*በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣው ጦርነት ምክንያት አፋር ክልል ውስጥ የተፈናቃይ ተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ባለሥልጣናት ዐስታወቁ። ጦርነቱ ተስፋፍቶና ተባብሶ በቀጠለባቸው ባለፉት ሦስት ሳምንታት በአፋር የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 300 ሺህ ማሻቀቡንም ተናግረዋል።
*የኢትዮጵያ አየር ክልል ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዛሬ ዐስታወቀ። የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያን ጨምሮ በኢትዮጵያ አየር ክልል የሚደረጉ በረራዎች አስተማማኝ እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በድረ ገጹ ገልጧል።
ዜናው በዝርዝር
*በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የተሰየመው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)እና ተባባሪዎቹ ጤና ሚኒስቴር «ወረራ በፈፀሙባቸው» ባላቸው «አካባቢዎች ከ1 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት» በመዝረፍ ማውደማቸውን ዛሬ ዐስታወቀ። የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሕወሓት እና ግብረአበሮቹ የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸሙን በመግለጥ የሕክምና ቁሳቁሶች መውደማቸውን ብሎም በርካታ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጧል። ሕወሓት በኃይል በያዛቸው አካባቢዎች በተለይም «እናቶች የሚወልዱባቸውን፣ ሕፃናት የሚታከሙባቸውን የጤና ተቋማት» ማውደሙንም ሚንስትሯ አክለው መናገራቸው ተገልጧል። በሕወሓት ከተያዙ «የአማራና የአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በተጨማሪ የፀጥታ ችግር ባለባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች»ም የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ሚንስትሯ መጠቆማቸውን የሀገር ውስጥ የመገናኛ አውታሮች ዘግበዋል። ሕወሓት እና ተባባሪዎቹ አሁንም ድረስ በኃይል በያዟቸው አካባቢዎች በጤና እና በሌሎች ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ የደረሰው ጉዳት በዝርዝር ዐይታወቅም። ሆኖም በኃይል በተያዙ አካባቢዎቹ ነዋሪዎች በመድኃኒት እና በምግብ እጦት ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን የሚወጡ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
*በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣው ጦርነት ምክንያት አፋር ክልል ውስጥ የተፈናቃይ ተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ባለሥልጣናት ዐስታወቁ። ጦርነቱ ተስፋፍቶና ተባብሶ በቀጠለባቸው ባለፉት ሦስት ሳምንታት በአፋር የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 300 ሺህ ማሻቀቡንም ተናግረዋል። የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ይህንኑ በተለይም ለዶይቼ ቬለ ገልጠዋል።
«ጦርነት ቀጠና ውስጥ የዞን 2፦ በርሃሌ አለ፤ እንዲሁም ከዞን 2 ጀምሮ ያለው፦ እዋ፤ አውራ እንዲሁም ጭፍራ፤ ዞን አንድ ደግሞ ሐዳር እያለ ወደ ዞን አምስትም ይሻገራል። ስለዚህ በአጠቃላይ አሁን ያለን የተፈናቃይ ቁጥር ከ300,000 በላይ ይደርሳል።»
በዚሁ ጦርነት የተፈናቀሉትን የተሻለ ደህንነት ወዳለበት አከባቢዎች እንዲጠጉ እየተሠራ መሆኑን አቶ መሐመድ ተናግረዋል። ጭፍራ አከባቢ የነበሩት 60 ሺህ ገደማ ተፈናቃዮች ወደ ሚሌ አቅጣጫ 50 ኪ.ሜ. ያህል ርቀት ላይ በተገነባ መጠለያ እየተረዱ መሆናቸውንም ገልጠዋል። ለተፈናቃዮቹ ለመድረስ መንግሥት እና የርዳታ ተቋማት ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም፤ በቂ እንዳልሆነ ግን አክለዋል። እስከ ከሚሴ አዋሳኝ ወረዳዎች ከ1.3 ሚሊየን የማያንስ ሕዝብ የጦርነቱ ውጤት ገፈት ቀማሽ መሆኑንም ኃላፊው ዐስታውቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ በባቲ ካሳጊታ አርሚ 4 የተሰኘው የሕወሓት ሰራዊት ላይ የመንግሥት ኃይሎች ምሽግ ሰብረው የበላይነት መውሰዳቸውን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ማምሻውን ዐሳውቋል። በዚህ ውጊያም ዐሥር ሺዎች ተደምስሰው የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም «በመቶዎች የሚቆጠሩ የጠላት» የተባለ ሰራዊት መማረክ መቻሉንም ዐስታውቋል።
