በአገራችን ምድር ለተፈጠረውና ለሚፈጠረው ችግርና ወንጀል ዋናው ምክንያት ህገ-መንግስቱ ነው ወይ? የህገ-መንግስቱ መለወጥ የህብረተሰባችንን መጠነ-ሰፊ ችግር 

ሊፈታው ይችላል ወይ?  ለዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ የተሰጠ መልስ!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                        ግንቦት 29 2023

ዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ እየደጋገመ የሚያነሳውና የሚጽፈው ነገር አለ። ይኸውም የህገ-መንግስቱ መለወጥ አስፈላጊና፣ ያሉንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ልቦና፣ የባህልና የኢኮሎጂ ቀውሶችን በሙሉ እንደሚፈታ አድርጎ ነው። በዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ ዕምነት ዛሬ አገራችን ላለችበት ቀውስ ዋናውም መነሻና ምንጭ ህገ-መንግስቱ ነው። ይህንንም ሃሳብ ልዑል አስፋው-ወሰን አስራተም ይጋሩታል። በእነዚህ ሰዎችም ዕምነት ህገ-መንግስቱ´ ከተሻሻለ ችግሮቹ መፈታታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎችም ባህርይ አውቶማቲካሊ ሊለወጥ ይችላል።  ይህ ግምት ግን የእነሶክራተስንም ሆነ በኋላ ላይ የተነሱትን የእነ-ላይብኒዝን፣ ካንትንና የሄገልን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ የሚፃረር ነው። በህብረተሰብ ታሪክ ግንባታ ውስጥ ያልተረጋገጠ ነው። እነሶክራተስና ፕሌቶ፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ እነ ዴካም ሆነ የጀርመን አይዲያሊስቶች እንደሚያስተምሩን የሰው ልጅ ችግር ሁሉ የማሰብ ችግር ወይንም ትክክለኛ ዕውቀት አለመኖር ነው ይሉናል። በሌላ አነጋገር፣ በተሳሳተ ዕውቀት ጭንቅላቱ የተቀረጸ ሰው ነገሮችን ሁሉ በጭንቅላታቸው እያቆመ ነው የሚመለከተውና፣ ከዚያ በመነሳት የራሱን ግምት ሊሰጥ የሚችለው። ስለሆነም ከጥንቱ ግሪክ ጀምሮ እስከ ማዕከለኛው አውሮፓ ክፍለ-ዘመን ድረስ የነበሩት በአገዛዞች የተቀሰቀሱት፣ ሃይማኖትንና ጎሳን አሳበው የተደረጉት ጦርነቶች በሙሉ ከአገዛዞች አርቆ አስተሳሰብ ጉድለት ነው ይሉናል። ለዚህ ነው እነ ሶክራተስና ፕሌቶ ዲያሌክቲካዊ የጥያቄ ዘዴዎችን በመፍጠር የሰው ልጅ ራሱን እንዲጠይቅ በማድረግ መልስ እንዲፈልግ መንገዱን ለማሳየት የሞከሩት። ከዚህ በመነሳትና ፍልስፍናን መሰረት በማድረግ ነው ዕውቀት የተባለው፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ማቴማቲክስ፣ በተለይም እንደ ጄኦሜትሪ የመሳሰሉት በሙሉ በሰው የማሰብ  ኃይል ሊፈጠሩ የቻሉት። በጥንታዊ ግሪክ ዘመን፣ እነ ሶክራተስና ፕሌቶ በህይወት በነበሩበት ዘመን ይታገሉ የነበረው የህገ-መንግስት ለውጥ ይደረግ ብለው በመቀስቀስ ሳይሆን፣ ጠቅላላው ዕውቀት የሚባለውና የገዢ መደቦች ይመሩበት የነበረው የተሳሳተ ዕውቀት፣ በመሰረቱ በስግብግብነትና ስልጣን ላይ( Power and Gred) ለመውጣት የተመሰረተው በአዲስ መልክ መጻፍና ጭንቅላቱ በሶፊስታዊ አስተሳሰብ ያልተመረዘ አዲስ ትውልድ መፈጠር አለበት በማለት ነው ያስተምሩት የነበረው። በሌላ አነጋገር፣ ህገ-መንግስት እንኳ ቢለወጥ ህገ-መንግስቱን ያጸደቁትና ህገ-መንግስትን ተገን አድርገው ስልጣንን በመያዝ ስንትና ስንት ወንጀሎች የፈጸሙት ህገ-መንግስት ስለተለወጠ እነዚህ ሰዎች እንደ አዲስ ሰዎች ሆነው ይፈጠራሉ ሊፈተሩ አይችሉም። ማንም ሰው እንደሚያውቀው ጭንቅላታችን እንደ ሶፍትዌር ነው።  ጭንቅላት በአንድ አስተሳሰብ ከተቀረጸና የሰው ልጅ ዕድሜም የተወሰነ ዕድሜን ካሳለፈ በኋላ ቀድሞውኑ በተቀረጸበት አስተሳስቡ ነው የሚገፋበት። ይህንን አስተሳሰብ እነ ፍሮይድ ይጋሩታል። ስለሆነም በሳይንስ፣ በማቲማቲክስና በፍልስፍና ምሁሩ በላይብኒዝ ዕምነት መሰረት የህግ መለወጥ በመሰረቱ የሰዎችን ባህርይና ድርጊታቸውን በፍጹም ሊቀይረው አይችልም። በሌላ ወገን የምንጠቀምባቸውን ሶፍትዌሮች በየጊዜው ማሻሻል ይቻላል፤ ይሻሻሉም። የሚያስቸግረው ግን የሰውን ልጅ ጭንቅላት መቀየር ወይም ማሻሻል ነው፤ በቀላሉ አፕዴት ሊደረግ የሚችል አይደለም።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችን ምደር ያለው ትልቁ ችግርና የችግሮቹ ምንጮች አብዛኛዎቹ ምሁራን ጭንቅላታቸው ኢምፔሪሲዝም በመባል የሰውን ጭንቅላት በሚበታትንና በሚበርዝ ዕውቀት መሰል የተቀረጸ በመሆኑ ነው። በዚህ ዐይነቱ ቁንጽል አስተሳሰብ መንፈሱ የተቀረጸ ግለሰብ የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን ግንባታ አስቸጋሪነት በፍጹም ሊረዳ አይችልም። በታሪክ ውስጥ የተሰሩ መልካም ነገሮችን ሁሉ በመካድ አንድን አገር በጨቋኞችና በተጨቋኞች መሀከል ብቻ የሚገለጽና፣ መፍትሄውም ጨቋኝ የሚባለው መደብ ወይም ብሄረሰብ እንዳለ ሲወገድ ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ ነው። መንፈሳቸው በተሳሳተ ትረካ የተቀረጸ ሰዎች ከማንኛውም ዕውቀት ከሚባላው፣ ከፍልስፍና፣ ከተፈጥሮ ሳይንስና ከሶስይሎጂ፣ ህብረተሰብአዊ ትችትን ካዘሉ ሊትረተሮች የራቁ ስለሆነ አንድ ጊዜ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ያንኑ የተሳሳተ ትረካቸውን በማውራት ስልጣንን ላለማጣት የማይሰሩት ወንጀል የለም።

