እስራኤል ኤርትራውያን ስደተኞችን ከግዛቷ አስወጣች

December 2, 2016

BBN News: የእስራኤል መንግስት በሀገሩ የሚገኙ ስደተኞችን ማስወጣቱን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ አንድ መረጃ እንደገለጸው ከሆነ፣ በእስራኤል የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ እንዲሔዱ የተደረገ ሲሆን፣ ስደተኞቹ ከእስራኤል ሲወጡም በነፍስ ወከፍ 3 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዩጋንዳና ሩዋንዳ ስደተኞቹን ከእስራኤል ተቀብለው በሀገራቸው ለማስተናገድ ፈቃደኛ የሆኑት አስቀድሞ ከአገሪቱ ጋር በገቡት ውል መሠረት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ስደተኛ ኤርትራውያኖቹ ከእስራኤል እንዲወጡ ከመደረጋቸው በፊት ሶስት ምርጫ እንደተሰጣቸው የገለጹት መረጃዎች፣ ምርጫዎቹም ወደ ሶስተኛ ሀገር መሻገር፣ እዛው በእስራኤል በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረግ እና በሶስተኛነት ደግሞ ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ እነዚህ ሶስት ምርጫዎች ከቀረቡላቸው ኤርትራውያኖች አብዛኞቹ ወደ ሶስተኛ ሀገር መሔድን ምርጫው አድርገዋል ተብሏል፡፡

የእስራኤል ሥነ ሕዝብና ኢሚግሬሽን ቃል አቀባይ ሰቢን ሃዳድ ከሁለት የአፍሪካ አገሮች ጋር ስደተኞችን ለማስወጣት ሀገራቸው ስምምነት ማድረጓን ዘገባዎች አስረድተዋል፡፡ እንደ ሚዲያዎቹ ዘገባ ከሆነ ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ በፈጸሙት ስደተኞችን የመረካከብ ሒደት በምላሹ ከእስራኤል የጦር መሣርያ እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉ በሶስቱ ሀገራት መካከል የተደረሰውን ምስጢራዊ ስምምነት ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች አስረድተዋል፡፡ ከእስራኤል ወደ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተላኩት ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ እስራኤል የገቡት ከባዱን የሰሃራ በረሃ ለወራት በማቆራረጥ ሲሆን፣ በእስራኤልም ለብዙ ዓመታት መቆየተቻውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Previous Story

የመደራጀት መብት ግዴትም አለበት (ይገረም አለሙ)

Next Story

70 ተማሪዎችን የያዘ የተማሪዎች ሰርቪስ ቦሌ ሰሚት ድልድይ ላይ ተገለበጠ

Go toTop