መንግሥት የፈረመው ስምምነት ጥራት የሌላቸው የቻይና ምርቶች እንዲገቡ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ

May 29, 2014

ሪፖርተር

‹‹በትራንስፎሜሽኑ  ዘመን የዓለም የንግድ ድርጅትን አንቀላቀልም›› አቶ ከበደ ጫኔ፣ የንግድ ሚኒስትር

መንግሥት ከዓመታት በፊት ከቻይና ጋር የተፈራረመው የንግድ ስምምነት የጥራት ደረጃቸው የወረዱ ምርቶች ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ምክንያት መሆኑን የንግድ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ገለጹ፡፡

የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለፓርላማው ባለፈው ማክሰኞ ባቀረቡበት ወቅት፣ ከፓርላማ አባል የቻይና ምርቶችን የጥራት ጉድለት የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

‹‹ጥራታቸው የጎደለ የቻይና ምርቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት ምክንያት ባለሀብቶች በዝቅተኛ ዋጋ ጥራታቸው የወረደ ምርቶችን ስለሚያዙ ነው፡፡ ይህንን ለመቆጣጠር ምን እየተደረገ ነው?›› በሚል ከፓርላማው አንድ አባል ለቀረበ ጥያቄ፣ የችግሩ ምንጭ የተጠቀሰው አለመሆኑን በመግለጽ መንስዔው መንግሥት ራሱ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች ጥራታቸው የተጓደለ ነው የተባለው ትክክል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የቻይና ምርት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የቻይና የደረጃዎች ባለሥልጣን ደረጃውን ከፈተሸ፣ ኢትዮጵያ እንደፈተሸች ተቆጥሮ ምርቱ ወደ ኢትዮጵያ ይግባ የሚል ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል አለ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተመሳይም ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና የሚላኩ ምርቶች በኢትዮጵያ የደረጃዎች ባለሥልጣን ፍተሻ ከተደረገበት የቻይና ባለሥልጣን እንዳደረገው ይቆጠራል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ይህንን በገለጹበት ወቅት የፓርላማው አባላት የተቋውሞ ጉርምርምታ አሰምተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ይህ ስምምነት እየጎዳን እንደሆነ ተደርሶበታል፤›› ብለው፣ ስምምነቱን ለማሻሻል በአሁኑ ወቅት ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መገባደጃ ላይ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን ትቀላቀላለች የሚል ዕቅድ መኖሩን በመጠቆም ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንዲያብራሩ ተጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም በተባለው ጊዜ ውስጥ የዓለም የንግድ ድርጅትን ኢትዮጵያ እንደማትቀላቀል ገልጸዋል፡፡

‹‹በዕቅዱ ዘመን የንግድ ድርጅቱ ለመቀላቀል ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ ውስጥ ስንገባ ግን ውስብስብ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ብለዋል፡፡

በሸቀጦች ንግድ ላይ ከ130 በላይ ጥያቄዎች ከአባል አገሮች መነሳቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ ለቀረቡ ጥያቄዎች ተገቢው ማብራሪያ በመሰጠቱ ተቀባይነት እንዳገኘ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቀረቡት ጥያቄዎች ደግሞ የአገሪቱን የአገልግሎት ዘርፍ ማለትም የባንክ፣ የቴሌ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የመሳሰሉት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ይህንን የአገልግሎት ዘርፍ ወደ ግል እንድናዘዋውር ግፊት እየተደረገብን ነው፤›› የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ቆም ብሎ ማሰብን መርጧል፤›› ብለዋል፡፡

በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እንዴት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሆኑ የሚለውን ሒደት መንግሥት እያጠና እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ለግብዓትነትም ቻይና የድርጅቱ አባል ለመሆን በርካታ ዓመታት እንደፈጀባትና አባል የሆነችውም በኢኮኖሚ አቅሟን ካፈረጠመች በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዓለም የንግድ ድርጅት የአገልግሎት ዘርፉን በአሁኑ ወቅት ወደ ግል ይዞታ ባይዘዋወርም ወይም ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ባይሆንም መንግሥት መቼ ለመክፈት  እንደሚፈልግ እንዲያሳውቅ መጠየቁን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቆም ተብሎ ማሰብ ተገቢ መሆኑ በመታመኑ፣ የዓለም የንግድ ድርጅት ሕጎች ከኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ፖሊሲዎች ጋር ያላቸውን መጣረስና መስማማት የመለየት ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Previous Story

አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለማግኘት ያሰቡ ግለሰቦች ሁለት ሚሊዮን ብር መዘረፋቸው ተጠቆመ

Next Story

ልማታዊ ፓትርያርክ (ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ)

Go toTop