የግሪኩንም ሆነ በኋላ ላይ የተነሳውን በካፒታሊዝም ላይ የተመሰረተውን የምዕራቡን ዓለም የህብረተሰብ ታሪክ በደንብ የተከታተለ ሰው የሚረዳው ነገሮች በሙሉ ልክ ዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ በቀላሉ እንዳስቀመጠው የሚታዩ አይደሉም። ስንትና ስንት ነገሮች ከተፈጠሩም በኋላ ነው በተለይም የአውሮፓ ማህበረሰብ በጦርነት ዓለም ውስጥ እንዲዘፍቅ የተገደደው። ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እንደ አጋጣሚ በመሆን የአውሮፓ ማህበረሰብ ሶሶት ጭንቅላትን የሚያድሱ ሂደቶችን በማለፍ ነው ዛሬ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የበቃው። እነዚህም ሪናሳንስ፣ ሪፎርሜሽና ኢንላይተንሜንት በመባል የሚታወቁ ናቸው። እነጆን ሎኮ የህግን-የበላይነት ከጻፉና ካስተማሩም በኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሰላሳኛው ዓመት ጦርነት፣ ሌሎች አነስተኛ ጦርነቶች፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ተካሂደዋል። የታወቀው የጀርመን ፈላስፋና የድራማ ሰው ፍሪድሪሽ ሺለር እንደሚያስተምረን፣ የዲሞክራሲን ጽንሰ-ሃሳብ ከአሪስቶተለስ ጀምሮ ሰምንተናል። ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላም ባርቤሪያን ሆነን ቀርተናል ይላል። በሁለት ሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥም የሰው ልጅ ከተማዎችን ገንብቷል፤ የዕደ-ጥበብ ስራን አዳብሯል፣ ከንግድ ጋርም ተዋውቋል፤ ይህንና ግን ከአረመኔያዊ ባህርዩ በፍጹም አልተላቀቀም ይለናል። በእሱም ዕምነት የዚህ ሁሉ ችግር ዋናውም ምክንያት ልብና መንፈስ ስላልተገኛኑና፣ መንፈስም በጥሩ ዕውቀት ስላልተቀረጸ ነው ይላል።  ይህ ሁሉ የተፈጠረው እነ ጋሊሌዮ፣ እነ ዴካ፣ ኒውተንና ሌሎች ሳይንቲስቶች ተፈጥሮንና ኮስሞስን ተመራምረው ለሰው ልጅ የሚሆን ሳይንሳዊ ግኝቶችን ካፈለቁ በኋላ ነው። የኋላ ኋላ ላይ የአውሮፓ የገዢ መደቦች ህዝቦቻቸውን በጦርነት ካደቀቁ በኋላ ያላቸው አማራጭ የህግ-የበላይነትን በየአገሮቻቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ እኛ የሰለጠን ነን በማለት ሌሎች አገሮችን የቅኝ ግዛታቸው በማድረግ ህብረተሰብአዊ ሂደታቸውን ለማጨናገፍ ችለዋል። እስካሁንም ድረስ በውክልና ጦርነት ርስ-በርስ ያፋጁናል። የበላይነታቸውን ተገን በማድረግ በዕዳ በመተብተብ ከፍተኛ ቀውስ እንድንገባ አድርገውናል።

