የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ባለአምስት ነጥብ የተቃውሞ ምክንያቶች ምላሽ ሳይሰጣቸውና መፍትሔ ሳያገኙ፣ የኢትዮጵያውያን ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሕጋዊ ዕውቅና እንዳይሰጠው አሳሰበ፡፡
ኢዴፓ ይህን የተቃውሞ ማሳሰቢያ ያቀረበው ዓርብ ጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ የተቃውሞው ምክንያት ደግሞ ቦርዱ ታኅሳስ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ባስተላለፈው ማስታወቂያ፣ ‹‹ኢዜማ ለሚባለው ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት እንደወሰነ፣ ነገር ግን የሚቃወም አካል ካለ ተቃውሞውን እንዲያቀርብ በጠየቀው መሠረት፤›› ነው ሲል አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ኢዴፓ አምስት የተቃውሞ ምክንያቶችን በመዘርዘር ለኢዜማ ሕጋዊ ዕውቅና እንዳይሰጠው ጠይቋል፡፡ ኢዜማ ሕጋዊ ዕውቅና እንዳይሰጠው ኢዴፓ ለተቃውሞ ያቀረባቸው ምክንያቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ኢዜማ በምሥረታ ላይ በነበረበት ጊዜ ኢዴፓ በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ከስሞ ከኢዜማ ጋር ተዋህዷል በማለት በተደጋጋሚና በተለያዩ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የሐሰት መረጃ ለሕዝብ አሠራጭቷል ሲል የሚከሰው ኢዴፓ፣ ‹‹ኢዜማ ይህ ያሠራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን በይፋ ለሕዝብ ማስተባበያ ሳይሰጥ ሕጋዊ ዕውቅና ቢሰጠው፣ የፓርቲያችንን ጥቅም የሚጎዳ ውጤት ስለሚያስከትል ዕውቅና እንዳይሰጠው፤›› በማለት ኢዴፓ የመጀመሪያ ምክንያቱን አቅርቧል፡፡
ኢዜማ ሕጋዊ ዕውቅና እንዳይሰጠው የቀረበው ሁለተኛ ምክንያት ደግሞ፣ ከፓርቲው ጽሕፈት ቤቶችና ንብረት ርክክብ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ በቂርቆስና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች፣ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ ሰፈነ ሰላም ቀበሌ የሚገኙ የፓርቲውን ቢሮዎች፣ ማኅተም፣ ልዩ ልዩ መዛግብትና ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ በቀድሞ የኢዴፓ አመራሮች እጅ ይገኝ እንደነበር በመጥቀስ ነው፡፡
በዚህም መሠረት፣ ‹‹የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች እስካሁን የፓርቲውን ንብረቶች ያላስረከቡና ‘ክሊራንስ’ ያልወሰዱ በመሆናቸው፣ እነዚህን ንብረቶች ለኢዴፓ አስረክበው ‘ክሊራንስ’ ሳይሰጣቸው እነዚህ ግለሰቦች ከፍተኛ አመራር ሆነው የተመረጡበት ኢዜማ ሕጋዊ ዕውቅና ቢሰጠው፣ የፓርቲያችን ጥቅም የሚጎዳ ውጤት ስለሚያስከትል ዕውቅና እንዳይሰጣቸው፤›› ሲልም ኢዴፓ የተቃውሞ ምክንያቱን አቅርቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኢዴፓ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅትም የኢዴፓን ሕጋዊ ማኅተም እንደሚጠቀሙና የኢዴፓ መሪ ነኝ በማለት ከቦርዱ ጋር ደብዳቤ እየተጻጻፉ እንደሆነ በማውሳት፣ ‹‹ግለሰቡ ከሕግ ውጪ የሁለት ፓርቲ አመራር ነኝ እያሉ በሚገኙበት በዚህ ወቅት፣ በእሳቸው እየተመራ የሚገኘው ኢዜማ ሕጋዊ ዕውቅና ቢሰጠው የፓርቲያችንን ጥቅም የሚጎዳ ውጤት ስለሚያስከትል ተቃውሞአችንን እናቀርባለን፤›› ሲልም ኢዴፓ ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡
‹‹ኢዜማ በስያሜውና በመመሥረቻ ጽሑፉ ላይ በግልጽ ያስቀመጠውን የማኅበራዊ ፍትሕ የማስፈን ዓላማ በግልጽ ተፃርሮ የቆመ በመሆኑና ወደፊትም ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ለፖለቲካ ሥልጣን ቢበቃ ተመሳሳይ ሕገወጥ ድርጊት በሕዝብና በአገር ላይ ሊፈጸም ስለሚችል፣ ከላይ በጠቀስናቸው ጉዳዮች ላይ ግልጽ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወሰድ ሕጋዊ ዕውቅና እንዳይሰጠው፤›› በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ኢዴፓ ጥቅሙን ለማስከበር በአሁን ወቅት በክስ ሒደት ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስ፣ ‹‹የክስ ሒደቱ ከመጠናቀቁ በፊት ኢዜማ ሕጋዊ ዕውቅና ቢሰጠው፣ ጥቅማችንን የሚጎዳ ውጤት ስለሚያስከትል ዕውቅናውን እንቃወማለን፤›› በማለት መግለጫውን አጠናቋል፡፡
በቀረበው የተቃውሞ ሐሳብ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህን የማድረግ ሥልጣን የላቸውም፡፡ ነገር ግን ተመካክረን ለሚጠይቀን አካል ዝርዝር መረጃ እንሰጣለን፤›› በማለት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ኢዜማ ግንቦት 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ባከናወነው መሥራች ጉባዔ አማካይነት አርበኞች ግንቦት 7፣ ኢዴፓ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ እንዲሁም የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ን ጨምሮ ራሳቸውን ባከሰሙ ሰባት ፓርቲዎች የተመሠረተ ፓርቲ ነው፡፡ በሒደትም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ራሳቸውን አክስመው ፓርቲውን መቀላቀላቸው ይታወሳል፡፡
ሪፖርተር