዙ ጊዜ አስቀድመው የሚጠይቁት ነገር ስለምንድን ነው?
ቅድስት:- ስለማንነት!…. ከራሳቸው ላይፍ ስታይል.. ከስማቸው ያሉበትን የመጡበትን….
ዘ-ሐበሻ:- ታዲያ እኛም ከእርሱ እንጀምር?…
ቅድስት:- እንደፈለክ!
ዘ-ሐበሻ:- ይሄንን በቅድሚያ ብጠየቅ የምትይው ነገር ካለ?
ቅድስት:- ይሄን ብጠየቅ?
ዘ-ሐበሻ:- አዎ!
ቅድስት:- (ሳቅ!..) የሥራ ሁኔታ እንዴት ነው? አንቺ ሴት ሆነሽ እንዴት እዚህ ቦታ እንዴት መጣሽ? ብቻሽን ነሽና እንዴት ልትመጪ ቻልሽ ምናምን…. ነው መስለኝ ጥያቄው የሚመስለኝ… (ሳቅ) እና ተደሰቺበታለሽ ወይ በሥራው? ይመስለኛል…
ዘ-ሐበሻ:- እሺ ቅድስት ማናት ብለን እንጀምር!…
ቅድስት:- ቅድስት ታዬ::
ዘ-ሐበሻ:- ይህን ጋዜጣ ለሚያነቡ ሰዎች ራስሽን አስተዋውቂ ብትባይ እንዴት ራስሽን ትገልጪዋለሽ?
ቅድስት:- የመጣሁት ከኢትዮጵያ ነው:: ተወልጄ ያደግኩትም ጅማ ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ከተማርኩና ከሰራሁ በሗላ ወደ አውሮፓ ሄድኩኝ:: ከአውሮፓ ወደ እዚህ መጣሁ:: ወደዚህ ሙቭ (ሀገር የቀየርኩት) ያደረግኩት በ1998 ነው::
ዘ-ሐበሻ:- አውሮፓ የት ነበርሽ?
ቅድስት:- ስዊድን ነበርኩ!…
ዘ-ሐበሻ:- እንዴት ነበር ወደ አሜሪካ የመጣሽው?
ቅድስት:- መጀመሪያ ያው በደርግ ጊዜ ነው ከሀገር የወጣሁት:: ስዊድን ሀገር ሄጄ ከዛ በሗላ 10 years ቆየሁ:: እዛ እያለሁ; እኔ እንኳን አልሞላሁም ጓደኞቼ ዲቪ ሞልተው ላኩልኝና መልሱ ሲመጣ በእኔ አድራሻ መጣ::
ዘ-ሐበሻ:- ስዊድን ሆነሽ ማለት ነው?
ቅድስት:- አዎ!
ዘ-ሐበሻ:- ኢትዮጵያ ውስጥ ምንድን ነበር ሞያሽ? ምንድን ነበር የምትሰሪው? እዛም እንደዚሁ ታክሲ ትነጂ ነበር?
ቅድስት:- ሙያ የሚባል ነገር ያው just ሀይስኩል ከጨረስኩ በሗላ ባንክ ትንሽ ሰርቻለሁ::
ዘ-ሐበሻ:- ቅድም የጋዜጠኝነት ሙያው አለኝ; በራዲዮ ሰርቼ ነበር ስትይኝ ነበር?
ቅድስት:- ጋዜጠኝነት እንኳን ሳይሆን በራዲዮ ነው:: የራዲዮ ፕሮግራም እናዘጋጅ ነበር – በቤተ ክርስቲያን ውስጥ:: በኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን ፕሮግራም እያዘጋጀን ስዊድን ሀገር ለ5 አመታት ሰርቼበታለው::
ዘ-ሐበሻ:- አሜሪካ ከመጣሽ በሗላ የታክሲ ሹፌርነቱ ሥራ የመጀመሪያ ሥራሽ ነው?
ቅድስት:- አይደለም:: መጀመሪያ ኤርፖርት ውስጥ እሠራ ነበር:: ለ2 ወራት በኤርፖርት ሥራዬ ሴክዩሪቲ ሆኜ ነበር የሠራሁት:: ከዛ በሗላ ደግሞ የአፍሪካ ሕጻናት እና ሴቶች እንክብካቤ ቡድን ውስጥ ሰርቻለሁ:: በዚህ መሥሪያ ቤት ውስጥ በሰዎች “አብዩዝ” የተደረጉ ልጆችን እና ሴቶችን መርዳት ነበር ሥራችን:: ከ6 እስከ 8 ወር ለሚሆን ጊዜ ሰርቻለሁ::
ዘ-ሐበሻ:- በሀገር ቤትም; በስዊድን ቆይታሽም የታክሲ ሾፌር ካልነበርሽ እንዴት አሜሪካ መጥተሽ ይህንን የሥራ ክፍል ልትመርጪው ቻልሽ?
