በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 448ሺህ 550 የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ዋለ

September 21, 2021

መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 448ሺህ 550 የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ዳሽን ቢራ በመጫን መነሻውን ከአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ ያደረገው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-26981 ኢት.ተሳቢ የጭነት ተሽከርካሪ አዲስ አበባ ከተማ ከደረሰ በኋላ ወደ ሀረር ከተማ በማቅናት ላይ እያለ ዛሬ ቃሊቲ ኬላ ላይ በተደረገበት ፍተሻ አሽከርካሪው በህገወጥ መንገድ ሲያጓጉዘው ከነበረ አራት መቶ አርባ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ የአሜሪካ ዶላር ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።

በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ዶላር በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ አሽከርካሪው ዶላሩን በቢራ ሳጥን ውስጥ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞክር

በኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው አሽከርካሪ ከነ ዶላሩ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተላልፎ ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑም ታውቋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ቀድሞ በዘረጋቸው ኔትዎርኮች በንግድ ተቋማት የሚሰበሰብ ዶላርን በሀገወጥ መንገድ በውድ ዋጋ እየገዛ ከሀገር እንዲወጣ እና በሀገር ውስጥ የዶላር እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አንዱና ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ነው የተገለጸው።

አሸባሪው ከዚህ የሚያገኘውን ገቢ ለሽብር ተግባር መፈፀሚያ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግለው ሲሰራ መቆየቱን ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት መግለጹን አስታውሷል።

ይህንን ለመከላከል ፖሊስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ኦፕሬሽን በጥቁር ገበያ ላይ የሚንቀሳቀሰው ህገወጥ የዶላር ምንዛሪ እየቀነሰ መምጣቱን አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ባካሄዱት የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጣቸውንም ነው የተገለጸው።

በአሸባሪው የህወሃት ቡድን አባልነት የሚጠረጠሩ አንዳንድ ግለሰቦች አሁንም ከድርጊታቸው ያልተቆጠቡ መሆኑን በተደረገው ክትትል መረጋገጡን የገለጸው ፖሊስ፤ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳሰቅ የነበረው ዶላር በቃሊቲ ኬላ የተያዘው በህብረተሰቡ ትብብር መሆኑንም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ መረጃውን ላደረሱ ግለሰቦች ምስጋና በማቅረብ፤ በቀጣይም ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ከህግ አስከባሪዎች ጎን በመሰለፍ፣ ጥቆማ በመስጠትና መሰል ህገወጥ ተግባራትን በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ዕውን ከአሜሪካ ጋር “ባንለካካ” እና ከወያኔ ጋር ብንደራደር ይሻለናል? – አንድነት ይበልጣል

Next Story

“በዓለም ላይ ያሉ አሸባሪዎች የሚረሽኑት ሰዎችን ነው፤ ህወሓት ግን ሰዎችን ረሽኗል፤ እንስሳትን ረሽኗል፤ እጽዋትንም ረሽኗል” – ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

Go toTop