በፖሊስ ይግባኝ የተጠየቀባቸው ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ከእስር ሳይለቀቁ ቀሩ

June 7, 2022
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ዋስትና በተፈቀደላቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ላይ ይግባኝ ጠየቀ። የይግባኝ አቤቱታው የቀረበለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት “ዳኛ የለም” በመባሉ ጉዳዩ ለነገ ረቡዕ ሰኔ 1፤ 2014 ተቀጥሯል።
መርማሪ ፖሊስ ይግባኝ የጠየቀው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ነው። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለጋዜጠኞቹ ዋስትናውን የሰጠው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 30 ረፋድ በነበረው የችሎት ውሎ ነው።
ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ከሰጠ በኋላ የሶስቱም ጋዜጠኞች ቤተሰቦች የተጠየቁትን የዋስትና ገንዘብ መክፈላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የፍርድ ቤት መፈቻ ትዕዛዙን ይዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኙት የሰለሞን ሹምዬ ቤተሰቦች “ይግባኝ ጠይቀናል አንፈታውም” መባላቸውን እህቱ ትግስት ሹምዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩት ሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዛሬ ከሰዓት በፖሊስ ታጅበው በፍርድ ቤት ቅጽር ግቢ ቢገኙም ችሎት ፊት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሰራተኞች “የይግባኝ ጉዳይ የሚመለከት ዳኛ የለም” በማለታቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ታስረው ወደሚገኙበት ፖሊስ ጣቢያ ተመልሰዋል።
(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪ ከሃያ አምስት ቢሊዮን ብር ወደ መቶ ቢሊዮን ብር ተመነደገ! – ሚሊዮን ዘአማኑኤል 

Next Story

የእምቧይ ካብ – አገሬ አዲስ

Go toTop