በዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳ የስልጤ ተወላጆች የስልጤን ዞን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

August 4, 2020

ኦገስት 5,2020

በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያና ያን ተከትሎ በተፈጠረው ሁኔታ ክቡር የሆነው የሰው ልጆች ሞትና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት የተሠማንን ከፍተኛ ሀዘን እንገልፃለን። ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወትን ላጡ ቤተሠቦች፣ዘመድና ወዳጆች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ መፅናናትን እንለምናለን።

በሌላው ገፅታ ደግሞ የህዝብ ተስፋ የሆነው የህዳሴ ግድባችን የመጀመሪያ ደረጃ የውሀ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ እንገልፃለን።

የስልጤ ህዝብ አኩሪ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነት፣ ሃይማኖትና ጂኦግራፊያዊ አሰፋፈር ያለው ህዝብ ነው። ሆኖም ግን ቀደም ሲል በነበሩት የኢትዮጵያ ነገስታት በከፋፍለህ ግዛው ስርአታቸው በታትነው ይገዙት እንደነበር የሚታወቅ ሀቅ ነው። የኸውም ግማሹን በጨቦና ጉራጌ አውራጃ፣ የተወሰነውን በከምባታና ሃዲያ፣ ቀሪውን ደግሞ በሃይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ከፋፍለው ቋንቋውን ባህሉንና ልማቱን በተገቢው መንገድ እንዳያለማ በማድረግ ለዘመናት ጭቆና ሲደርስበት የኖረ ህዝብ ነው።

በኢትዮጵያ ህግ-መንግስት አንቀጽ 46 ንዑስ አንቅፅ አንድ መሰረት፣የፌደራል መንግስት በክልሎች የተዋቀረ ነው

ክልሎች ደግሞ የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነትና በፈቃድ ላይ በመመስረት ነው በሚለው ድንጋጌ

መሠረት ማንነቱን ለማስወሰን ለረጅም አመታት ሰላማዊና እልህ አስጨራሽ ትግል ታግሎ የተለያዩ በማዕከልም

እንዲሁም በግል እየተወሰነበት የነበረውን ጨቋኝ ጫናዎችንና ውሳኔዎችን በመቃወም ጥያቄውን ወደ ፌዴሬሽን

ም/ቤት በመውሰድ የፌዴሬሽን ም/ቤት በመጨረሻ በሚያዚያ 5/1992 የስልጤ ሕዝብ ማንነት በስልጤ ሕዝብ በራሱ

ሕዝበ-ውሳኔ( ሪፈረንደም) እንዲወስን የተወሰነውን ታሪካዊ ውሳኔ ተከትሎ ፣ የፌደራል መንግስት ከደቡብ ብሔር

ብሔረሰብ ክልል ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ሕዝበ-ውሳኔ በመጋቢት 1993 ዓ.ም 99.9% በሆነ ድምፅ የስልጤ ሕዝብ

የስልጤ ብሔረሰብ መሆኑና የጉራጌ ብሔረሰብ አካል አለመሆኑን አረጋግጧል።

በመሆኑም የስልጤ ሕዝብ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የራሱን ክልል አደራጅቶ ራሱን በራሱ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 46/1 መሠረት መተዳደር ሲገባው በወቅቱ በበላይነት ሲመራ የነበረው (ኢህአዴግ) ለራሱ አገዛዝ እንዲያመቸው መጀመሪያ ክልል 7 ዋና ከተማውን ሆሳዕና አድርጎ ሲከልለው ፣ በመቀጠልም የደቡብ ክልል ናችሁ በአዋሣ ከተማነት ጨምሮ ሲጨፈልቀው ከቆየ በኃላ በደቡብ ክልል ውስጥ የታቀፉት ብሔረሰቦች ባቀረቡት ጥያቄ መነሻነት የስልጤ ህዝብም በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት የራሱን የአስተዳደር ክልል የመመስረት ጥያቄውን በአንክሮ በመጠየቅ ላይ ሲሆን፣ የህዝቡን ፍላጎት ባላገናዘበ የሚደረግ ጥናትም ይሁን የፖለቲካ ውሳኔን ሕዝባችን “አምቤው” ማለትም እምቢ በማለት ስሜቱን በቁጣ እየገለፀ ይገኛል።በዚህም ምክንያት በተለያየ ጊዜያት ከሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የተውጣጡ የሓይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ የዞኑ ሐርዴ (ወጣቶች) ጋር በመሆን የክልልነት ይገባኛል ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ እያቀረቡ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። በመሆኑም እኛ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የምንኖር የስልጤ ተወላጆች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በሐገራችንና በዞናችን በልማት፣

በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የባህል ጉዳዮች የነቃ ተሣትፎ ስናደርግ እንደቆየነው ሁሉ፤ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል በስልጤ የማንነት ጥያቄ ፣ ለወራቤ ሆስፒታል ግንባታ ድጋፍ ፣ለታላቁ የህዳሴ የአባይ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ ፣ በቅርቡም በሳንኩራና በስልጤ ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖቻችን ዕርዳታ እንዲሁም በዚህ ወቅት ደግሞ በኮቪድ-19 ድጋፍ የሃገራችን ችግር ችግራችን ነው በሚል ተቆርቋሪነት ምንም እንኳ እኛም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ብንሆንም ቅድሚያ ለሕዝባችን በማለት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነን ለወገናችን ድጋፋችንን በሰፊው አድርገናል ወደፊትም ከህዝባችን ጎን በመሆን ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።

ሆኖም የዚህ የአቋም መግለጫ መውጣት ዋነኛው መንስዔ የሚከተለው ነው። የደቡብ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ባለበት ሒደት የስልጤ ዞን ም/ቤት በህዳር 2012 በወራቤ ከተማ በመሰብሰብ ክልልነት ይፈቀድልኝ ጥያቄውን ወስኗል። ይሁን እንጂ የተወሰኑ ግለሰቦች ጥያቄውን ከሕዝቡ እምነት፣ ፍላጎት እና ፈቃድ ውጪ ወደ ሌላ አቅጣጫ እየወሰዱት በመሆኑ መላው በዞኑ የሚገኘው ሕዝባችን፣ ከሀገር ውጭ ማለትም በደቡብ አፍሪካ፣በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በዩናይትድ ስቴስ ኦፍ አሜሪካ እና በካናዳ ይህንን ህዝብን እያስቆጣ የመጣውንና እልባት ያላገኘውን የክልልነት ጥያቄ “ሐርዴ አምቤው በል” (ወጣት እምቢ በል) በሚል የጋራ አቋም ተነሳስቶ እየጠየቀ ያለውን ህገ-መንግስቱ የሚፈቅደውን የመብት ጥያቄ የምንደግፍ መሆኑን ለመግለፅ ሲሆን እንደተለመደው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ከጎናችሁ እንደምንቆም አቋማችንን እየገለፅን ይህ ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ የሚመለከታቸው ማንኛውም አካላት የጥያቄውን አንገብጋቢነት በመገንዘብ አሁን እየተካሄደ ባለው የለውጥ ሒደት ላይ አስቸጋሪና ውስብስብ ሁኔታን እንዳይፈጥር በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው በአክብሮት እንጠይቃለን።

ግልባጭ

• ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ (አዲስ አበባ)

• ለፌዴሬሽን ም/ቤት (አዲስ አበባ)

• ለሰላም ሚኒስቴር (አዲስ አበባ)

• ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ( ዋሽንግተን ዲሲ)

• ለደቡብ ክልል ም/ቤት (አዋሳ)

• ለስልጤ ዞን ም/ቤት (ወራቤ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

“ዘንግህን ማወዛወዝ ትችላለህ፡፡አፍንጫየየን መንካት ግን አትችልም፡፡” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Next Story

በአማራ ብሄር ተወላጆች እና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቁም!!!

Go toTop