*የኢትዮጵያ አየር ክልል ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዛሬ ዐስታወቀ። የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያን ጨምሮ በኢትዮጵያ አየር ክልል የሚደረጉ በረራዎች አስተማማኝ እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በድረ ገጹ ገልጧል። በመገናኛ አውታሮች የተጠቀሰው እና ቀደም ሲል የወጣው መግለጫ፦ «መሠረተ ቢስ እና ከእውነታው የራቀ» ነው ብሏል። የውጭ የዜና አውታሮች በትናንትናው እለት የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (FAA) ወደ አዲስ አበባ ስለሚደረጉ በረራዎች ለአውሮፕላን አብራሪዎች የሰጠውን ማስጠንቀቂያን አሰራጭተው ነበር። ረቡዕ ዕለት የወጣው የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ አውሮፕላኖች ላይ «በቀጥታ አለያም በተዘዋዋሪ» ከምድር ለምድር ወይም ከምድር ወደ አየር ለሚተኮስ መሣሪያ ሊጋለጡ ይችላል ብሎ ነበር። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የያዙ የደኅንነት እና የጥበቃ መስፈርቶችን እንደሚከተል ዐሳውቋል። የበረራ ክልሎቹ እና የአውሮፕላን ማረፊያዎቹ ተጠቃሚ ደምበኞቹ ደኅንነታቸው እና ጥበቃቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ በመጥቀስ፤ አስተማማኝ መሆኑንም «በጥብቅ ልናረጋግጥላችሁ» እንሻለን ብሏል በመግለጫው።
*የአማራ ክልል ለጦርነቱ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ በመሆኑ የፌደራሉ መንግሥት ለክልሉ አስፈላጊውን የበጀት እገዛ እንዲያደርግለት ጠየቀ። አብዛኛውን የጦርነቱ ወጪ የሚሸፍነውም በክልሉ መሆኑ ተገልጧል። በዚህም የተነሳ በክልሉ የበጀት እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልና በክልል በጀት ሊገነቡ የታሰቡ አዳዲስ የልማት ሥራዎች እንደማይከናወኑም ክልሉ ዐስታውቋል። በ2014 ዓ.ም ሊጀመሩ ታስበው የነበሩ «አዳዲስ የካፒታል ፕሮጄክቶች» እና አስገዳጅነት የሌላቸው በክልሉ በጀት ሊሠሩ የታሰቡ አዳዲስ ፕሮጄክቶች ለጊዜው እንዲቆዩም መወሰኑን የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሐሪ ዛሬ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«የክልሉ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት አንጻር የፌዴራል መንግሥትም እዚህ ላይ እገዛ እንዲያደርግልን ጥያቄ አቅርበናል ከዚህ በፊትም፤ አሁንም እናቀርባለን። ምክንያቱም ጠላት በመውረሩ ብዙ ኪሳራዎች፤ ሰብአዊም ቁሳዊም ጉዳቶች ደርሰዋል። ይኼንን ሊያካክስ የሚችል ነገር የፌዴራል መንግሥት ማድረግ አለበት ብለን እየጠየቅን ነው። ጦርነቱ በሚካኼድበት በአሁኑ ወቅት እንኳን ብዙውን ወጪ በክልል በኩል ነው እየተሸፈነ ያለው። ጦርነቱ በክልሉ በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።»
የአማራ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ ለአማራ ክልል የካፒታል ማስፈፀሚያና ለመደበኛ ወጪዎች ከ80 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን ዐሳውቆ ነበር። ከዚህ በጀት ውስጥ 34 ቢሊዮን ብር ከክልሉ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን፤ 200 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከውጪ ረጂ ድርጅቶች በርዳታ ይሰጣል ተብሎ የታሰበ ነው፡፡ ጦርነቱ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ የፈጠረ ሲሆን፤ ከ1 ሚሊዮን በላይ ደዎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል። 6 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በችግር ላይ እንደሚገኙ መንግስት ዐስታውቋል።
