የእንባ ጠብታ – እኔንያየህተቀጣ

February 18, 2021

በፈረንጆች አቆጣጠር ኦክቶበር 8, 2018 ከምሽቱ ከምሽቱ አራት ሰዓት ሆኗል:: ከሁለት ወራት የአዲስ አበባ ቆይታ በሁዋላ ወደሰሜን አሜሪካ ለመመለስ ከአዲስ አበባ ቶሮንቶ ለመብረር በተዘጋጀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ET502 አውሮፕላን ውስጥ ቁጭ ብያለሁ:: በአዲስ አበባ ቆይታዬ ከቤተሰብ: ጉዋደኛ: እና ወዳጅ ዘመድ ጋር ያሳለፍኳቸውን ጊዜያት በማሰላሰል በሃሳብ ጭልጥ አልኩ:: አንድ ነገር በሃሳቤ ደጋግሞ ይመጣል: የትንሿ እህቴ ቤዛ ነገር:: ስለአሜሪካ ኑሮ የምትጠይቀኝ ጥያቄዎችና: ስለ አዲስ አበባ ከተማ ለውጥ የምታስረዳኝ ነገር ሁሉም ድቅን አሉብኝ:: ቤዛ ከጥቂት ዓመታት በፊት ታዳጊ ሕፃን ነበረች: አሁን ግን ከሶስት ወራት በሁዋላ ከጥቁር አንበሳ በዶክትሬት የምትመረቅ ሀኪም::

 

አንድ መንገደኛ ኤክስክዩዝ ሚ ማይ ሲት ነምበር ኢዝ 13ኬ ብሎ ከሃሳብ ከአነቃኝ:: ለማረጋገጥ የመቀመጫ ቁጥሬን አውጥቼ ተመለከትኩ: 13 ጄ አዎ መንገደኛው የሚቀመጠው በእኔና በአውሮፕላኑ መስኮት በኩል 13 ኤል በተቀመጠችው ሴት መሃከል ነው:: የመስማማት ፊት እያሳየሁ ተነስቼ አሳለፍኩት:: ሻንጣውን ማስቀመጫው ውስጥ ካስቀመጠ በሁዋላ ተቀመጠ:: ምንም ጊዜ ሳያባክን በእንግሊዘኛ ማርክ እባላለሁ አንተን ማን ልበል? አለኝ:: እኔም ዳሞታ እባላለሁ መልካም ትውውቅ አልኩኝ: ምክረአብ የሚለው ስሜ ብዙ ጊዜ ለውጫውያን ስለሚያስቸግር በአያቴ ስም ወይም በአጭሩ በመጀመሪያው ፊደል ዲ ብለው እንዲጠሩኝ አደርጋለሁ::

 

ከአውሮፕላ አስተናጋጆች አንዷ ክቡራትና ክቡራን መንገደኞቻችን: አውሮፕላኑ በረራ ሊጀምር ስለሆነ: የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቻችሁን በማጥፋት:መቀመጫችሁ ላይ በመቀመጥና የደህንነት ቀበቶአችሁን በመታጠቅ እንድትተባበሩን እንጠይቃለን ብላ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ባስተላለፈችው መልዕክት አቁዋረጠችን::

 

አውሮፕላኑ ወደሁዋላ ከሄደና ከአኮበኮበ በሁዋላ በፍጥነት ተነሳ:: አዲስ አበባና አካባቢዋ ያሉ ከተሞች በፍጥነት ወደ ሩቅና ትንንሽ ዕይታዎች ሲቀየሩ ተመለከትን:: ያንን ተከትሎ ከአብራሪዎች አንዱ ክቡራትና ክቡራን ከአዲስ አበባ ቶሮንቶ ወደሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ኢቲ 502 በደህና መጣችሁ:: በጉዞአችን መሃል ደብሊን አየርላንድ ላይ የ45 ደቂቃ ቆይታ ካደረግን በሁዋላ ወደቶሮንቶ የምናደርገውን ጉዞ እንቀጥላለን የሚል መልዕክት አስተላለፈ:: በመቀጠልም የበረራ አስተናጋጆች: አውሮፕላኑ የሚፈለገው ከፍታ ላይ ስለደረሰ የደህንነት ከበቶአችሁን መፍታት: ኤሌክትሮኒክስ መጠቀምና: መንቀሳቀስ ትችላላችሁ:: በጉዞአችን ላይ እራት: መቆያ እና: ቁርስ የምናቀርብ መሆናችንን እንገልፃለን የሚል መልዕክት ተላለፉ:: ማርክ ትከሻውን በመጠኑ ወደእኔ ዘወር ካደረገ በሁዋላ: አዲስ አበባ ላይ ትራንዚት እያደረክ ነው? በማለት ጠየቀኝ :: የለም የለም አዲስ አበባ ለሁለት ወር ቤተሰብ ጥየቃ መጥቼ እየተመለስኩ ነው ከአልኩት በሁዋላ: ምን አይነት ጥያቄ ነው ኢትዮጵያዊ አልመሰልኩትም እንዴ!? አልኩ በሆዴ:: ማርክ ጥያቄውን ቀጠለ: አዲስ አበባ ጥሩ ጊዜ አሳለፍክ? ከዳያስፖራ ሕይወት የተማርኩትን የውሸት ፈገግታ ካሳየሁ በሁዋላ: አዎ ለእረፍት ስትመጣ: በጠዋት አላርም አይቀሰቅህም: ስትነሳ ጥሩ ቁርስ ይቀርብልሃል: የእረፍት ቀናትና በዓላትን ከቤተሰብ: ጉዋደኛ: እና ወዳጆችጋ ሰብሰብ ብለህ ያሳልፋለህ: እያልኩ የጠየቀኝንና: ሊጠይቀኝ ይችላል: ያልኩትን ጥያቄ አንዴ ልመልስና እርፍ ልበል በሚል መለስኩለት:: የበረራ አስተናጋጆች በመንገደኞች ምርጫ እራት ማስተናገድ ጀምረዋል:: እኔ ቤተሰቦቼ የወጪ ብለው በጋበዙኝ ላይ ምንም ነገር ላለመጨመር አስተናጋጆቹን እቆያለሁ አልኳቸው:: መንገደኞች ሲመገቡና የቆርቆሮ ቢራና ወይን ጭምር እያዘዙ ሲጠጡ ዙሪያውን ከቃኘሁ በሁዋላ መታጠቢያ ቤት ደርሼ ተመለስኩ:: የመመገቢያ እቃዎች በአስተናጋጆች ከተሰበሰቡ በሁዋላ የአውሮፕላን ውስጥ መብራት ተቀንሶ ጭልምልም እንዲል ሆነ:: አብዛኞቹ መንገደኞች የአየር መንገዱን ፎጣ መሳይ ብርድልብስ በመከናነብ ተኙ:: ብቻዬን የቀረሁት መሰለኝ: እኔ እንኳን አውሮፕላን ላይ ከለመድኩት ቦታ ውጪ እንቅልፍ አይወስደኝም:: የጆሮ ማዳመጫውን ከሰካሁ በሁዋላ ከፊት ለፊቴ የሚገኝ ተንቀሳቃሽ ምስል ማሳያ ነክቼ የበረራ መረጃዎችን መከታተል ጀመርኩ::

