ለቸኮለ! ሰኞ ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

November 8, 2021

1፤ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም እና ደኅንነት ምክር ቤት ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ዙሪያ እንደሚወያይ ምክር ቤቱ በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የኅብረቱ የፖለቲካ፣ ሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ ግጭቱን አስመልክተው ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የሚሰጡ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ የኅብረቱ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆም ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ እያደረጉት ስላለው ጥረት ገለጻ እንደሚያደርጉ ተገልጧል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ምክር ቤቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ የለም። የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ግን ውይይቱ እንደተካሄደ እና ኦባሳንጆ በሰጡት ገለጻ ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩም፣ ለንግግር የሚሆኑ በሮች አሉ በማለት መናገራቸውን ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ዘግቧል።

2፤ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ትናንት ወደ መቀሌ አቅንተው ከሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔል ጋር እንደተወያዩ የሕወሃት ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኦባሳንጆ እና ደብረጺዮን ውይይት በትግራዩ ግጭት እና በሰብዓዊ ቀውሱ ዙሪያ እንደነበር እና በግጭቱ ዙሪያ ደብረጺዮን የሕወሃትን አቋም ለኦባሳንጆ እንደገለጹላቸው ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ኦባሳንጆ ወደ መቀሌ የተጓዙት ከተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ጋር ነው። የሕወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ዛሬ ለዶቸቨለ በሰጡት ቃል፣ በትግራይ ላይ ፌደራል መንግሥቱ ጥሎታል ያሉትን እቀባ ካነሳ፣ ሕወሃት ተኩስ አቁም ለማድረግና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

3፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ ከሚደረጉ ጉዞዎች ውጭ ሌሎች ጉዞዎችን በሙሉ ለጊዜው ማቋረጡን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ድርጅቱ ሠራተኞቹ እና ዲፕሎማቶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ያገደው፣ የሀገሪቱ ጸጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ የደኅንነት ስጋት ፈጥሯል በማለት እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዙሪያ እንደሚመክር ይጠበቃል። ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት ሊያካሂድ ያሰበውን ስብሰባ ለዛሬ በማዛወር፣ በምትኩ የምክር ቤቱ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ባወጡት መግለጫ የግጭቱ ተፋላሚ ወገኖች ባስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ይታወሳል።

5፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያ ሁለት ወታደራዊ ኢላማዎችን እንደደበደበ የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። አንደኛው ኢላማ በደቡባዊ ትግራይ ራያ ዞን ውስጥ አረዳ ባታ በተባለ ቦታ የሚገኘው የሕወሃት ታጣቂዎች ማሰልጠኛ ጣቢያ ሲሆን፣ ሌላኛው በሰሜን ወሎ ዞን እና በአፋር ክልል አዋሳኝ ልዩ ስሙ ኪሊዋ ወይም ሐጂሜዳ በተባለ አካባቢ የሚገኝ ሌላ የታጣቂዎች ማሰልጠኛ፣ የአማጺ ቡድኑ የሎጅስቲክ ማከማቻ እና የተጠባባቂ ታጣቂዎቹ ማቆያ ሥፍራ እንደሆነ ተገልጧል።

6፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስም ማንነትን መሠረት ያደረገ የሚመስል ጅምላ እስር እየተካሄደ ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል። እስሩ ሕጸናትን ያሏቸውን እናቶች ጨምሮ ሰሞኑን በተለያዩ በርካታ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው፣ ከመንገድ እና ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው በፖሊስ ጣቢያዎች መታሰራቸውን እንዳረጋገጠ የገለጠው ኮሚሽኑ፣ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ታሳሪዎቹን እንዳይጎበኙ እና ምግብ እና አልባሳት እንዳያቀብሏቸው እንደተከለከሉ ገልጧል። ጸጥታ ኃይሎች በተጠርጣሪዎች ላይ የሚወስዱት ርምጃ ስብዓዊ መብቶችን፣ ሕጋዊነት፣ የጥበቃ አስፈላጊነትን እና ከመድልዖ ነጻ የመሆን መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እንዲሆን ኮሚሽኑ አሳስቧል።

