ኢትዮጵያውያን ሆይ! ብሔራዊ የመንፈስ ልእልናችን ጣረ ሞት ላይ እንዳለ ይህ አንዱ ምልክት ነው!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ከክርስቶስ ልደት በፊት የታሪክ ጠሐፊው ሄሮዱተስና ከክርስቶስ ልደት በኋላም ነቢዩ መሐመድ ኢትዮጵያን የፍትሀዊ ሰዎችና የፍትህ አገር ሲሉ መስክረውላት ነበር፡፡ ስናስተውል ያደግነውም በልጆቻቸው ሳይቀር ፈርደው ፍትሀዊ ፍርድ የሚሰጡ ሽማግሌዎችና “የተናገርኩት ተሚጠፋ የወለድኩት ይጥፋ” የሚሉ ወላጆችን ነበር፡፡

እንደዚህ አይነቱን መለኮታዊ የመንፈስ ልእልና እንደ ጃኖ ለብሳ የኖረች አገር በወሮበሎች እጅ ወደቀችና ኢፍትሐዊነት፣ አረመኔነት፣ ስርቆት፣ ቅጥፈትና ውሸት የኑሮ ዘይቤ የሆነባት ብቻ ሳይሆን በሰው ነፍስ ጫማ የሚገዛባት አገር ታቅፈን ቁጭ አልን፡፡

ለሁለት አመታት እስከ ከወራት በፊት ድረስ እነዚህ ተጫጉላ እንደ ወጡ አዲስ ሙሽሮች አንድ ላይ ሆነው ጫማ ከአውሮጳ የሚሸምቱት ጉዶች በወንበር ተጣልተው ሕዝብን እርስ በርሱ ሲያጫርሱት ነበር፡፡ እርስ በራሳቸውም ለመጠፋፋት እንደቆረጡም በአገር ውስጥም ሆነ በዉጭ ባሉ የሕዝብ መገናኛዎች ሁሉ ሲደነፉ ነበር፡፡ በወንበር ግጥሚያው ምክንያት ከሁለቱም ወገን ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደተጨፈጨፍ፣ ከኣስራ አምስት ሚሊዮን በላይ ስደተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የተጨፈጨፈው አንድ ሚሊዮን ሕዝብ በአማካኝ አምስት የቤተሰብ አባል ቢኖረው ወደ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ አሁንም ማቅ ለብሶ በሐዘን ተቆራምዶ፣ ከፊሉም ህሊናውን ስቶ፣ የተቀረውም በዚሁ ምክንያት በተለያዬ በሽታና ችጋር ተቆራምዶ ይገኛል፡፡ ስደተኛው ሕዝብ ኑሮውን መልሶ ማቋቋም ተስኖት መንገድ ላይ ተኝቷል፤ የሚቀምሰው አጥቶ በርሃብና ርሃብ ወለድ በሽታዎች በማለቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይኸንን የሚመልከተው የኢትዮጵያ ሕዝብም ህሊናው መግሎ “እህህ” እያለ ይኖራል፡

እነዚህ ጉዶች ለወንበራቸው ሲሉ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ በባሩድ አስጨፍጭፈው የአሞራና የአውሬ ሲሳይ አድርገው ሟቾቹ በገበሩት ግብር እየተላላሱ ታውሮጳ ጫማ ሲሸምቱ የጅብን ያህል እንኳ አይሰገጥጣቸውም፡፡ ያፈናቀሉት አስራ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ የሚለብሰው የሚቀምሰው አጥቶ በጠኔ ሲያልቅ እነሱ ዮሮ እንደ ገለባ እየነሰነሱ አውሮጳ የጫጉላ ሽርሽር ሲያደርጉ እንኳን የሰው የጅብም ደመነፍስ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ለወንበር በከፈቱት ጦርነት ልጁን፣ ወንድሙን፣ እህቱን፣ አባቱንና እናቱን ያጣው ሕዝብ እስካሁን ተሐዘን መቀመቅ ገብቶ መውጫ መንገዱ ጠፍቶ ሳለ እነሱ በዚሁ በሚሰቃየው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውሮጵላን ከንፈው ተአውሮጳ ሱቅ ውስጥ “ጫማህ ያምራል!” ሲባባሉ እንኳን እግዚአብሔር በአምሳሉ ፈጠረው የሚባለውን የሰውን የአህያን ታፋ ተነነፍሱ የሚገምጠውን ጅብን ያህልም ለሰው ነፍስ ደንታ ያላቸው አይመስሉም፡፡

እነዚህ የጫጉላ ሽርሽር ላይ ያሉ ጉዶች ገንዘቡን አርሰው ወይም ሸቀጥ ነግደው እንዳላገኙት የታወቀ ነው፡፡ ገንዘቡን ያገኙት በሰው ነፍስ ነግደው ነው፡፡ ገንዘቡን ያገኙት ያስገደሉት፣ያሰደዱትና ወህኒ የሚያሰቃዩት ሕዝብ ተገበረው ግብር ወይም በእርሱ ስም ከተረጠቡት እርጥባን  ዘርፈው ነው፡፡ እንኳን ሊዘርፍ ወድቆ የተገኝን ገንዘብ ለማንሳት የሚጠየፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰው ነፍስ ልብስ በሚገበዩ ጉዶች እየተገዛ ነው፡፡

እንደነዚህ ጉዶች ሁሉ ህሊናው በበራኪና ታጥቦ ወደ ጭራቅነት የተለወጠ ሰው “በፖለቲካ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም” የሚለውን መጤና እጅ እጅ የሚል አሰልቺ ድሪቶ ተረት እየተረተረ ምንም ላይመስለው ይችላል፡፡ እንደነሱ ይሉኝታ ያልፈጠረበት ይኸንን ተረት እንደ ኣቡጀዲ እየሸረከከ ባስፈጁት፣ ባፈናቅሉት፣ በሐዘን ወስጥ በዘፈቁትና የወደፊት እጣ ፈንታውን ባጨለሙት የኢትዮያ ሕዝብ ምራቁን ሊተፋ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ሁሉ ህሊና ቢስ አረመኔ የጠነባ ታሪኩን ተመሬት ላይ ጥሎ ነገ  በእርጅናም ሆን በበሽታ ተመቃብር ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! የሄሮድተስና የነቢዩ መሐመድ ዘመን ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የእኛ ዘመን ኢትዮጵያም የመንፈስ ልእልና እንደነዚህ ዓይነቶች ጉዶች ወንበር ተወጡቡት ዘመን ጀምሮ ጣረ ሞት ውስጥ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ የመንፈስ ልእልናችን ሙጣጭም ሳይቀር ሲው ብሎ ሳይጠፋ ቢያንስ ቢያንስ ትንሽ እንጥፍጣፊ የሰው ባህሪ ያላቸው ሰዎች ተብሔራዊ ወንበሮች ማስቀመጥ በአስቸኳይ ያስፈልጋል፡፡

በእንደነዚህ አይነት ጉዶች ሸኮና እንድትረገጥ የዳረጋትን ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይቅር ይበላት፡፡ አሜን፡፡

 

ግንቦት ሁለት  አስራ አምስት ..

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አማራን የማጥቃትና ሀገር የማፍረስ ወንጀል ይቅርታ የለውም፣ ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላልና

Next Story

“ሽንት አስጨራሽ ቀልድ እና አሽሙሮች…” | ፍራሽ አዳሽ | ተስፋሁን ከበደ | arts tv

Go toTop