 

በአየር ላይ የቆመ የሚመስለው የኢቲ 502 አውሮፕላን በሜድተራንያን ባህር ላይ 550 ማይል ወይንም 900 ኪ.ሜ በሰዓት ያህል እየከነፈ መሆኑን ያሳያል:: ትራንዚት የምናደርግበት የአውሮፓው ደብሊን ከተማ ለመድረስ የ 8 ሰዓታት ያህል በረራ ይቀረናል:: ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በአግራሞት እንዳፈጠጥኩ በአግራሞት ወንድማማቾቹን ኦሊቨር እና ዊልበርን ራይት ማሰብ ጀመርኩ:: ሁለቱ የአሜሪካው ኖርዝ-ካሮላይና ከተማ ነዋሪዎችና የበረራ ፈጠራ ባለሙያዎች:: ዓለም የአየር በረራዎችን እንደአሁኑ የሸረሪት ድር ከማስመሰሉ በፊት በዲሴምበር ወር 1903 ዓ.ም የመጀመሪያውን የሙከራ በረራ ከመሬት 120 ጫማ ከፍ በማለት ለ 12 ሰከንዶች ያህል በረዋል:: እኔ በአውሮፕላን እየተሻገርኩት ያለሁትን ሜዲተራንያን ባህር አቁዋርጠው አንዱ አውሮፓ ሀገር ለመድረስ በማሰብ ስንት ስደተኞች ህይወታቸውን አጥተው ይሆን ስል ራሴን ጠየኩ:: ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካና አካባቢው ሃገራት ዜጎች ለምን ከሀገራቸው ይሰደዳሉ? ለምንስ ይሄንን የሞትና የሽረት ጉዞ መረጡ? መልስ ለማግኘት በመቸኮል ጉግል ማድረግ ጀመርኩ:: እንደ ዩናይትድ ኔሽን ዩኒቨርሲቲ http://unu.edu ዘገባ ሰዎችን ለስደት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል ድህነት: ጦርነትና: የአየር ንብረት ለውጥ ይገኙበታል:: ከአንዱ የመረጃ መረብ ወደሌላኛው የመረጃ መረብ በመለዋወጥ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረቴን ቀጠልኩ:: እንደ አለማቀፍ ስደተኞች ጉዳይ ማህበር አይ. ኦ. ኤም www.iom.com ዘገባ ከ2016-2019 ባሉ አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ሜዲተራንያን ባህርን ሲያቁዋርጡ ህይወታቸውን ያጡ ስደተኞች ቁጥር:-

2016-3,740
2017-3,139
2018-2,299
2019-1,283 ነው

ህይወታቸውን ከአደጋ ለማትረፍና: የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ተስፋ ሰንቀው በማያውቁት መንገድ ወደማያውቁት ሀገር የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ህይወታቸውን ያጡትንና: የት እንደደረሱ የማይታወቁትን ወንዶች: ሴቶችና: ሕፃናት እያሰብኩ የእንባ ዘለላዎች በጉንጮቼ ላይ ይወርዱ ጀመር :: እንባዬን ከፊቴ ላይ እየጠራረኩ ሳለቅስ መንገደኞች አለማየታቸውን ለማረጋገጥ ዘወር ዘወር አልኩኝ: ሁሉም ተኝተዋል:: ደብሊን ለመድረስ 6 ሰዓት ያህል በረራ ይቀረናል#እኔንያየህተቀጣ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የሞራል ዝቅጠት እና የአድርባይነት ልክፍት ፡ ጣምራ ደዌዎቻችን! – ጠገናው ጐሹ

Next Story

ዛሬም አድዋ! – ጌታቸው ለገሰ

Go toTop