“ጣውላ ረዘም ያለ ምስማር ሲመታባት፤ ምሥማርን ምነው ጎዳሽኝ ብላ አፍ አውጣት ብትናገር፤ ምስማር ጮክ ብላ በአናቴ ላይ የሚያርፈውን መዶሻ ብታይ አይዞሸ ነበር የምትይኝ! አለች የሚል ቢህል አውቃለሁ!
የመከላከያ ሠራዊት እና የመንግሥት አገልግሎቶች የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ ትግራይ ክልልን በከፊል መልቀቃቸው ይታወቃል፡፡ ይህን አስመልክቶ ከተሰጡት ማብራሪያዎች አንፃር ገዝፎ የወጣው “ጦሩ በሕዝብ ጭምር ጥቃት እየደረሰበት መሆኑ ነው!” የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህ የሚያሳየው የትግራይ ሕዝብ ለህወሓት ያሳየውን ግልፅ ወገንተኝነት ነው፡፡ ደጀን የሌለው ጦር ዝም ብሎ ማለቅ አለበት ካልተባለ፤ የትግራይ ሕዝብ ለሠራዊቱ ደጀን ለመሆን ለምን አልቻለም? ይልቁንም የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን ለምን ይደግፋል? የሚለው ጥያቄ በቅጡ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ብዙ የመላምት ምላሾች ቢኖሩም የትኞቹም ቢሆኑ ይህን ጥያቄ አሟልተው ሊመልሱ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ጥቂቶቹን እንመልከት፤
መላምት 1፤ ከህወሓት ሥርዓት ተጣቃሚ በመሆኑ ነው!
በትግራይ ውስጥም ሆነ ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ አብዛኛው ሕዝብ ከሌሎች በተለየ የኑሮ ሁኔታ ላይ ነው ለማለት የሚያስችል ተጨባጭ መረጃ የለም፡፡ እርግጥ ነው፤ ቀላል የማይበሉ የትግራይ ተወላጆች በተለያየ መስክ በሚደረጉ ያልተገቡ ግንኙነቶች ተጠቅመው፤ በዘረፋ ላይ ተሰማርተው ቅምጥል ኑሮ እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ግን ከ1.8-2 ሚሊዮን የሚጠጋ የትግራይ ሕዝብን በዕለት ደራሽ እርዳት ሊያወጣው አልቻለም፡፡ ትግራይ በተለየ ሁኔታ ተጠቅማለች የሚለውንም ተረክ በመቀሌ እና በአንድ አንድ ከተሞች በሚገነቡ ሕንፃዎች ለማስረዳት ካልተሞከረ በስተቀር የሰፊውን ዜጎች ሕይወት ሊቀይሩ የቻሉበት ሁኔታ አልታየም፡፡
ህወሓት በ30 ዓመት የገዢነት ታሪኩ የትግራይን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት ሊያሟላ ያልቻለ ድርጅት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ይህ ሕዝብ ከህወሓት ጎን በመሰለፍ የሕይወት ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነው፡፡ ሰለዚህ የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት ጎን መሰለፍ ከጥቅም ጋር የተያያዘ ነው ለማለት የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ህወሓት ተሸንፎም ቢሆን ከለላ በመስጠት እና ደጀን በመሆን የሚያሳዩት ነገር ፍቅራቸው ከጥቅም ጋር የተያያዘ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡
መላምት 2፤ ህወሓት በዘረጋው የአፈና መዋቅር ምክንያት ሰለሚፈራ ነው!
ህወሓት የዘረጋው የአፈና መዋቅር የትግራይ ሕዝብ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ የማድረጉ ነገር እውነት ቢሆንም፤ በዚህ መላምት ምክንያት ባለፈው 30 ዓመት በመላው ኢትዮጵያ የነፃነት እንቅስቃሴ ሲፋፋም በትግራይ እዚህ ግባ የሚባል እንቅስቃሴ ማድረግ ያለመቻሉን አንደ ሰበብ ሲቆጠር ነበር፡፡ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመሃል አገርም ሆነ በሌሎች ክልሎች ያሉ በተመሳሳይ ዝምታ ሲከፋም ህወሓት በመደገፍ ለመሳተፋቸው እንደ ሰበብ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ህወሓት ሲመታና ለአፈና የሚሆን አቅም ባጣበት ከሕዳር 19 በኋላም ቢሆን ህወሓትን ልክ አይደለም ብሎ ደፍሮ ለመናገር የሚደፍሩ በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት መቀሌ መቆጣጠሩን ተከትሎ ጄኔራል ባጫ “አሁን የትግራይ ሕዝብ በሠላማዊ ሠልፍ ደስታውን ይገለፃል!” ምክንያቱም “ምንም የሚያስፈራራው ሀይል የለም!” ብለው ተስፋ ቢያደርጉም እስከ ዛሬ ድረስ ከምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ በመባል የሚታወቁት (አሁንም በጦሩ ቁጥጥር ሥር ያሉትና ደጀን የተባሉት አካባቢዎች) በስተቀር በዋና ከተማ መቀሌ የድጋፍ ሠልፍ ማየት አልተቻለም፡፡
ከዚህ አንፃር የትግራይ ሕዝብ ለህወሓት ያለው ድጋፍ በአፈና የተዘጋጀ መዋቅር በመፍራት ብቻ ነው ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በተለይ የህወሓት ቁጥጥር በሌለባቸው የውጭ ሀገርና የመሀል አገር ይህ በፍፁም ሰበብ ሊሆን እንደማይችል መገመት ይቻላል፡፡
