የታፈነዉ ጠጣር እዉነት …1 ለህዝቦች አብሮነት! – ታዬ ደንድአ

#image_title

በኢትዮጵያ የአሁናዊ ሁኔታዉ አስቸጋሪነት በሚገባ ይታወቃል:: የፀጥታ.. የኢኮኖሚና የሌብነት ችግሩ አጥንት ድረስ ይሰማል:: ይህን ለመቋቋም ከብረት የጠነከረ አንድነት ይጠይቃል:: ግና እዉነቱ ታፍኖ ዉሸቱ አየር ይዟል:: አንዳንዱ ኦሮሞንና ኦሮሞነትን የችግሩ ባለቤት ሊያደርግ ሲሞክር ይታያል:: እጅግ አደገኛ የኦሮሞ ጥላቻ ተደጋግሞ ሲሰራጭ ይሰማል:: ይህ ውዥንብር ህዝቡን ላልተገባ አሉታዊ አመለካከት አጋልጧል:: ህዝቡ ያለወንጀሉ እንዲፈረጅ ተደርጏል:: በአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ምስኪኑ ኦሮሞ ሲታመም እንኳን ለመታከም ተቸግሯል:: የሴራ ፖለቲካዉ መተባበር የሚገባቸዉን አቃቅሯል:: አዝማሚያዉ በጣም አደገኛ መሆኑን ማዬት ይቻላል:: ከአሁኑ በእዉነት ሊጠራ ግድ ይላል! ይህን ማድረግ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ከግለሰብ ህዝብ ይበልጣል!

ለነገሩ ሁሉም የጉዳዩን አመጣጥ ያስታዉሳል:: ከዚህ ቀደም ፖለቲካ ቁማር እንደሆነ በግልፅ ተነግሮናል:: ከኦሮሞ አንፃር ቁማሩ ሁለት ጉዳዮችን ያካትታል:: አንደኛዉ ውስጣዊ አንድነቱን መናድ ላይ አተኩሯል:: ታላቁ ህዝብ በአከባቢ.. በሀይማኖትና በጎሳ ተከፋፍሎ እንዲያንስ ታስቦ ይሰራል:: ሰሞኑን በመስኪድ ፈረሳ ምክንያት የቱለማ ኦሮሞን ከሙስሊም ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት የተሰራዉ ተንኮል ይታወሳል:: በመዋቅር ስም በደቡብ ኦሮሚያ የተፈጠረዉ ውዥንብርም ወንድማማቾችን ነጣጥሎ ለማዳካም ከተሸረበዉ ሴራ ይመነጫል:: እንዲህ ዓይነት ተንኮል በዞን… በወረዳ… በቀበሌና በጎጥ ደረጃም ተተግብሯል:: ለማንኛዉም ሴራዉ በተደጋጋሚ ተሞክሮ እንደከሸፈ ቁማርተኛዉም ያዉቃል! ህዝቡ ከሴረኛዉ ቀድሟል!

ኦሮሞን በወንድሞቹ ዘንድ ለማስጠላት የተወጠነዉ ሁለተኛዉ ቁማር ግን አደገኛነቱ ያሳስባል:: በአንድ በኩል ከማንም በላይ በመከራ እሳት እየተቃጠለ ያለዉን ንፁህ ህዝብ የተለየ ተጠቃሚ ለማስመሰል የሀሰት ሪፖርት ይቀርባል:: የፎቶና የቪድዮ ድራማ ይሰራል:: በሌላ በኩል ደግሞ አሳፋሪ ተግባራት ተፈፅሞ በኦሮሞነት ካባ ይፎከራል:: ሀይማኖትና ብሔር በአደባባይ ይዘለፋል:: ያለሀፍረት “ፖለቲካ በማታለል የታጀበ ቁማር ነዉ” ይባላል:: ቁማሩን የሚጫወቱትም ለኦሮሞ ተብሎ እንደሆነ ይመሰላል:: ጫወታዉን ለማሳመር በቁማርተኛዉ ስብዕና ፈፅሞ የሌለዉ ኦሮሙማ በየመድረኩ ይደጋገማል:: በዘመድ አዝማድ ተደራጅቶ ሀገር ይጋጥና በተጎጂዉ ህዝብ ስም ለመሸፈን ይሞከራል:: በህዝቡ ዘላቂ ኪሳራ ሴረኛና ዘራፊ ጊዜያዊ ርካሽ ጥቅሙን ያካብታል:: ህዝቡ ግን በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን በረሃብ ሲሞት ሁሉም አይቷል:: የሌሎችን እርዳታ እንኳን እንዳያገኝ ለገፅታ ጥራት ተብሎ መከራዉ ይደበቃል:: በአጋጣሚ የህዝቡ መከራ ከተሰማ መልሶ ለመሸፈን ዶክመንተሪ ይሰራል:: አሁን በኦሮሚያ ስለህዝቡ ሞትና መፈናቀል መረጃ ማግኘት ከሰማይ ይርቃል! የክልሉ ህዝብ በኢህእዴግ ዘመን የነበረዉን የህብት ነፃነትን እንኳን አጥቷል:: በሌቦች ዉሳኔ ምርቱን ከገበያ ዋጋ በታች ለቁመርተኛዉ ደላሎች ለመሸጥ ይገደዳል:: ማህበራዊ ግልጋሎት ከናካቴዉ ተረስቷል:: በሀገር ደረጃ 3 % የነበረዉ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት እንኳን በኦሮሚያ 2% ብቻ እንደነበር ልብ ይሏል! በተለያዬ ቦታ ሰዉ በዘፈቀደ ይገደላል:: የከረዩ አባገዳ ከ14 ባለሟሎቹ ጋር ተረሽኖ ፍትህ ተነፍጏል:: ከኢትዮጵያ በውሳኔ የቆመዉ የስቃይ ምርመራ በኦሮሚያ ብቻ ቀርቷል:: ዛሬም እንደትላንቱ ዜጎችን በምርመራ ስም ማኮላሸት ቀጥሏል!