ቅድስት:- ባንክ ሰርቼ ነበር:: በዌልስ ፋርጎ (wells Fargo) ባንክ ውስጥ እየሰራሁ አብሬያቸው ቸርች የምሄዳቸው ልጆች እነርሱ ታክሲ ይነዳሉ:: እና ብዙ ጊዜ አንዳንድ ቦታ ለመሄድ አንድ ነገር ለማድረግ; በሕብረት የሆነ ነገር ለማድረግ እነርሱ ፍሪ (ጊዜ አላቸው) ናቸው:: እኔ ማስፈቀድ ምናምን ስላለብኝ አይመቸኝም:: ከዛም ለምን እኔም እንደነርሱ አልሰራም ብዬ አስብ ነበር:: ይህ ሀሳብ በአእምሮዬ ውስጥ እንዳለ አንድ ቀን መንገድ ላይ ስሄድ አንዲት ሶማሌ የባሏን ታክሲ ይዛ ነው መሰለኝ ስትነዳ አየሗትና እንዴት የሱማሌ ሴት ታክሲ የነዳች እኔን ያቅተኛል ብዬ ካልጀመርኩኝ ሞቼ እገኛለሁ አልኩ::
ዘ-ሐበሻ:- ከዛስ?
ቅድስት:- ከዛማ አብረውኝ ቸርች የሚሄዱትን የታክሲ ሹፌሮች አነጋግሬያቸው ታክሲ ሥራ ለመጀመር እንዴት እንደማደርግ ፕሮሰሱን ነገሩኝ እና ጀመርኩት::
ዘ-ሐበሻ:- አንዴ ኢንተርቪውን ላቋርጠው… ጉንፋን ይዞኛልና አፍንጫዬን ማጸዳዳት ይኖርብኛል::
ቅድስት:- ሶፍት ልስጥህ?
ዘ-ሐበሻ:- አይ ተይው!… ግን ጉንፋኔን እንዳላጋብብሽ?
ቅድስት:- I know!… (ሳቅ…)
ዘ-ሐበሻ:- (ከጥቂት ቆይታ በሗላ) እሺ አሁን መቀጠል እንችላለን::… እና ያቺ ሱማሌ ነች መነሻ የሆነችሽ ማለት ነዋ!
ቅድስት:- አዎ ሱማሌዋ ናት መጀመሪያ አእምሮዬ ውስጥ የነበረውን ሀሳብ በደንብ አጠናክሬ እዚህ ሥራ ውስጥ ያደረገችኝ ማለት ይቻላል:: በጣም ሞራል ሰጠችኝ:: የሶማሌ ሴት የነዳች እንዴት ያቅተኛል ብዬ ገባሁበት::
ዘ-ሐበሻ:- የታክሲ ሾፌር ከሆንሽ በሗላ ሥራውን እንዴት አገኘሽው?
ቅድስት:- በጣም easy (ቀላል) ሥራ ሆኖ ነው ያገኘሁት:: ስለእውነት ለመናገርም የሚከብድ ሥራ አይደለም:: ደግሞ ከእኔ በፊትም የሚገርምህ ሁለት ኢትዮጵያውያን ሴት የታክሲ ሾፌሮች ነበሩ:: ሆኖም ጥቂት ጊዜ ሰርተው ጥለው ወጡ ወዲያው::
ዘ-ሐበሻ:- አሁን ግን እዚህ የኤርፖርት ታክሲ ላይ አንቺ ብቻ ነሽ ሴት?
ቅድስት:- ያው ከሀበሻ እኔ ብቻ ነኝ:: ከነጮች ግን አንድ ሴት አለች:: almost 5 Years ይሆናል ብቸኛዋ ሴት የሀበሻ የታክሲ ሾፌር እኔ ነኝ ያለሁት::
ዘ-ሐበሻ:- ከብዙ የታክሲ ሾፌሮች እንደምሰማው ሥራውን የምትሰሪው ትንሽ ሀላፊነት ወስደሽ ነው:: ወንጀለኛ ሊያጋጥም ይችላል:: ሰካራምና በአደንዛዥ እጽ የደነዘዘ ሰው መጫን አለ:: አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰው ጭነሽ መንገድ የመጥፋት ነገር አለ:: እና አንቺ በዚህ ሥራ ውስጥ ያጋጠመሽ ነገር ምንድን ነው?