ይህ ከቦን ከተማ የራይን ወንዝ አቅራቢያ የሚያሰራጨው የዶይቸ ቬለ ሬዲዮ ዜና ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊያ የድርቅ ኹኔታው «በከፍተኛ ፍጥነት» እየተባባሰ መሆኑን አስጠነቀቀ። በዚህም የተነሳ ሶማሊያ ውስጥ 2,3 ሚሊዮን ሰዎች የውኃ እና የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ዓለም አቀፍ ድርጅቱ ገልጧል። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA)በድርቁ የተነሳ ወደ 100.000የሚጠጉ ሰዎች ከቀዬያቸው መፈናቀላቸውን ዐስታውቋል።
*አውስትሪያ በመላ ሀገሪቱ የጸረ ኮሮና ክትባት አስገዳጅነትን በመደንገግ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች። እንደ ጎረቤቷ ጀርመን የኮሮና ተሐዋሲ በከፍተኛ ሁኔታ የተሠራጨባት ኦስትሪያ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ደግሞ ሀገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲተገበር አውጃለች። በዚሁ ሳምንት ተመሳሳይ ገብ ባልተከተቡት ላይ ብቻ ተጥሎ ነበር። ኦስትሪያ ውስጥ ባለፉት ሰባት ቀናት የተመዘገቡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከእያንዳንዱ 100,000 ሰው 1,000 በኮሮና እየተጠቃ ነው። አምስተኛ፤ ስድስተኛ አለያም ስድስተኛ የኮሮና ወረርሽን ማስተናገድ አንሻም ያሉት የሀገሪቱ መራኄ-መንግሥት አሌክሳንደር ሻለንቤርግ ስለ ክትባቱ አስገዳጅነትም ዛሬ በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።
«አሁን ውሳኔ ላይ የተደረሰበት በሀገር አቀፍ ደረጃ የክትባት አስገዳጅነት እንደሚኖር ነው። ይህም ከሚቀጥለው ጥር 24 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።»
በዚህ አዋጅ የጸረ ኮሮና ክትባትን አስገዳጅ በማድረግ አውስትሪያ ከአውሮጳ ሃገራት የመጀመሪያዋ ሆናለች። በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እድሜያቸው ከአምስት እስከ ዐሥራ አንድ ድረስ ያሉ ሕጻናትን መከተብ በመጀመርም የኦስትሪያ መዲና ቪዬና ከአውሮጳ ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን ዐሳይታለች። ከፊታችን ሰኞ ይጀምራል የተባለው የእንቅስቃሴ ገደብ ቢበዛ ለ20 ቀናት የሚቆይ ነው። ከዐሥር ቀናት በኋላ ኹኔታው ተገምግሞ ገደቡ ለተከተቡት ብቻ የሚነሳ መኾኑም ተገልጧል። ኦስትሪያ ውስጥ ገደቡ በሚጣልባቸው ቀናት ማንኛውም ሰው ለሥራ እና እንደ ምግብ አለያም መድኃኒት አስፈላጊ የኾኑ ጉዳዮችን ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ከመኖሪያ መውጣት አይቻልም። ይህን በሚተላለፍ ላይ ቅጣት ይኖራል ተብሏል። መዋእለ ሕጻናት እና ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው ቢቆዩም ወላጆች በተቻለ መጠን ልጆቻቸውን ቤታቸው እንዲያቆዩ ተመክረዋል። 8.99 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት ኦስትሪያ አራተኛ ዙር የኮሮና ወረርሽኝ ተቀስቅሷል። ለወረርሺኙ መስፋፋትም የሀገሪቱ መራኄ-መንግሥት ያልተከተቡ ሰዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
*ከአውስትሪያ ባሻገር ጀርመንም አዲስ የኮሮና ደንብ አውጥታለች። የኮሮና ተሐዋሲ በከፍተኛ ፍጥነት በተሰራጨባት ጀርመን የወጣው አዲሱ ደንብ በሥራ እና በሕዝባዊ መገናኛ ሥፍራዎች ለመገኘት መከተብ፣ ተመርመሮ ከተሐዋሲው ነጻ መሆንን አለያም ከተሐዋሲው ስለማገገም ማረጋገጫማሳየት (3G)ያስፈልጋል ተብሏል። ከፊታችን ረቡዕ አንስቶ በመላው ጀርመን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ለመግባት ከሦስቱ አንዱ ያስፈልጋል ተብሏል። ያልተከተቡ ሰዎች በራሳቸው ወጪ ምርመራ ማድረግ ይገባቸዋል። ከዚያም ባሻገር የአፍና አፍንቻ መሸፈኚያ ማድረግ ግዴታ ሲሆን ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነትም ይወሰናል ተብሏል። በጀርመን ሀገር ተወዳጅ የሆነው የገና ሰሞን ገበያ ባየርን በተባለው ግዛት ሙሉ ለሙሉ መሰረዙም ተገልጧል። በባየርን የምሽት ጭፈራ ቤቶች፤ ቡና ቤቶች እና በምሽት የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ እንዲዘጉ ተወስኗል። የጀርመን የጤና ሚንሥትር ዬንስ ስፓን፦ ጀርመን ውስጥ የኮሮና ሥርችቱ ካለፈው ሳምንት እጅግ በከፍተኛ ኹኔታ መጨመሩን ዛሬ ይፋ በማድረግ «እጅግ አሳሳቢ» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዓለም ዜናውን ሙሉ ዘገባ እዚህ
dw ማድመጥ ይቻላል።
<
>