ነገር ግን የህዝብ ፍላጎትና የቁማርተኛ ጥቅም ለየቅል:: ሌብነት እንደሀገርም ከባድ ጉዳት ማስከተሉ በፓርላማ ሳይቀር ተደጋግሞ ተነስቷል:: ህገ-መንግስቱን በመቃረን መሬት የሌባና የደላላ መሆኑን ሰምተናል:: ኦሮሞ ደግሞ ከማንም በላይ የሌብነት ሰለባ ሆኗል:: አብዘኛዉ የተዘረፈዉ መሬት የኦሮሞ አርሶ አደር መሆኑ ይታወቃል:: ኦሮሞ ሀብት-ንብረቱ ብቻ ሳይሆን ማንነቱ ጭምር ተሰርቋል:: ዉሃ ሲጠይቁት ወተት የሚሰጥ የዋው ህዝብ ገፊና አፈናቃይ እንዲመስል ተደርጏል:: ከነባራዊዉ ትርክት አንፃር ይህ እዉነት ለማመን ሊቸግርም ይችላል:: ግና መራራ ሀቁን መግለፅ አሁን ግድ ይላል:: የቁማርተኛ ሌባ ወንጀል ፈፅሞ ኦሮሞን አይመለከትም:: በመሰረቱ ሌባ ሆድ እንጂ ብሔር .. ሀይማኖት ወይም ሰፈር የለዉም:: ትውልዱ የትም ቢሆን ሌባ ከሌባ አይለይም:: ኦሮሞነት… አማራነት ወይም ትግራዋይነት ክፋቱን አይለውጥም:: እዉነቱን ለምናገር ግን አቃፊዉ የኦሮሞ ህዝብ የወንድሞቹ ደስታና ሀዘን ተጋሪ እንጂ ለቁማርተኛ ሌቦች ወንጀል አባሪ አይደለም!

ለህዝቦች አንድነት ሲባል የታፈነዉ ጠጣር እዉነት ሊገለጥ ይገባል:: ቁማርተኛ ሌቦች በህዝብ ኪሳራ ለመጠቀም ኦሮሞን ልዩ ተጠቃሚ ለማስመሰል ብዙ ደክሟል:: በተጨባጭ ግን ምስኪኑ የኦሮሞ ህዝብ የቁማሩ ልዩ ሰለባ ሆኖ ይገኛል:: ከሁሉም ለከፋ መካራ መጋለጡ አንሶት በወንድሞቹ ዘንድ ባልተገባ መንገድ ይታያል:: ለህዝቦች ሰላም… ነፃነት.. እኩልነት.. ወንድማማችነትና የጋራ ዘላቂ ተጠቃሚነት ሲባል እዉነቱ ሊነገር ይገባል!

እዉነትና አንድነት ለሰላም! ሠላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለሰዉ ልጆች! መልካም ቀን!

ታዬ ደንድአ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ከ ፬ ኪሎ የተሰማው ጉድ/ከአማራ ህዝባዊ ግንባር መግለጫ ተሰጠ/የባለስልጣኑ አጃቢ ያደረገው የሴት ጠለፋ/(አሻራ ዜና

Next Story

በሁሉም አከባቢዎች ያሉ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞች ሃገር የቆመበትን ምሰሶ የሚቦረቡሩ ቅንቅኖች ናቸው!!!

Go toTop