የዶ/ር ኪዳነ አለማየሁንና የሌሎችንም የህገ-መንግስት መለወጥ ቅስቀሳ የምንቀበል ከሆነ ኃይላችንን በሙሉ በዚህ ላይ ብቻ እንድናውል እንገደዳለን። በነገራችን ላይ ህገ-መንግስቱ ላይ ሰውን ግደል፣ አገር በታትን፣ ሀብት ዝረፍ፣ የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል አንዱን አበልጽግ፣ ሰፊውን ህዝብ ደግሞ ደሃ አድርገው የሚል አንቀጽ የለም፤  የአገርንም ሀብት ለውጭ ከበርቴዎች… ወዘተ ሽጥ የሚል አንቀጽ በፍጹም የለበትም። 70% በመቶ የሚሆነው ህገ-መንግስት ጉድለት የለበትም። አንቀጽ 39 የሚለው ነው የሰውን ትኩረት የሳበው። ይህ አንቀጽ ቢነሳ እንኳ ጭንቅላታቸው በተሳሳተ ትረካ የተገነባና ስንትና ስንት ወንጀሎች የሰሩ ሰዎች ስልጣን ላይ እስካሉ፣ ወይም የስልጣን ተካፋይ እስከሆኑ ድረስ የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች ይፈታሉ´ ማለት አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ በሚገባ የተዘጋጀና የተገለጸለት ኃይል እንደሌለ ይገባኛል። ይሁንና ግን እነ አቢይና ሺመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም ወያኔዎች ከውጭ ኃይል ጋር በማበርና ዕርዳታ በማግኘት የሚያደርሱት መጠነ-ሰፊ ጥቃትና ወንጀል የግዴታ መገታትና መንፈሳቸው ያልተበረዙ ሰዎች ስልጣንን መያዝ አለባቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችን ምድር እስካሁን ድረስ የሚሰጡ የትምህርት ዐይነቶች የቱን ያህል ለጥፋት እንደዳረጉን በማጥናት ለአዲሱ ትውልድ የሚስማማና ጭንቅላትን ብሩህ የሚያደርግ ትምህርት ማውጣት ያስፈልጋል። በዚያው ሂደት ውስጥ ህገ-መንግስቱንም ማሻሻልና፣ ህገ-መንግስቱን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚያደርጉ የሰለጠኑ ሰዎች ማፍራት ያስፈልጋል። በአዲስ መልክም የሚጻፈው ህገ-መንግስት ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ወንጀል የሰሩ ሰዎችን በምንም ዐይነት ከተጠያቂነት ሊያድናቸው አይችልም። አዲስ በሚጻፈውና በሚጸድቀው ህገ-መንግስትና ሌሎች ባሉ ህጎች አማካይነት በህዝባችንና በአገራችን ላይ ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው።  ባጭሩ የአገራችን ችግር ህገ-መንግስትን በመለወጥ የሚፈታ ሳይሆን፣ የጭንቅላት ችግር ነው። ሎጂክንና ዲያሌክቲክን ለመረዳት የማይችል፣ ለማዳመጥና ለመግባባት የማይፈልግ፣ ቶለራንስ የሚባልን ነገር የማያውቅ የህብረተስብ ኃይል እስካለ ድረስ ህገ-መንግስት ተለወጠ አልተለወጠ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ሰለሆነም በዚህ ዐይነቱ ፋይዳ-ቢስ ነገር ላይ ጊዜያችንን ባናባክን በጣም ጥሩ ነው። መልካም ግንዛቤ!!

 

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ሰበር ዜና! በተመስገን ጥሩነህ የተመራው ዘግናኝ ግፍ ተጋለጠ!! | የአማራ ድምጽ ዜና | The Voice of Amhara

Next Story

ሰበር ዜና!! ምስራቅ ጎጃም ደብረ ኤልያስ 118ቱን አጋድሙት!!| የአማራ ድምጽ ዜና

Go toTop