በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ800 በላይ መኖሪያ ቤቶች መፍረሳቸውን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ ቤቶቹ እንዲፈርሱ የተደረጉት ለመንገድ ግንባታ ተብሎ ነው ቢባልም፣ አብዛኛዎቹ የቤት ባለቤቶች ግን ተገቢው ካሳ እና ምትክ ቤት እንዳልተሰጣቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቤቶቹን የማፍረስ ዘመቻውን የተወጣው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሲሆን፣ ባለስልጣኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊያፈርሳቸው ያቀዳቸው ቤቶች ቁጥር 2 ሺህ ነበር፡፡
File Photoበ2009 በተደረገው ቢዚሁ የማፍረስ ዘመቻ በአብዛኛው ተጎጂ የሆኑት ወይም ቤታቸው የፈረሰባቸው በመንገድ ዳር የነበሩ የቤት ባለቤቶች ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከመንገድ ገባ ብለው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡ ቤታቸው እንዲፈርስባቸው ከተደረጉ ሰዎች ውስጥ የካሳ ተብሎ ገንዘብ የተሰጣቸው ቢኖሩም፤ የተሰጣቸው ገንዘብ እና የመኖሪያ ቤታቸው ደረጃ ግን በፍጹም የሚመጣጠኑ እንዳይደሉ ተጎጂ ነን ባዮች ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ ዘረፋ እና ሙስና ከሚፈጸምባቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ለመንገድ ግንባታ ተብሎ ቤታቸው ለሚፈርስባቸው ነዋሪዎች ደረጃውን ያልጠበቀ ካሳ በመስጠት የሚታወቀው ባለስልጣኑ፣ በዚህ ድርጊቱም ብዙዎችን ቤት አልባ አድርጎ እንዳስቀረ ከዚህ ቀደም ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሰበቦች ቤታቸው ፈርሶ የትም የወደቁ ሰዎች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ለህንጻ ግንባታ፣ ለመንገድ ፕሮጀክት፣ ለፋብሪካ ግንባታ እና መሰል ጉዳዮች ቤታቸው የፈረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ያለ በቂ ካሳ እና ምትክ መኖሪያ ቤት የትም ወድቀው ቀርተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ደግሞ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ፣ ለስኳር እና ለማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ተብሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ጎዳና ላይ መውደቃቸው ከዚህ ቀደም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በ2009 ያፈረሳቸው ከ800 በላይ ቤቶች፣ ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች በከተማዋ ያፈረሷቸውን ቤቶች አያጠቃልልም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ከግንባታ ጋር በተያያዘ በ2009 ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን አፍርሷል፡፡
(BBN News – 10/21/17)