ቅድስት:- ጥሩ ጥያቄ ነው:: ወንጀለኛ እንኳን አጋጥሞኝ አያውቅም:: በጣም የሚያጋጥመኝ ያው መንገድ መጥፋት ነው:: በታክሲ ስራ ውስጥ መንገድ መጥፋት So normal ነው ይሄ:: እ.. እ… (እንደማሰብ አለችና) አንድ ጊዜ እንደውም ምን አጋጠመኝ መስለህ? አንዱን ደንበኛዬን ሆቴል እየወሰድኩት እያለ ሰውዬውም እኔም ሆቴሉ ያለበትን ቦታ አናውቀውም:: እየነዳሁ ሆቴሉ ጋር ስልክ ደውለን አድራሻውን ጠየቅኳቸው:: በየት በየት እንደምሄድ የነገሩኝ በትክክል አልገባኝም.. በቃ ሰውዬውን ይዤው ጠፋሁ:: ይገርምሀል ሰውዬው ምንም ነገር አይናገርም:: ዝም ብሎ ብቻ ነገሩን ይከታተላል:: ከተማውን ዞሬ ዞሬ እንደገና ሆቴሉ ጋር ስደውል የሚነግሩኝ መንገድ አይገባኝም:: ቢቸግረኝ ስልኩን ለተሳፋሪው ሰጠሁት:: ከዛ በሗላ በይ ከዚህ በኩል ተመለሺ ብሎኝ በተሳፋሪዬ እየተመራሁ ሆቴሉ አደረሰኩት:: ካሁን ካሁን ጮኸብኝ ብዬ ስፈራ እሱ እንደውም ቲፕ አድርጎ ሲከፍለኝ እኔ ‘ይሄን ያህል ገንዘብ አይመጣም; እንደውም ጊዜህን ሁሉ ስላጠፋሁብህ አላስከፍልህም’ ስለው እርሱ ጥሩ ሰው ስለነበር ከነቲፑ ሰጥቶኛል:: ሆኖም ግን ወንጀል ምናምንም አጋጥሞኝ አያውቅም::
ዘ-ሐበሻ:- አንቺ የታክሲ ስራ አስከፊ ጎን የምትይው ምንድን ነው?
ቅድስት:- መቼም በእኔ አስከፊ አድርጌ የምወስደው መንገድ መጥፋትን ነው:: ሰው ይዞ መጥፋት በጣም በጣም የሚያስፈራ ነው:: ሌላው ደግሞ ማታ መሥራት ትንሽ አደገኛ ሊሆን ይችላል:: አንዳንድ ጊዜ የሰከረ ሰው ሊያጋጥም ይችላል:: ማታ መሥራት ጥሩ አይደለም:: በተለይ ወደ ኖርዝ ሚኒያፖሊስ ማታ ከሆነ ሰው ይዞ መሄድ ብዙም ጥሩ አይደለም::
ዘ-ሐበሻ:- አንቺ ማታ ማታ አትነጂም ማለት ነው?
ቅድስት:- ማታ በጣም አላመሽም::
ዘ-ሐበሻ:- በሴትነትሽ ተሳፋሪ ሆኖ የሚተናኮልሽ የለም?
ቅድስት:- ማለት የኤርፖርት ታክሲ ስለሆነ የምሰራው ብዙም እንደዚህ ያለው ነገር አያጋጥምም:: ብዙ ጊዜ ከኤርፖርት ራሳቸውን ችለው; የኤርፖርት ትኬት ገዝተው የሚሄዱ ሰዎች ወደ ቤታቸው ወይም ወደ ሆቴል አንዳንዴም ወደ ሥራቸው ስለሆነ ብዙም እንደዚህ አይነት ሰዎች የሉም:: የሲቲ ታክሲ ስለማልሰራ ብዙም አልጨነቅም:: የሲቲ ታክሲ ግን ብዙ ጊዜ እንደዚህ ያለው ነገር ሊከሰት ይችላል::
ዘ-ሐበሻ:- በሚኒሶታ በሲቲ ታክሲ ውስጥ ሴት ሹፌር አለች እንዴ?
ቅድስት:- No! የለችም::
ዘ-ሐበሻ:- እዚህ ሚኒያፖሊስ-ሴንትፖል ኤርፖርት ታክሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ ስንት ኢትዮጵያውያን አሉ?
ቅድስት:- I think እስከ 150 የምንሆን ይመስለኛል::
ዘ-ሐበሻ:- እንግዲህ ከነዚህ ሁሉ መካከል አንዷ ብቸኛ ሴት አንቺ ነሽና ውሎሽ ከወንዶች ጋር ነው ማለት ይቻላል::
ቅድስት:- በሚገባ!..
