የፈተና መሰረቅ ከግለሰብ ይልቅ ተቋማዊ እየሆነ መምጣቱ እና በአጠቃላይ የደረሰብን የሞራል ክስረት ከፍተኛ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ፡፡
ሚንስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ንግግር ላይ፤ የእኔ ክልል ተማሪዎች ማለፍ አለባቸው በሚል በተቋም ደረጃ የፈተና ወረቀቶችን በመስረቅና መልስ በመስጠት ጭምር ተባባሪ የሆኑ አመራሮች መኖራቸው በማንሳት፣ የትምህርት ሥርዓቱ ጥራት ተዓማኒነት ከፍተኛ ጥያቄ ዉስጥ መግባቱን አስረድተዋል፡፡
አንድ ሰዉ በዚህ የትምህርት ስርዓት ዉስጥ አልፎ ድግሪ ሲያገኝ፣ ድግሪዉ ለማህበረሰብ መስጠት ያለበትን መልዕክት ይሰጣል ወይ፣ ትርጉም ያለዉ መመዘኛስ ይኖረዉ ይሆን መባል አለበት። ይህንን ማድረግ የሚቻለዉ ግን ሥርዓቱን ተዓማኒነቱ የተጠበቀ ከሆነ ብቻ ነዉ ብለዋል፡፡
‘’ግማሹ ለፍቶ ጥሮ ዉጤት እየያዘ፣ ሌላዉ ደግሞ ከድግሪ ፋብሪካዎች ድግሪ እየተቀበለ የሚያልፍበት ሁኔታ ካለ ችግሩ የተወሰኑ ሰዎች ማለፍ ሳይሆን፣ ችግሩ የትምህርት ጥራቱ ላይ ነዉ’’ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ፈተና የሰዎችን ክህሎት እና ታታሪነት መለኪያ መሆኑ ቀርቶ፣ ተሰርቆ ና መልስ ተሰጥቶ የሚመጣ ዉጤት ምዘና አያሟላም፣ ተዓማኒነትም አይኖረዉም ሲሉም ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል፡፡
አክለውም “የትምህርት ተቋማት ምዘና ተደርጎባቸዉ ሰርተፊኬት ይስጡ በሚባልበት ሁኔታ በተለይ ለግል ትምህርት ቤቶች የሥራ ሰርተፊኬት የሚሰጠዉ በችሎታቸዉ ሳይሆን በጉቦ ከሆነ ሲስተሙ ፈርሷል። ይህንንም ሁላችንም ነው የምናዉቀዉ። ነገርግን ፊትለፊት ስለማንነጋገርበትም ሥር የሰደደ መፍትሄ ልንፈልግለት ያልቻልነዉ ጉዳይ ነዉ“ ብለዋል፡፡
የትምህርት ሥርዓቱን ተዓማኒነት ጥያቄ ዉስጥ የሚከት አካሄድ በጣም ተንሰራፍቷል ያሉት ሚንስትሩ የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል እንደዚህ ያሉ አሰራሮችን ማስቆምና የሥርዓቱን ተዓማኒነት ችግር ዉስጥ የሚከቱ ጉዳዮችን ከሥር መሰረታቸዉ መፍታት አለብን ሲሉ ለሰው ሃብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ማለዳ