በአዲስ አበባ የዳቦ እጥረት ተከሰተ
(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ ዳቦ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ እንዳልሆነ ተገለፀ፡፡ የከተማው ነዋሪዎች በየዳቦ ቤቱ ዳቦ ለመግዛት ሲሄዱ ዳቦ አለመኖሩ እየተነገራቸው በተደጋጋሚ እየተመለሱ መሆኑንና ችግሩም እስካሁን እንዳልተቀረፈ ሰንደቅ ጋዜጣ በጥቅምት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል፡፡ እንደጋዜጣው ዘገባ ከሆነ አንዳንድ ዳቦ መሸጫ ሱቅ የሥራ ኃላፊዎችና ባለቤቶች በተገኘው መረጃ መሰረት በዳቦ መሸጫ መንግሥት ከተመነው ዋጋ አንፃር ሲታይ
አንድን ዳቦ ለገበያ በማቅረብ የሚገኘው የትርፍ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ዘርፉ አበረታች አለመሆኑ ተገልፁዓል፡፡ እጥረቱን በተመለከተ ጋዜጣው ያነጋገራቸው በንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ሰይድ፤ የዳቦ ዋጋ ትርፍን በተመለከተ መንግስት ተመኑን ሲያስቀምጥ ያሉትን ወጪዎች ታሳቢ አድርጎ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የተፈጠረውንም የዳቦ እጥረት በተመለከተ ስንዴ በእህል ንግድ በኩል ተገዝቶሀገር ውስጥ ሲገባ መንገድ ላይ በተፈጠረው መዘግየት የተፈጠረ መሆኑን ኃላፊው አመለክተዋል፡፡ ያም ሆኖ እህል ንግድ ከመጠባበቂያ ክምችቱ በማውጣት ለአዲስ አበባም ሆነ ለክልል የዱቄት ፋብሪካዎች እንደተቀመጠላቸው ኮታ እንዲያከፋፍል መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ መንግስት በሀገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በሚል በ 2003 ዓ.ም. በበርካታ የፍጆታ
ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን ከጣለ በኋላ በስተመጨረሻ የሌሎች ተመን ሲነሳ የስኳር፣ የዘይትና የስንዴ ምርቶችን የማከፋፈል ስራ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ውሎ እስከ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ይሁን እስካሁን በስርጭቱ ረገድ በስኳር ላይ ተደጋጋሚ ችግር እየታየ ሲሆን አሁን ደግሞ በዳቦ ስንዴ ላይ ችግሩ እየተንፀባረቀ መሆኑን ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የመጅሊስ እና የዑለማዎች ምክር ቤት የይፍረሱ ክስ ለሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርብ ተገለፀ
(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ እስልምና እና የዑለማዎች ምክር ቤት ይፍረሱ በሚል የቀረበው አቤቱታ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ፤ በድጋሚ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርብ ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ጥቅምት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ባወጣው እትሙ አስነብቧል፡፡
የታሰሩት የኢትዮጵያ ሙስሊም ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ እንደተናገሩት፤ የተጀመረው ክስ ለመስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ድጋሚ ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለውን ለማየት እንደነበር ተናግረው ፤
ጉዳዩ ተብራርቶ በመቅረቡ ለማክሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚሰየም ጋዜጣው ቢዘግብም የማክሰኞ ችሎት ውሎውን በመለከተ ግን ያለው ነገር የለም፡፡ እንደጋዜጣው ዘገባ ከሆነ ፤ ዑለማዎች ምክር ቤት በራሱ በእስልምና ጠቅላይ ጉባዔዎች ስር ያለ በመሆኑ እና የነዚህ የበላይ ደግሞ መጅሊሱ በመሆኑ ዑለማዎች ምክር ቤት የማስመረጥ መብት የለውም የሚለው የክሱ አንዱ ጭብጥ መሆኑን ጠበቃ ተማም መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
እንደጠበቃ ተማም ገለፃ፤ ዑለማዎች ምክር ቤት ምርጫ ያካሄደው የራሱ የሆነ ህጋዊ ሰውነት ሳይኖረው ነው፡፡ ምርጫውን የማካሄድ ስልጣን የዑለማዎች ምክር ቤት ሊሆን አይችልም፡፡ ምርጫው አስመራጭ በሌለበት ሁኔታ ሊደረግ አይችልም፡፡ ለዚህም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣውን ሁሉ በማስረጃነት አቅርበናል በማለት የክሳቸውን ዝርዝር ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀረቡ የክስ ፋይሎች መካከል ፤ ጅሃዳዊ ሃረካትን በተመለከተ በኢቴቪ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ደህንነት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ተከሰው የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ የዘጋቸው ፋይሎች በሰበር ችሎቱ በድጋሚ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ፖሊስ በቦምብ ፍንዳታ ህይወታቸው ያለፈው ሶማሊያውያን አሸባሪዎች ናቸው ሲል መናገሩ ተጠቆመ
(ዘ-ሐበሻ) ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ማዞሪያና ቦሌ ሚካኤል መግቢያ አካባቢ በቦንብ ፍንዳታ ህይወታቸው ያለፈው ሁለት ሶማሊያውያን ሽብርተኞች መሆናቸውን ማረጋገጡን፤ የፌደራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ማስታወቁን ሪፖርተር በጥቅምት 6 ቀን 2006 ኣ.ም. እትሙ ዘግቧል፡፡
የአንድ ግለሰብ ሰርቪስ ቤት ተከራይተው ከነበሩት ሶማሊያውያን መካከል አንደኛው ከ20 ቀናት በላይ የቆየ ሲሆን፤ ሌላኛው ፍንዳታው ከመድረሱ በፊት ከሁለት ሰዓታት በፊት የደረሰ መሆኑን ግብረኃይሉ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡ ሽርተኛ የተባሉት ሶማሊያውያን ካፈነዱት ቦምብ በተጨማሪ መጠናቸው ያልተገለፀ ቦምቦችና አንድ ሽጉጥ ከሁለት ካርታ ጥይት ጋር መገኘቱን፣ የፈንጅ ማቀጣጠያና የአደጋ መከላከያ ጃኬቶች ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ማሊያና ቀበቶዎች መገኘታቸውም ተጠቁሟል፡፡
እንደሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ከሶማሊያውያኑ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ 3 ተጠርጣሪዎችና የቤቱ አከራይ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡ የአደጋውን መንስኤና
አጠቃላይ ስለነበረው ሁኔታ ፖሊስ መረጃ እያሰባሰበ በመሆኑ ዝርዝ መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይህደጎ ስዩም ለሪፖርተር የገለፁ ቢሆንም፤ የፌደራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ግለሰቦቹ ሽብርተኛ መሆናቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደጠቆሙት ከሆነ የፍንዳታው ቅንብር ኢህአዴግ ቀደም ሲል ልክ ጨዋታው ሲያልቅ በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ካሸነፈ ስታዲየም አካባቢ በማፈንዳት የድርጊቱ
ፈፃሚዎች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ተቃዋሚዎች እና የኃይማኖት አክራሪዎች ናቸው ለማለት አቅዶት የነበረውን ሆን ብሎ ግቡ ሳይሳካ ሲቀር በበሌላ ቦታ ማፈንዳቱን የከዚህ ቀደም የኢህአዴግን ድርጊት እያመሳከሩ ያስታወሱ
አልታጡም ፡፡ በተለይም በፍንዳታው ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ የታሰሩ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ላይ መንግስት የወሰደውን እርምጃ እንዲደግፉና እንዲፈጡ የሚጠይቀውን ጫና በመግታት እውቅና ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ከኢህአዴግ ውስጥ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