70 ተማሪዎችን የያዘ የተማሪዎች ሰርቪስ ቦሌ ሰሚት ድልድይ ላይ ተገለበጠ

December 8, 2016

ሸገር ራድዮ እንደዘገበው – (ወንድሙ ኃይሉ)

በአ.አ ቦሌ ሰሚት ድልድይ ላይ ዛሬ ጠዋት 70 ተማሪዎችን የጫነ የሳፋሪ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ሰርቪስ ተገለበበአዲስ አበባ ቦሌ ሰሚት ድልድይ ላይ ዛሬ ጠዋት 70 ተማሪዎችን የጫነ የሳፋሪ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ሰርቪስ ተገለበጠ::በመኪና ውስጥ ከነበሩ 70 ተማሪዎች አስሩ ከባድ የአካል ጉዳት ገጥሟቸው ወደ ሚኒልክና የካቲት ሆስፒታሎች እንዲሁም ወደ ኮተቤ ጤና ጣቢያ ለህክምና ተወስደዋል፡፡

የአካል ጉዳት ያጋጠማቸውን ተማሪዎች ወደ ህክምና የወሰደው የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን አንቡላንስ ነው ተብሏል፡፡

የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሸገር ሲናገሩ ዛሬ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ30 በተገለበጠው መኪና ውስጥ የነበሩትና መጠነኛ መጫጫር ያጋጠማቸው ስልሣዎቹ ተማሪዎች ደግሞ ወደየቤታቸው ተመልሰዋል፡፡

የሳፋሪ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለቤት አቶ እዬብ አየለ መኪናውን በኮንትራት አምጥተነው ለሰርቪስ አገልግሎት የምንጠቀምበት ነው ያሉ ሲሆን ከአደጋው በኋላ አሽከርካሪው የቴክኒክ ችግር አጋጥሞኝ ነበር በማለት ነግሮኛል ብለዋል፡፡

በሌላ የአደጋ መረጃ ትላንት በየካቲት 12 ሆስፒታል የተነሣ የእሳት አደጋ መድኃኒቶችን አቃጠለ ተባለ፡፡

ከእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለሸገር ሲናገሩ ትላንት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ውስጥ ባለው የካቲት 12 ሆስፒታል የመድኃኒት መጋዘን ላይ የተነሣው እሣት የዋጋ ግምታቸው ለጊዜው ያልታወቀ የተለያዩ መድኃኒቶችን አጥፍቷል ብለዋል፡፡

ትላንት ከቀኑ 7 ሰዓት ከ50 ደቂቃ በሆስፒታሉ የመድኃኒት መጋዘን ላይ የተነሣውን እሣት ለማጥፋት በሁለት ከባድ መኪኖች ስድስት ሺ ሌትር ውሃ ተጠቅመናል ከተሰማሩት 13 የአደጋ ተከላካይ ሠራተኞቻችን ውስጥ አንዱ በእሣቱ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞታል ያሉት አቶ ንጋቱ እሣቱን ለማጥፋት አርባ ደቂቃዎች ፈጅቶብናል በማለትም ነግረውናል፡፡

የእሣት አደጋው መንስኤ ምንድነው የሚለውን ለማወቅ ፖሊስ በማጣራት ላይ ነው ተብሏል፡፡

 

Previous Story

እስራኤል ኤርትራውያን ስደተኞችን ከግዛቷ አስወጣች

Next Story

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከታሰረበት ዝዋይ እስር ቤት የለም መባሉ ቤተሰቦቹን ግራ አጋብቷል

Go toTop