የማይቻል የለም    (ዘ-ጌርሣም)

September 19, 2020

የማይቻል የለም ለሰው የሚሳነው
ብሩህ አዕምሮና ቅን ልቦና ካለው
ከአምላክ በተሰጠው ፀጋ ካወቀበት
የሚያቅተው የለም የማይሳካለት
ተፈጥሮ ምሥጢር ነው
ብዙ ትርጉም ያለው
የረቀቀ ጥበብ
ጠውልጎ የሚያብብ
ተረካቢ እሚሆን ትውልድ የሚፈልግ
በራሱ ሕግጋት ባይወድ እንኳን በግድ

ተፈጥሮ ያልዳኘው
ወሰን ያልገደበው
ሚዛን ያልጠበቀ
መስመር የለቀቀ
ዉሃ ሞልቶ ሲፈስ
እየጠራረገ ሁሉን በማግበስበስ
ይገባል ወደ ወንዝ
ፍሰቱን ለማገዝ
ከዚያ በኋላማ ኃይሉን አጠናክሮ
ፏፏቴ በመስራት ሽቅብ ተፈናጥሮ
ይተፋል ሞገዱን
በማርጠብ ዙሪያውን

የማይቻል የለም ለሰው የሚሳነው
ብሩህ አዕምሮና ቅን ልቦና ካለው

የሞገዱን ግፊት
ጥቅሙን ያልተረዱት
ሰጥመው ይቀራሉ
ወይ ይንሳፈፋሉ
እንደ ደረቀ ዛፍ
የሌለው ቅርንጫፍ
ዘዴውን ያወቁት
በዕውቀት የመጠቁት
አገርን በማልማት
ወጥተው ከድህነት
ከተመፅዋችነት
ስደትን እስቁመው
ዜጎችን አጥግበው
ሁሉም በሀገራቸው
ይኖራሉ ኮርተው
በግልፅ ውይይት
አጥፍተው ልዩነት
ተጋግዘው በጋራ ይበለፅጋሉ
ጤናማ ቤተሰብ ይመሰርታሉ
ታሪክ ተረካቢ ትውልድ ያፈራሉ
ሁሉም ጠግቦ አዳሪ ሆነው ይኖራሉ

የማይቻል የለም ለሰው የሚሳነው
ብሩህ አዕምሮና ቅን ልቦና ካለው

ሰላም ካለ በአገር
በጭራሽ አይኖርም የማይቻል ነገር
በትምህርት መበልፀግ
በሀብት መበልፀግ
በሰላም መታደግ
በጤናም መታደግ
ቀና አዕምሮ ካለ
ከሚያዝን ልብ ጋር የተደላደለ
የማይቻል የለም
እያንዳንዱ ዜጋ ከጣረ ለሰላም
ከራስ ጋር መታረቅ
ሃሣብ ሳይሄድ ዕሩቅ
ተጠየቅ ራስን
ተጠየቅ ምላስን
ብሎ በመሞገት
ይገኛል ትርጉሙ የሰላም ምንነት
በሰላም አዉለኝ
ለጎርቤቶቸም ሰላሙን ስጥልኝ
ብሎ ለሚወጣ ወደ ሥራ ሊሄድ
የማይቻል የለም የማይቀና መንገድ
የማይቻል የለም ለሰው የሚሳነው
ብሩህ አዕምሮና ቅን ልቦና ካለው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የሕግ የበላይነትን ሊያስከብር ያልቻለ መንግስት በሕዝብ እምነት ሊጣልበት አይችልም

Next Story

ባዲሱ ዘመን ለሰው ልጅ ህይወት ክብር እንስጥ

Go toTop