ፍዳ በአገር ሞልቶ
መከራ በርትቶ፤
ማስተዋል ተስኖኝ
ምፍቻው ቁልፍ ጠፍቶኝ
ባዝኜ ባዝኜ፤ ዋትቼ ዋትቼ
እራሴን መርምሬ ውስጤን ተመልክቼ፤
፟፟፟፟፟
አልኩ፤
የት አለ ማስተሬ
የት ሄደ ዶክተሬ
ወዴት ነው ማወቄ
የት ጠፋ መርቀቄ፤
የት አለ ደብተሬ
የት ሄድዋል ብዕሬ?
ያየቸከቸኩት በጠባ በነጋ ይታደገኝ ብዬ ከመከራ አለንጋ፤ ፌደል የቆጠርኩት ፈተና ያለፍኩት ያነበብኩ የጻፍኩት ያየሁ ያዳመጥኩት
ያሁሉ እውቀቴ ምጡቅ ምርምሬ ወዴት ተበተነ ትቢያ ሆነ ዛሬ፤ ብዬ ብመራመር አውጥቼና አውርጄ
ይህ እውቀት የምለው ከንቱው ልምምዴ ከህሊና ይልቅ ገባሪው ለሆዴ
ከቶ አልጎበኘኝም አልረገጠም ደጄ።
ዋ!
ይኸው በዚህ ምክንያት ይኸው በዚህ ሳንካ
ለእኔ ብዬ አልሰማ ወንድሜ ሲነካ፤
አልገለጥ አለኝ ተሳነኝ ነግ በኔ
የምቀጥል እኔ ተርተኛ መሆኔ።
እንግድያስ፤
ልከልስ ከጀልኩኝ እንደገና አስክዋላ
ሀ ብሎ መጀመር ክጥንቱ ከህዋላ
ምን አልባት ምን አልባት አቅሌ አደብ ገዝቶ
ሀ! ብዬ ከመማር ዋ! ብዬ ላይ ረግቶ
ይፈታ ይሆናል ይህ ሁሉ መከራ
ሰው ሰው ያላረገኝ ያወጣኝ ከተራ።
ፒትስበርግ
በላቸው ገላሁን
ሚያዝያ 2016