መላምት 3፤ የትግራይ ሕዝብ የደረሰበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጋር ሊወግን የቻላው በሌሎች ሀይሎች እየደረሰብት ያለው መከራ ሰለገፋው ነው! የሚሉ መከራከሪያዎች መቅረብ ጀምረዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በኤርትራ፤ በመከላከያና በአማራ ልዩ ሀይል የሴቶች መደፈር፤ የንብረት ዘረፋ፤ ወዘተ ተቆጭቶ ነው ወደ ህወሓት የተጠጋው የሚሉ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ በሰበብነት የቀረቡት ነገሮች ተፈጠሩ ከመባላቸው በፊትም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት መስመር ውጭ የሆነበት ጊዜ ታይቶ አይታወቀም፡፡ እነዚህ ጥቂት እውነት ያዘሉ፤ በፕሮፓጋንዳ የገዘፉ እና የዓለም ማህበረሰብን ጭምር ያንጫጩ ድርጊቶች የህወሓት የእጅ ሥራዎች አለመሆናቸው ጭምር በገለልተኛ አካል መጣራት የሚኖርበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን የትግራይ ሕዝብ አሁን ደረሰበት የተባለውን መከራ ለመቀነስ ወይም እንዲቀር ለማድረግ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ከህወሓት ጎን በመቆም የወሰዳቸው ድርጊቶች አንገት የሚያስደፉ ናቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል የሰብዓዊ መብት ማክበር ሪከርድ የሌለውን ድርጅት በመደገፍ ሲካፍም የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረግ የሚታረም አይደለም፡፡
ሰለዚህ የደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት መደፈር ለህወሓት እንዲያድሩ አድርጓቸዋል የሚለውን ለመውሰድ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ህወሓት በሰብዓዊ አክባሪነት ድጋፍ ሊያገኝ የሚችል ድርጅት መቼም ሊሆን አይችልም፡፡
መላምት 4፤ የትግራይ ህዝብ ህወሓት ከሌለ ይጠፋል ይህ ቀደም ሲል በፓርቲው ምሥረታ ወቅት የትግራይ ብሔረተኝነትን ለማስፈን “የአማራ ገዢ መደብ” በሚል የተጀመረን የጠላትነት ተረክ አሁን ደግሞ ሌሎች ተጨምረው ከኤርትራ መንግሥት እና ከአብይ መንግሥት በሚል “የትግራይ ሕዝብ ከበባ ውስጥ ነው!” የሚል የሥጋት ተረክ እየተሰራጨ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሚገርም ሁኔታ አብረውን የሚኖሩ የትግራይ ሰዎች ሁሉ ይህን ፕሮፓጋንዳ አምነው መከላከል እንዳለባቸው ይሰማቸዋል፡፡ በፍቅር የምናውቃቸው ወንድም እህቶች ሊያጣፉን ነው የሚል እሳቤ ውስጥ መገኘታቸው ሊያበሳጭ ሁሉ ይቸላል፡፡ ወጣት ሴት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንኳን “ለትግራይ መሞት ክብር ነው!” እስከሚሉ ድረስ የዚህ ትርክት ሰለባዎች ናቸው፡፡ በግሌ የአማራ ልሂቅ ይሁን ሕዝብ ወይም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምን የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት ይሰራል ብለው እንደሚያምኑ ለመረዳት ይከብደኛል፡፡ እንደ መንግሥትም ይህ ግብ ሆኖ ሊሰራ የሚችልበት አንድም ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚጠፋበት ሁኔታ ባይኖርም፤ ቢጠፋ ሌሎች ምን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ለመረዳትም አልችልም፡፡እንደዚያም ሆኖ ግን በዚህ የተሳሳተ “የተከበናል” ትርክት የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጋር ተቆራኝቷል ብዬ ለማመን እገደዳለሁ፡፡
ችግሩ የዚህ ተረክ ተቀባይ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ይሀን ተረክ የሚያስፋፉት ነብስ ዘርተውበት እውነት የሚያስመስሉት፤ ጥቂት ጥቅማቸው የተነካበቸው ተጋሩዎች መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ምንም ዓይነት ዋጋ የሚከፍሉ ይሉኝታ ቢሶች እንደሆኑ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የትግራይን ሕዝብ በእሳት ሲማግዱት የጭራሩን ያህል የማይሳሱለት፤ በረሃብና ሞቱ ሲነግዱ አንዲት የፍየል ግልገል ያጡ የማይመስላቸው፤ አስርበው ፎቶዎን ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያውሉ፣ ከዚህ በሚገኘው ጥቅም ተንደላቀው የሚኖሩ፤ ለግልና ለቡድን ፍላጎታቸው ያደሩ የሞራል ልሸቀት ላይ የሚገኙ የትግራይ ልጆች መኖራቸው እኔ የገባኝ አውነት ለጊዜው ይህ ነው፡፡
ሠላም ለኢትዮጵያ አገራችን እና ሕዝቧ
ግርማ ሰይፉ ማሩ