በአማራ ክልል የተመዘገበውን የ12ኛ ክፍል ውጤት ትንተናና አስተራረም በመቃዎም ነገ በመላ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱን የአማራ ተማሪዎች ማህበር አስታወቀ። የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ደግሞ ሊደረግ ለታሰበው ሰልፍ እውቅና እንደማይሰጠው አመልክቷል፡፡
የ2013 ዓ ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትና ትንተና ችግር አለበት በሚል በወላጆች፣ በተማሪዎች፣ በመምህራንና በተቋማት ከፍተኛ ቅሬታና ውዝግብ አስነስቷል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጉዳዩን የሚያጣራ 11 አባላት ያሉት አጣሪ ቡድን ወደ ትምህርት ሚኒስቴር የላከ ሲሆን የተማሪዎች ቅሬታ የመጨረሻ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ጊዜ እንዲራዘም ደብዳቤ መፃፉ ተገልጧል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ተቋማት ፎረምም ፈተናው እንደገና እንዲታረም፣ አሊያም ተማሪዎች ሌላ ፈተና እንዲፈተኑ በሚል የተማሪዎችን የፈተና ውጤት ቅሬታ ተጋርቷል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ የዞን ትምህርት መምሪያዎችም እንዲሁ በፈተናው ውጤትና አስተራረም ዙሪያ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
የአማራ ተማሪዎች ማህበር በበኩሉ “የተዛባና የተሳሳተ” ያለውን የተማሪዎች ውጤት እንደገና እንዲስተካከል አለዚያም እንዲመረመር የሚያሳስብ ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በአማራ ክልል በሁሉም ከተሞች እንደሚያካሂድ አመልክቷል፡፡
የማህበሩ ፕረዚደንት እሸቱ ጌትነት ለዶይቼ ቬሌ የሰልፉን ዓላማ ተናግረዋል፣
“የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና ይዘትና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤትን በተመለከተ ነው፣ የፈተና ይዘቱ የክልሉን ነባራዊ አውድና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ማዕከል ያላደረገ፣ አገሪቱ የቆየችበትን ያላገናዘበ ፈተና ወጥቷል ፣ ያ ፈተና ትክክል አይደለም አይመጥንም የሚል አንዱ ነው” ብሏል፡፡
እንደ ፕረዚደንቱ በተለይ በምስራቅ አማራ የነበሩ ተማሪዎች በጦርነት ውስጥ የቆዩ፣ በስነ ልቦና የተጎዱና ለፈተና በቂ ጊዜ ያልተሰጣቸው ነበሩ፣ ይህን ለዓለም ለማሳወቅ ሰልፉ ተዘጋጅቷል ነው ያለው፡፡
ሌለው የሰልፉ ዓላማ “የፈተና እርማቱ ችግር ያለበት መሆኑ በትክክል እየታየ፣ ከ100 ነጥብ በታች አምጥታችኋል የተባሉ ጎበዝ ተማሪዎች ውጤታቸው ሲመረመር ከ600 በላይ ሆኖ በመገኘቱና ተማሪዎች ባስመዘገቡት ውጤት ልክ አልተመዘኑም የሚል ግንዛቤ በመያዙ ሌላኛው የሰልፉ ዓላማ ይህን መቃወም ነው ” ሲል ነው እሸቱ ለዶይቼ ቬለ የተናገረው፡፡ የሁሉም ክልል ተማሪዎችና ወጣቶችም ቅሬታቸውን እንዲጋሩላቸው የተማሪዎች ማህበር ጠይቋል፡፡
ሰልፉ ነገ እሁድ እንደሚካሄድ ለሚመለከታቸው ሁሉ ማሳወቃቸውንም የተማሪዎች ፕረዚደንት አመልክቷል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አንዳመለከተው ደግሞ ነገ መጋቢት 18/2014 ዓ/ም ለሚደረገው ሰልፍ እውቅና እንደማይሰጥ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በመግለጫው መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ባለበት ወቅት የአማራ ተማሪዎች ማህበር ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ነቅፎታል፡፡
“የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ምክክርና ውይየት ካደረገ በኋላ ከአገራዊ፣ ክልላዊና ከበሕር ዳር ከተማ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳትና ከደህንነት ሥጋት አኳያ ተመዝኖ ሰልፉ በከተማችን መካሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ እውቅና የሰጠው ሰልፍ የለም” ብሏል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ አክሎም ከእውቅና ውጪ የሚደረግ ማነኛውም ሰልፍ ላይ ለሚደርስ ጥፋት ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት እንደማይወስድ አስጠንቅቋል፡፡
የባህርዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን እንደ,ዘገበው የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ጉዳይ ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ላይም ተነስቶ ሰፊ መከራከሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
የአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ በእርማት ወቅት የተፈጠረ ስህተት የለም፣ በፈተና ውጤት ትንተና ወቅት የታዩ የተወሰኑ ችግሮች ግን እንደነበሩና የ20ሺህ ተማሪዎችን ቅሬታ በመቀበል፣ የ559 ተማሪዎች ውጤት መስተካከል መቻሉን ገልፀው ነበር፡፡
DW Amharic
————————————–
ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
ሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የ12ኛ ውጤትን ተንትኖ የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር ውጤቶቹን ተንትኖ ፍትሐዊ የኾነ የመቁረጫ ነጥብ መወሰንና ግልጸኝነት የመፍጠር ኀላፊነት እንዳለበት ቢታወቅም በተለያዩ ምክንያቶች የአማራ ክልል ተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ በመሆኑ ከፍተኛ ድንጋጢ እና ይህንም ተከትሎ ቁጣ ፈጥሯል ፡፡ ቁጣውም ሆነ ድንጋጤው ተገቢ ምክንያት አለው ።
ይሁን እንጂ ውጤቱ ከተገለጸ በኋላ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባደረገው ግምገማ የክልሉ ተማሪዎች ከሀገራዊ አማካኝ ውጤት ዝቅ ያለ መኾኑን ያረጋገጠ ሲሆን ውጤቱ እንዲስተካከል ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባበት ወቅት እንዲራዘም እና ጉዳዩ እንዲጣራ ለትምህርት ሚኒስቴር በጽሑፍ ጥያቄ አቅርቧል ።
ከትምህርት ቢሮው በተጨማሪ በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረምና የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እንዲሁም ደግሞ ከ15/07/2014 እሰከ 16/07/2014 ዓ.ም ድረስ በተካሄደው የክልሉ ምክርቤት ጥያቄው ተነስቶ ሰፊ ውይይት ያደረገበት ሲሆን ችግሩ በአጭር ጊዜ ተፈቶ ተማሪዎች መፍትሔ እንዲያገኙ አቅጣጫ አስቀምጧል ።
በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ሂደቱን የሚያጣራ አስራ አንድ አባል ያለው ግብረ ኃይል ወደ ትምህርት ሚኒስትር የተላከ ሲሆን የተላከው ቡድን የተሰጠውን ተልዕኮ አጠናቆ አልተመለሰም።
መንግስት በጀመረው አካሄድ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ባለበት ሰዓት በአማራ ተማሪዎች ህብረት የሚመራ በ18/07/2014 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ ተቋማት ደብዳቤና ማስታወቂ መለጠፉን ተመልክተናል ።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር ከአካሄደ በኃላ ከተለያዩ ሀገራዊ እና ክልላዊ እንዲሁም ከከተማችን ነባራዊ ሆኔታ በመነሳት በተለይም ደግሞ ከደህንነት ሰጋት አኳያ ተመዝኖ ሰልፎ በከተማችን ለጊዜው መካሄዱን ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ ዕውቅና የሰጠው ስልፍ የለም ።
ሰለሆነም በ18/07/2014 ዓ.ም በዕለት እሁድ ሰለተጠራው ሰልፍ የሰጠው ምንም ዓይነት ዕውቅና አለመኖሩን በድጋሚ እየገለፀን ከከተማ አስተዳደሩ ዕውቅና ወጭ የሚደረግ ማንኛውም ሰልፍ ላይ ለሚደረስ ጥፋት ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት አይወስድም ። በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች ፣ተማሪዎችና መምህራን ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር ራሳችሁን በማቀብ የክልሉ መንግስት የጀመረውን ትግል የመጨረሻ ውጤት በትግስት እንድትጠብቁ በጥብቅ እናሳስባለን ።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት