ተጠየቅ (ዘ-ጌርሣም)

November 19, 2020

ተጠየቅ በህግ ፊት
ለፈፀምከው ክህደት
ቁምና ተሟገት
ሳይበየንብህ የዕድሜ ልክ እሥራት
ምስክር ከሌለህ
ዋቢም ካልቆመልህ
በወፍና ድንጋይ
ቀርበህ አደባባይ
እሰጥ አገባ በል
ከቻልክም አስተባብል
መሃላውን ፈፅም እውነቱን ተናገር
ህሊናህን ሞግት ያለ መደናገር
ተጠየቅ በህግ ፊት
ለፈፀምከው ክህደት
ቁምና ተሟገት
ሳይበየንብህ የዕድሜ ልክ እሥራት
ትናንት ሕዝብ በደልክ
የሀገር ጦር በተንክ
ከሥራም አባረርክ
ከሀገር አሰደድክ
የተፋለመህን እሥር ቤት ውስጥ አጎርክ
በጭካኔ በትር አካላት አጎደልክ
ወጣት አኮላሸህ
ጉብሏን አመከንህ
የእምነት ስዎች ደፍርክ
ሃይማኖት አረከስክ
ታሪክን
እምነትን
ባህልን
ሰብዕናን (ሰውነትን)
አቆሸሽክ
ተጠየቅ በህግ ፊት
ለፈፀምከው ክህደት
ቁምና ተሟገት
ሳይበየንብህ የዕድሜ ልክ እሥራት
ገበሬ እያሞገስክ
እሱኑ የበደልክ
መልሰህ የገደልክ
አምኖህ የኖረውን
አብሮህ የበላውን
አብሮህ የሞተውን
በቸገረህ ጌዜ አብሮህ የቆመውን
ደክሞት በተኛበት
በደረቁ ሌሊት
መከላክያውን
የሀገር መከታውን
ብሔር የሌለውን
ፖለቲካ ስልጣን የማይመኘውን
የዚያችን ድኃ ልጅ
የዚያን አፈር ገፊ የገበሬን ቀኝ እጅ
አንተን እያኖረ ለራሱ የማይበጅ
ሲያገኝ ፍርፋሪ
ሲያጣ ጦም አዳሪ
እሱ እየሞተ ሌላውን አኗሪ
በሆነው ወገን ላይ
በፈፀምከው በደል ባደረስከው ስቃይ
የጥይት እሩምታ እንዳዘነብክበት
የእጅህን አታጣም ቀኗ የመጣችለት
ተጠየቅ በህግ ፊት
ለፈፀምከው ክህደት
ቁምና ተሟገት
ሳይበየንብህ የዕድሜ ልክ እሥራት

2020-11-19

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ሰይጣን ለወያኔ እጅ ሰጠ! – ይነጋል በላቸው

Next Story

” ኦሮማይ ! ”  በቋንቋ ና በዘር መቧደን አከተመ፡፡… – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Go toTop