ገረመኝ! ዛሬ ባዩሽ አለማየሁ አንድ ብቻ አልነበረችም፣ ብዙ ነበረች አሉን፤ የስራ ባልደረቦቿ፡፡ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ገጣሚ፣ ዜማ አፍላቂ፣ ተራኪ፣ አክትረስ፤ ከመሆኗም በላይ በሬዲዮ፣ በትያትር ቤቶች፣ በቲቪ፣
በፊልሙ፣ ወ.ዘ.ተ.ተሳታፊ ነበረች ሲሉ! “እነ-ባዩሽ” ብንላት ይገልፃት ይሆን? ዘንድሮ ዲግሪዋንም ከትያትር ጥበባት ክፍል (አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ) ልትቅበል ነበር ብልውናል፡ ስንት አልማ ነበር ይሆን? የሚያሳዝነው ግን በተለይ የሴት ደራሲያን ድርቅ ባጠቃት ሃገር ፡ በህይወት እያለች፡ ይህ ሁሉ ችሎታና ክህሎት አንድም ቀን ስትመሰግንበት ወይም ስትሸለምበት አለማየታችንና አለመስማታችን ነው፡፡ በስንቱ እንቆጭ እንናተዬ ?! በየሚዲያው ተደጋግመው ለዕይታ የሚቀርቡት ውስንና የተመረጡ የሷን ያህል ተሰጥኦ አላቸው ተብሎ ያልተነገሩን ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ችሎታዋ ካለፈች በኋላ ቢዘረዘር ምን ሊጠቅማት፡ እያለች ይህን ምስክርነት ብትሰማ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ዛሬስ እንደሷ የተደበቁ ስንት ይሆኑ፡ ስንቱ ይሆን በራሱ ስራ ሌሎች ሞገስና ሽልማት ሲያገኙበት ቁጭ ብሎ የበዬ ተመልካች የሆነ? ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አና ባጭሩ አርቲስቶች እባካችሁ ፡ በቲፎዞ ሳይሆን የላቁ የሚባሉትን ባለሞያዎች አጉልታችሁ አሳዩ አሸልሙ፡ ነግ በኔ ይልመደባችሁ፡፡ ወይ እስቲ ትንሽ መፅሃፍ ብጤ አዘጋጁና፡ ስለእያንዳንዱ አርቲስት ታሪክና ያበረከተውን አስተዋፅኦ ያለውን ክህሎት የያዘ የጋራ የሆነ (Biography) ነገር ፃፉና አሳትሙ፡ በህይወት፡ እያላችሁ፡፡ ሚዲያዎችም ሃገርን መጥቀም ከሆነ ግባችሁ የታወቁት ላይ ብቻ ክምትረባረቡ የተደበቁትንም አውጡና አበረታቱ፡ ለማለት ያህል ነው፡፡
በመጨረሻም የአርቱን ዘርፍ በእጅጉ ያጎደለቸውን አንድ ሆና ብዙ የነበረቸውን አርቲስት ባዩሽ (እነ ባዩሽ) አለማየሁን ነፍስ ፈጣሪ በገነት ያኑርልን፡ ለቤተሰቦቿና ፡ወዳጅ ዘመዶቿ፡ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡
(ትዕግስት ገላዬ)