የመጨረሻው ደወል! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

February 5, 2023

ኳ! ኳ! ኳ! ይላል፤
በማርያም ደጃፍ – በገብርኤል፤
በጎርጊስ ደጅ – በሩፋኤል፤
በጨርቆስ ደጃፍ – በአማኑኤል፤
በተክልዬ – በሚካኤል፤

ኳ! ኳ! ኳ! እያለ፤
የመጨረሻው ደወል ተደወለ !
አትንበርከኩ በቃ !
ቆማችሁ የጴጥሮስን ሞት ሙቱ እያለ::
ስደት አገር አሟጦ – ሃዘን ሰብዕናችሁን አጉብጦ ፤
ችጋር አጥንታችሁን ግጦ – ፍርሃት አንቀጥቅጦ ፤
ድህነት አፍጥጦ – በደል እግሩን አንፈራጦ ፤

አይግዛችሁ ይበቃል !
የአያት የቅድም አያቶቻችሁ ቃል፤
እንቢኝ ነው ደጉ – እንቢኝ ይበልጣል::

ይዩት_ ድፍረታችሁን !
ይረዱት_ ዕምነታችሁን
ይወቁት_ ኩራታችሁን !
አትንበርከኩ – ከንግዲህ ይበቃል፤
እንቢኝ በሉ – እምቢኝ ይሻላል::

አትፍረክረኩ_ ጽኑ በዕምነት !
የጀግኖች ልጆች ጀግኖች_ መሆናችሁን ይወቁት፤
ለአምባ ገነኖች አትንበርከኩ_ ቁሙ ለነፃነት፤
ቆማችሁ ተጎንጩ – ዳግም የጴጥሮስን ሞት ::

የልጆቻችን አንገት_ በጠራራ ፀሐይ ሲቀጭ ፤
የአያት የቅድም አያቶቻችን_ አጽም ሲንቀጫቀጭ ፤
ተንበርክከን ሳይሆን_ አጎንብሰን ፤
የጀግኖችን ሞት እንሙት_ በአንድነት ቆመን !
የአያት የቅድም አያቶቻችን ወጉ ፤
እምቢኝ ይሻላል_ አሻፈረኝ! ነው ደጉ ::

በኢትዮጵያ ምድር –
አብሮነትና ዕምነት ጸንቶ እንዲኖር፤
ሕዝብ በአንድነት ቆሞ – መሞት ይጀመር፤
ሞት በገዛ እጁ ይፈር ፤
ክርስቲያንና እስላሙ_ አብሮ ያብር ::

አትፍረክረኩ_ ጽኑ በዕምነት !
የጀግኖች ልጆች ጀግኖች_ መሆናችሁን ይወቁት፤
ለዘረኞች አትንበርከኩ_ ቁሙ ለነፃነት፤
ቆማችሁ ተጎንጩ – ዳግም የጴጥሮስን ሞት..
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም እንደ ጥንቱ፤
ማ’ተቡን ያጽና በደምና_ ባጥንቱ ::

እነሆ ኳ! ኳ! ኳ! ይላል፤
የመጨረሻው ደወል ተደውሏል፤
የበደል ፍጻሜው_ ይሆናል !!!

አንድ ቀን !
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ወቅታዊው የኢኦተቤክ ትንተናና ትንበያ በፍሰት ሰንጠረዥ

Next Story

መልዕክት ከታማኝ | Tamagne Beyene

Go toTop