1፤ ፌደራል መንግሥቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነትን ወደ ከተማዋ አስተዳደር ሊያዛውር እንደሆነ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱን ለመረከብ ጥናቶችን አጠናቆ ለመንግሥት እንዳቀረበ የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ቀንዓ ያዴታ ትናንት ለከተማዋ ምክር ቤት ጉባዔ ተናግረዋል። በተለያዩ አዋጆች ላይ የተደረጉ ጥናቶች የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለከተማዋ አስተዳደር መሆን እንዳለበት የሚያመለክቱ እንደሆኑ ቀንዓ አብራርተዋል። ከንቲባ አዳነች ከቀንዓ ማብራሪያ ቀደም ብለው፣ የፖሊስ ኮሚሽኑ ተጠሪነትና አደረጃጀት እንደገና መስተካከል እንዳለበት ለምክር ቤቱ ተናግረው ነበር። የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ሙሉ በሙሉ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠው በ1997 ዓ.ም ነበር።
2፤ በትግራዩ ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጅ የሆኑ የትግራይ ተወላጆችን የወከለ አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሰው ልጅ መብቶች ኮሚሽን ዘንድ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ክስ እንደመሠረተ ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። ለኮሚሽኑ የክስ አቤቱታ ያስገባው “ሌጋል አክሽን ወርልድ ዋይድ” የተሰኘ በውጭ ሀገር የሚገኝ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፣ አቤቱታው ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ሲቪሎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያቆም፣ ወደ ትግራይ ያልተገደበ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ እንዲፈቅድ እና የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በተለይም የትግራይ ተወላጆችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብር ትዕዛዝ እንዲሰጥ ነው። ኮሚሽኑ በትግራይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ መርማሪ አካል ባለፈው ሐምሌ ያቋቋመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን መርማሪ ኮሚሽኑን እንደማይቀበል ማሳወቁ ይታወሳል።
3፤ መኢአድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ የማስቆም ሕገ መንግሥሥታዊ ግዴታውን እንዳልተወጣ በመግለጽ ለምክር ቤቱ ደብዳቤ ማስገባቱን ዶቸቨለ ዘግቧል። ምክር ቤቱ መንግሥትን መቆጣጠር እና መንግሥት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት እንዲያስጠብቅ የማስገደድ ሥልጣኑን እንዳልተወጣ መኢአድ በደብዳቤው ገልጧል። መኢአድ ጨምሮም፣ ምክር ቤቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ እንዲያስቆም፣ የጸጥታ አካላትን የሚያዘውን የመንግሥት አካል አስቀርቦ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ባስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ፣ አስፈጻሚው አካል ድርጊቱን እንዲያስቆም እንዲያስገድድ ወይም ሀገሪቱን ከመበታተን ለማዳን አዋጅ እስከማወጅ ድረስ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል። ፓርቲው ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በጻፈው ሌላ ደብዳቤ፣ የዜጎችን እና የሀገሪቱን ደኅንነት የሚጠበቅበትን መንገድ እንዲከተሉ አሳስቧል።
4፤ ኦፌኮ በሳዑዲ ዓረቢያ በማጎሪያ ማዕከላት በሥቅየት አያያዝ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ሕይወት ለማትረፍ አስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ኦፌኮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ እና ሌሌች ሀገራት ለሥቅየት የሚዳረጉት፣ የፖለቲካ አመራሩ የተዛባ በመሆኑ፣ መንግሥት ውጤታማ የልማት ፖሊሲዎች ስለሌሉትና የልማት ፖሊሲ አተገባበሩ የጥቂት ግለሰቦችን ጥቅም ያማከለ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሷል። ከሳምንት በፊት የመንግሥት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ወደ ሪያድ አቅንቶ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር ችግሩን ለመፍታት የተነጋገረ ሲሆን፣ ውይይቱ ምን ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣ ግን አልተገለጸም።
5፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም 35.5 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች ወደ መቀሌ በአውሮፕላን እንደሚያጓጉዝ በድረገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ድርጅቱ ዕቅዱ በቀን 10 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ለማጓጓዝ ሲሆን፣ ዛሬ 10 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶችን አጓጉዣለሁ ብሏል።
6፤ ሱዳናዊያን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሱዳንን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘውን ዋናውን እውራ ጎዳና ዘግተው እንደዋሉ ሮይተርስ ዘግቧል። በአውራ ጎዳናው ላይ ግመሎችን እና የቀንድ ከብቶችን የጫኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንደቆሙ እና በጥር ወር መገባደጃ ግድም ብቻ 1 ሺህ 500 ያህል የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ግብጽ ከማለፍ እንደታገዱ ዘገባው አመልክቷል። ወታደራዊው መንግሥት በኤሌክትሪክ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ ተቃዋሚዎች አውራ ጎዳናውን መዝጋት የጀመሩት ባለፈው ወር ሲሆን፣ በመስመሩ መዘጋት ሳቢያ ግመሎችን እና የቀንድ ከብቶችን የሚሸጡ ሱዳናዊያን ነጋዴዎች ለኪሳራ እንደተዳረጉ ገልጸዋል። የቤጃ ጎሳ ተቃዋሚዎች ደሞ ወደ ፖርት ሱዳን የሚወስደውን መስመር ከዘጉ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል።
7፤ አሜሪካ የሱማሊያን የዲሞክራሲ ሂደት ያስተጓጉላሉ ባለቻቸው የቀድሞ እና የአሁን የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሌሎች ግለሰቦች ላይ የቪዛ እገዳ እንደጣለች የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። አሜሪካ የጣለችው የቪዛ ማዕቀብ በተለይ የምርጫ ማጭበርበር በሚፈጽሙ፣ ጋዜጠኞችን እና ተቃዋሚዎችን በሚያስሩ እና በሚያንገላቱ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ ባለሥልጣናት እና ግለሰቦች ላይ ነው። ብሊንከን የቪዛ እገዳ መጣላቸውን ይፋ ባደረጉበት ዕለት፣ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፎርማጆ ሥልጣን ዘመን ከተጠናቀቀ ዓመት የደፈነበት ዕለት መሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]