ዘ-ሐበሻ:- ታዲያ ከወንዶች ጋር እንደመዋልሽ ወንዶችን ምን ታዘብሻቸው?
ቅድስት:- (ረዥም ሳቅ…) እኔ ከሕጻንነቴ ጀምሮ ወንዶችን ናቸው ጓደኞቼ:: ከሴቶች በላይ ከወንዶች ጋር ነው የምውለው:: አንዳንድ ጊዜ ሴት መሆኔንም የሚረሱበት አጋጣሚ አለ:: እነርሱ ብዙ ነገር ነው የሚያወሩት:: (ሳቅ…) በጣም ደስ ብሎኝ ነው ከወንዶች ጋር የምውለው:: ምንም ያየሁባቸው የታዘብኳቸው ነገር የለም:: ደግሞ እንደየአካባቢያችን እና እንደምንግባባቸው ሰዎች ነው የምንቆመው:: አብረውኝ የሚቆሙት (ተራ እስኪደርስ ለመጠበቅ ማለቷ ነው) ያሉት “ኩል” የሆኑ ናቸው::
ዘ-ሐበሻ:- ብዙ ጊዜ ወንዶች ስለምንድን ነው የሚያወሩት?
ቅድስት:- (ሳቅ..) እሱ ጠፍቶህ ነው እኔን የምታደርቀኝ? (ሳቅ…) ብዙ ጊዜ ሴት ያወራሉ:: ስለማህበራዊ ጉዳይ ያወራሉ:: ግን አብዛኛውን ጊዜ ስለሀገር ጉዳይ በማውራት ነው የሚያሳልፉት:: ስለሀይማኖት ጉዳይም ያወራሉ:: ግን ብዙ ትኩረት የሚሰጡት በሀገር ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ነው::
ዘ-ሐበሻ:- አላማሽ ምንድን ነው?
ቅድስት:- አላማዬ መማር ነው:: ከዚህ ቀደምም ተምሬ አቋርጬው ነው:: አሁን እሱን ከተማርኩ በሗላ ወደ ሀገሬ መግባትና ከሕጻናት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን መስራት እፈልጋለሁ:: ሕጻናትን በጣም ስለምወድ እነርሱን ማስተማር ደስ ይለኛል:: የወሰድኩትም ትምህርት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በዚህ ዙሪያ መሥራት እፈልጋለሁ::
ዘ-ሐበሻ:- ብዙ ኢትዮጵያውያን ሀገሬ መግባት እፈልጋለሁ ይላሉ ልክ እንዳንቺ; ግን ሲገቡ አይታዩም:: ለምን ይመስልሻል?
ቅድስት:- መቼም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እዚህ ይኑር እንጂ ልቡ ያለው ሀገር ቤት ነው:: ስለሀገሩ የማያስብና የማይናፍቅ የለም:: ያለመሙላት ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም ቢገባ ደስ ይለዋል:: እኔም ከወጣሁ ቆይቻለው:: ሰውን ወደ ሀገሩ እንዳይሄድ የሚያደርገው የገንዘብ ጉዳይ ነው:: እዛ ሄዶ ከዚህ ዝቅ ብሎ መኖር ስለማይፈልግና ኢትዮጵያ ሄጄ ከዚህ ያነሰ ልኖር? እያለ ስለሚፈራ; እሄዳለሁ እንዳለ ሳይሳካለት እዚሁ ይቀራል:: እኔም የምፎክረው ገንዘብ ቢኖረኝ ዛሬ እሄዳለሁ እያልኩ ነው::
ዘ-ሐበሻ:- ወደ ሥራሽ እንመለስና; ከመኪና ጋር አብሮ መዋል ብዙ አደጋ አለው:: ችግርም ያጋጥማል:: ለመሆኑ መንገድ ላይ እየሄድሽ ጎማ ቢፈነዳብሽ ራስሽ ነሽ የምትቀይሪው?
ቅድስት:-(ሳቅ..) ኸረ እኔ አልችልም:: ጎማ ቢፈነዳብኝም ቢበላሽብኝም መኪናዬን አስገፍቼም (ቶው አስደርጌ) ይዤ ወደ መካኒክ ነው የምሮጠው::
ዘ-ሐበሻ:- የሚኒሶታ አየር ትንሽ ይከብዳል:: በተለይ በክረምቱ ጊዜ ያለው በረዶ ጠንከር ያለ ነው:: አንቺ እንዴት ነው ይህንን አስቸጋሪ የክረምት ወራት ካለ አደጋ በረዶ ላይ በመንዳትና; በረዶ ላይ ቆሞ ወረፋ በመጠበቅ የምትሰሪው?
ቅድስት:- ይገርምሀል እኔ የሚኒሶታ ክረምት አይከብደኝም:: እንደውም ተስማምቶኝ ነው የምሰራው:: ለምን መስለህ ስዊድን ሀገር ከዚህ የባሰ በረዶ (ስኖው) አለ:: እናም ተስማምቶኝ ነው የምሰራው:: በደንብ ከለበስክ ከሚኒሶታ በጋ ክረምቱን እመርጣለሁ:: መንዳቱም ቢሆን ተጠንቅቀህ ከነዳህ መንሸራተትም አደጋም የለም:: ለታክሲ ስራ ገበያ የሚኖረው የክረምቱ ጊዜ እንደሆነም አትርሳ:: (ሳቅ) ስለዚህ ክረምቱን እወደዋለሁ::
ዘ-ሐበሻ:- ኢትዮጵያውያን ወንዶች በቤት ስራ ደካሞች ናችሁ እንባላለንና አንቺም ከእነርሱ ጋር እንደመዋልሽ ሙያውም ጠፍቶብሽ ይሆን?
ቅድስት:- (ሳቅ…) አልክድም:: እንደ ሴት መንጎዳጎድ አይሆንልኝም:: እንደውም እዚህ ያሉት በጣም ይፈታተኑኛል… (ሳቅ) ሙያሽን እንቅመሰው እስኪ አገልግል ፈትፍተሽ አምጪ ይሉኛል; ግን አይሆንልኝም:: እኔም ሴትነቱ ጠፍቶኛል መሰለኝ አላበላም ብዬ ቁጭ ብያለሁ:: አልሞከርኩትም እንጂ ሳይጠፋኝ አይቀርም:: ለራሴም ቀባ ቀባ አድርጌ ነው የምበላው: እንደወንዶቹ ቀለል ያሉ የፈረንጅ ምግብ; ሩዝ ወይም ፓስታ እያበሰልኩ ነው የምመገበው:: ወጣ ወጡን ነገር ሳልረሳው አልቀርም::
ዘ-ሐበሻ:- አግብተሻል?
ቅድስት:- አላገባሁም::
ዘ-ሐበሻ:- ለምን አላገባሽም ብዬ አልጠይቅሽም:: ግን ብዙ ጊዜ ከወንዶች ጋር ስለምትውይ ተጽእኖ አሳድሮብሽ ይሆን?
ቅድስት:- ኖ! ላሳደረብኝም:: Just የራሴ የሆነ ፐርሰናል ጉዳይ ያለማግባት ጉዳይ ነው::
ዘ-ሐበሻ:- እሺ እንተወው:: የሕይ ወት ፍልስፍናሽ ምንድን ነው?
ቅድስት:- እኔ በእግዚአብሄር የማምን ሰው ነኝ:: የቤተክርስቲያን ሰው ነኝ:: ያደግኩትም ከእግዚአብሄር ቃል ጋር ነው:: በሕይወቴ የሚያጋጥሙኝ ነገሮችና የሚፈጠሩት ሁኔታዎች ሁሉ በእግዚአብሄር ፈቃድ ብዬ ነው የማምነው:: ከዛ በተረፈ እኔ ማድረግ ያለብኝን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ ቀጥሎ ያለው በእግዚአብሔር የሚሆን ነው::
ዘ-ሐበሻ:- በመጨረሻም ምን ትያለሽ?
ቅድስት:- ማለት የምፈልገው? ብዙ ጊዜ ለሀበሾች ታክሲ ነው የምነዳው ስል አንዳንዱ ይደነግጣል; አንዳንዱ ይገረማል; አንዳንዱ አብረታቶኝ ያልፋል:: አብዛኛው ሴት ሆኜ የታክሲ ሥራ ላይ ሲያየኝ ‘ጉድ’ ይላል:: እኔ የምለው ግን በተለይ ሴቶች የታክሲ ሥራ አያስፈራም; ቀላል ነው; ኑና ሞክሩት ነው የምለው:: ብዙ ጊዜ የእኛ ሴቶች ፈሪዎች ነን:: መንገድ እንፈራለን… አይናፋር ነን… ግን ኑ የታክሲ ሥራ ቀላልና የሰነፍ ሥራ ነው የምለው:: ሴቶች መጥተው ቢሞክሩት ደስ ይለኛል::
ዘ-ሐበሻ:- እናመሰግናለን ቅድስት::
ቅድስት:- እኔም አመሰግናለሁ:: ®