7፤ አሜሪካን፣ ብሪታኒያን እና ጀርመንን ጨምሮ 16 የበለጸጉ ሀገራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በትግራዩ ጦርነት ላይ ያወጡትን የዓለማቀፍ መብቶች ጥሰት የምርመራ ሪፖርት በደስታ እንደተቀበሉት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የሪፖርቱን ግኝቶች መቀበሉን፣ ቀጣይ ምርመራዎችን ለማድረግ እና ሕጋዊ የማስተካከያ ርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል መግባቱን ያደነቁት ሀገራቱ፣ የኤርትራ መንግሥት እና ሕወሃትም ተመሳሳይ ርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

8. ዛሬ በኢትዮጵያ ፌስቡክ፣ ሜሴንጀር፣ ኢንስታግራም እና የተወሰኑ የዋትስአፕ እና ቴሌግራም መገናኛ ዘዴዎች እንደማይሰሩ የሀገራትን ኢንተርኔት የሚከታተለው ኔትብሎክስ የተሰኘው ድርጅት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ አገልግሎት ያቋረጠው፣ ዛሬ የተጀመረው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ወረቀት ተሰርቋል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጧል። መንግሥት ግን ፈተናው ተሰርቆ ወጥቷል መባሉን አስተባብሏል።

9፤ ሀገር ዓቀፉ የፈተናዎች ድርጅት ዛሬ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን መስጠት እንደጀመረ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ፈተናው በአማራ ክልል የግጭት ቀጠና በሆኑት ሰሜን ወሎ ዞን፣ ደቡብ ወሎ ዞን እና ዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የማይሰጥ ሲሆን፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተናው እንደማይቀመጡ ተገልጧል። በግጭት ሳቢያ ዛሬ የተጀመረውን ፈተና ለማይወስዱ ተማሪዎች ኤጀንሲው ወደፊት በሁለተኛ ዙር ለሚሰጠው ፈተና እንዲዘጋጁ ያደርጋል ተብሏል።

10፤ የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት መሪ እና የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ከዓመት በኋላ በነጻ ምርጫ በሚመረጥ መንግሥት ውስጥ ለምርጫ እንደማይቀርቡ ለአልጀዚራ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ቡርሃን በመፈንቅለ መንግሥት በተወገደው የጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥት ምትክ ሌላ የሲቪሎች መንግሥት ማዋቀር እንደሚፈልጉ ገልጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱዳን ሙያተኞች ማኅበር ጦር ሠራዊቱ በድጋሚ የሽግግር መንግሥቱ አካል መሆን የለበትም በማለት ለትናንት እና ዛሬ ሀገር ዓቀፍ ሥራ ማቆም አድማ እንደጠራ አልጀዚራ ዘግቧል።

11፤ ቻይና በኬንያ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ልታቋቁም አስባለች በማለት የአሜሪካው ፔንታጎን ለሕግ መምሪያ ምክር ቤቱ ባቀረበው ማስጠንቀቂያ አዘል ሪፖርት መግለጡን የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳጣጣለው በኬንያ የቻይና ኢምባሲ ማስታወቁን ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ አስነብቧል። አሜሪካ በቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ጊዜ ከነበራት የኃያላን ጅዖፖለቲካዊ የፉክክር ስነ ልቦና ገና አልወጣችም ያለችው ቻይና፣ አሜሪካ ሃላፊነት የጎደላቸው ሪፖርቶችን ከማውጣት እንድትቆጠብ አሳስባለች። አሜሪካ እና እንግሊዝ በኬንያ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች ያሏቸው ሲሆን፣ ቻይና ደሞ ብቸኛው ወታደራዊ ጦር ሠፈሯ በጅቡቲ ያቋቋመችው ጦር ሠፈር ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

፲፩ኛ ስዓት፡ ዕድል እና ገደል= ገድል + ድል

Next Story

የአንቶኒ ብሊንከን መግለጫ ዋና ጭብጥና የዐብይ አሕመድ ሚና

Go toTop