ካለፈው ህዳር ወር 2014 ጀምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ሰለሞን ሶካ፤ ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተሾሙ። አቶ ሰለሞን የመሪነት ቦታውን የተረከቡት “ኢንሳ”ን ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የመሩትን ዶ/ር ሹመቴ ግዛውን በመተካት ነው።
አቶ ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነ መሾማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል። ከማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በሶፍት ዌር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ሰለሞን፤ በ“ኢንሳ” ከሶፍት ዌር መሐንዲስነት እስከ ቡድን መሪነት ባሉት ቦታዎች አገልግለዋል።
አዲሱ ተሿሚ በኮምፒውተር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከቻይና ኤሌክትሮኒክ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ነው። አቶ ሰለሞን ከዘጠኝ ወር በፊት የምክትል ዳይሬክተርነት የኃላፊነት ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ “ኢንሳ” ከመመለሳቸው በፊት፤ “ቴክ ማሂንድራ” በተባለ የህንድ የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎት እና አማካሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል።
በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ዕጩ የነበሩት አቶ ሰለሞን፤ የተወዳደሩበትን የደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንን ወክለው የፓርላማ አባል መሆን ችለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከተቀላቀሉ በኋላ የምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተሰይመዋል።
ኃላፊነታቸውን ለአቶ ሰለሞን ያስረከቡት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ከጥር 2012 ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በዋና ዳይሬክተርነት መርተውታል። ዶ/ር ሹመቴ ወደ ኢንሳ ከመምጣታቸው በፊት ለስምንት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።
ዶ/ር ሹመቴ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነውም አገልግለዋል። የቀድሞው የ “ኢንሳ” ዋና ዳይሬክተር የመንግስት ኃላፊነት ሹመት ከማግኘታቸው አስቀድሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ። ዶ/ር ሹመቴ ከ“ኢንሳ” ዋና ዳይሬክተርነታቸው የተነሱት “ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ቦታ በመታጨታቸው መሆኑን” ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን እና ኮምፒውተርን መሰረት ያደረጉ ቁልፍ መሰረት ልማቶች ደህንነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለበት ኢንሳ፤ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል፤ በተመረጡ ድንበር ዘለል የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይገኝበታል። የሳይበር ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር ሂደት ለፖሊስ እና ሌሎች በህግ ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ትብብር የማድረግ እና ድጋፍ መስጠትም ከተቋሙ ተግባራት መካከል የሚጠቀስ ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ለማቋቋም በ2006 ዓ.ም የወጣው አዋጅ፤ ተቋሙ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ አንድ ዋና ዳይሬክተር እና እንደ አስፈላጊነቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እንደሚኖሩት ይደነግጋል። አቶ ሰለሞን ሶካ በምክትል ዳይሬክተርነት ከተሾሙ ካለፈው ህዳር ወዲህ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለተቋሙ ሶስት ተጨማሪ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ሾመዋል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ የ“ኢንሳ” ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ሆነው የተሾሙት አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ እና አቶ ዳንኤል ጉታ ሲሆኑ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ደግሞ አስቴር ዳዊት በተመሳሳይ የኃላፊነት ሹመት አግኝተዋል። በቀድሞው የሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት ወ/ሮ አስቴር፤ ወደ “ኢንሳ” ከመምጣታቸው በፊት በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)