ቤተሰቦቻቸው እንደገለፁት ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ የልብ ሕመም የነበረባቸው ሲሆን ለዚህም በአገር ውስጥና በውጪ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል። ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የነበሩት ፍሰሐ ሕይወታቸው ያለፈው አርብ ሚያዚያ 28/2014 ዓ. ም. እኩለ ሌሊት አካባቢ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እሁድ ሚያዚያ 30/2014 ዓ. ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጿል።
ከእስር ከወጡ በኋላ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ስላለፉባቸው ሁኔታዎች የሚተርክ “አብዮቱና ትዝታዬ” የሚል መጽሐፍ ያበረከቱ ሲሆን፣ በዚህም “ደርግ በወሰዳቸው በጎ ዕርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ በማወቅ፣ በድፍረት፣ ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለው ነበር።
ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ከመጀመሪያው መጽሐፋቸው በተጨማሪ ሁለተኛ መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ ነበሩ።
ትግራይ አድዋ ውስጥ የተወለዱት ሌፍተናንት ኮሎኔል ፍሰሐ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአደዋ ንግሥተ ሳባ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃን አዲግራት ውስጥ በሚገኘው አግአዚ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ ወደ ሐረር ጦር ትምህርት ቤት ገብተው ከሰለጠኑ በኋላ በክብር ዘበኛ ውስጥ ገብተው በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተመድበው አገልግለዋል።
ወደ አሜሪካ በመሄድ ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጠና ወስደዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ተከታትለዋል።
ንጉሡን ከሥልጣን ያስወገደው ሕዝባዊ አብዮት ሲፈነዳና በደርግ አማካይነት ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ሲመሠረት ከጦር ኃይሉ ተወጣጥተው የአመራርነት ቦታውን ከያዙት የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ነበሩ።
ከዓመታት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሲመሠረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪም ምክትል በመሆን የአገሪቱ ሁለተኛ ሰው ለመሆን በቅተው ነበር።
ከአማፂያን ጋር ለ17 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየው አስተዳደራቸው እየተዳከመ መጥቶ ፕሬዝዳንቱ አገር ለቀው ከተሰደዱ በሳምንታት ውስጥ የአማጺያኑ ስብስብ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የኢሕዲሪ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ።
ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐን ጨምሮ በአገር ውስጥ የተገኙት የቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣናት በአገሪቱ ውስጥ በተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተከሰው ለዓመታት በተካሄደ የፍርድ ሂደት እስር ተፈርዶባቸዋል።
ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታም ለ20 ዓመታት በእስር ካሳለፉ በኋላ ከ10 ዓመት በፊት በይቅርታ መለቀቃቸው ይታወሳል።