ይክበር የአንች ቀን (ዘ-ጌርሣም)

November 22, 2020

ይከበር የአንች ቀን በሆታ በልልታ
ይዘመር ዝማሬ ከበሮ ይመታ
ቢፃፍ ስለማያልቅ የእናቶች ውለታ
ዘጠኝ ወር በሙሉ አንችው ተሸክመሽ
ደምና እስትንፋስሽን ቀንሰሽ አካፍለሽ
ውጋቱን ቁርጠቱን እምቅ አርገሽ ችለሽ
ማሞና ማሚትን በጉያሽ ውስጥ አቅፈሽ
ሽንትና ቅዘኑ ከረፋኝ ሳይወጣሽ
ሰውን ሰው ያረግሽው እናት አንች እኮ ነሽ
ልዩ የዓለም ፀጋ የተፍጥሮ ዉበት
መለኮት የቀባሽ ሰባቱን ቀለማት
ሚስት
እናት
እህት
አክስት
አያት
አይት
ምራት
ተብለሽ እንድትጠሪበት
የሚፈጠሩብሽ አንበሳና አንበሲት
ይከበር ያንች ቀን በሆታ በልልታ
ይዘመር ዝማሬ ከበሮው ይመታ
ቢፃፍ ስለማያልቅ የእናቶች ውለታ
መለኮት ተጠቦ ተጨንቆ ፈጥሮሽ
ምድርን እንድትሞያት አደራ ተብለሽ
ማህፀንን ለብቻሽ መርቆ ሰጠሽ
እናትም አንችው ነሽ እህትም አንች ነሽ
ከደግነት ጋራ ፈትፍተሽ ያጎረስሽ
በምን ቃል ይገለፅ ይዘከር ውለታሽ
የፍቅርን ጎተራ የደግነትን ባንክ
የትዕግሥትን ጋራ የማስተዋልን መስክ
ለእናት ታድሏታል በሰፊው ያለልክ
የቤቱ መሠረት ጉልላቱም አንች
የውስጡን የውጩን የምታመቻች
ሕይወት መና ሁና በቀረች ያለ አንች
ለአያሌ ዘመናት ተጨቁነሽ የኖርሽ
ኋላ ቀር ሥርዓቶች መጠቀሚያው አርገውሽ
በልጆችሽ ትግል ይኸው መድረክ ወጣሽ
በየሥርዓቱ የምትኖሪው እናት
ጭቆናሽ ይለያል በመልክና በዓይነት
አንደኛው ፊትሽን ሸፍኖት ይኖራል
ሌላው በበኩሉ ቤት ቁጭ በይ ይልሻል
ሦስተኛው ትምህርትን ይከለክልሻል
እጥፍ ድርብ በደል ተጭኖሽ ኑረሻል
ዕድሜ ለልጆችሽ ነፃ አውጥተውሻል
አክብሩላት ባዕሏን የእናታችን ቀን
አድምቁላት ባዕሉን የእህታችን ቀን
አደባባይ ወጥታ አብራን መዋሏን
ከድርብ ጭቆና ነፃ እንድትሆንልን
ደመቅ እናድርገው ሆ ! በይው ብለን
ጀግና አይኖርም ነበር አንች ባትወልጅው
ሊቅም አይፈጠር አንች ባታምጭው
ምድር እራቁቷን ነበር የምትቀረው
ጦር ሜዳ ቢልኩሽ ጀግና ታዋጊያለሽ
የፈሪውን ሀሞት ኮስተር ታረጊያለሽ
ከሊቅ ጋር ቢያውሉሽ ታመራምሪያለሽ
ለገበሬውማ አጣማጁ አንችው ነሽ
ወሰኑ አይታይም ሴት ያንች ችሎታሽ
እስኪ ጠቀስ እናርግ ስመ ጥር ሴቶችን
በአድዋ ጣይቱን
የማይጨዋን ነብር ሽዋረግድን
በእስራዔል ማየርን
የእንግሊዟን ታቸር ኢንድራ ጋንዲን
አሁን ካሉት እንኳን አንጀላ መልከርን
አደባባይ ቆመው ደምቀው የታዩትን
የሴትን ችሎታ ያስመስከሩትን
ባሰለፉሽ ቦታ ቀድመሽ ትገኛለሽ
የታመመ አስታመሽ ለዘማች ሰንቀሽ
ፆታሽ ሳይወስንሽ የሴት ወንድ ሁነሽ
በሁሉም ሙያ መስክ ቀድመሽ ትታያለሽ
ይከበር ያንች ቀን በሆታ በልልታ
ይዘመር ዝማሬ ከበሮው ይመታ
ቢፃፍ ስለማያልቅ የሴቶች ዉለታ
እናክብረው በዓሉን የእናትችን ቀን
አደባባይ ወጥታ አብራን መዋሏን
ከድርብ ጭቆና ነፃ መሆኗን
እናድምቀው በዓሉን እልል ሆ ! ብለን
ይበሰር ደስታው ትውልዱም ይወቀው
ስህተት እንዳይሰራ እንዳያስጠይቀው
ታሪክ ተረካቢ ወጣቱ ነውና
አብረነው እንቁም ክንዱ እስከሚጠና

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ሰበር ዜና/የመከላከያ ሠራዊት በአድዋ ተምቤን መሥመር ማይቅናጥል በተባለውና ልዩ ስሙ ሰላስል በተሰኘው የሐውዜን ተምቤን መገንጥያ መንገድ

Next Story

ወታደሮች ተላልፈው ተሰጡ፣300 ሰዎች ራሳቸውን ስተው ተገኙ፣ቄሮ የዘጋው መንገድና መንግሥት ያገደው አካውንት”72 ሰዓት ብቻ”ጠቅላይሚንስትሩ

Go toTop