አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለማግኘት ያሰቡ ግለሰቦች ሁለት ሚሊዮን ብር መዘረፋቸው ተጠቆመ

May 29, 2014
 ታምሩ ጽጌ
ethiopianreporter
በአዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ በሕገወጥ መንገድ የውጭ አገር ገንዘቦችን የሚዘረዝሩ ግለሰቦች፣ አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለማግኘት የማያውቋቸው ግለሰቦች ዘንድ ሄደው ሁለት ሚሊዮን ብር መዘረፋቸው ተጠቆመ፡፡

በዕለተ ሰንበት እሑድ ግንቦት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የስልክ ጥሪ የደረሳቸው ግለሰቦች ስለሚያገኙት ሥራና ትርፍ እንጂ ሊገጥማቸው ስለሚችለው ችግር አለማሰባቸውን የገለጹት ምንጮች፣ በደረሳቸው የስልክ ጥሪ ‹‹አንድ መቶ ሺሕ ዶላር አለን›› ያሏቸው ግለሰቦችን ማንነት ሳይሆን፣ የሚገኙበትን ሥፍራ ብቻ መጠየቃቸውን አውስተዋል፡፡

በእጃቸው አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ቀርቶ ምንም ነገር ያልያዙት ግለሰቦች ያሉበትን ቦታና የያዙትን የተሽከርካሪ ዓይነት ሲነግሯቸው፣ ተዘራፊዎቹ ግለሰቦች ሁለት ሚሊዮን ብር ይዘው ለመድረስ ጊዜ እንዳልፈጀባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸክመው አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ለመግዛት የሄዱት ግለሰቦች የጠበቃቸው አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ሳይሆን መሣሪያና ከፍተኛ ማስፈራሪያ በመሆኑ፣ ምንም ሳያንገራግሩ ሁለት ሚሊዮን ብራቸውን እንዳስረከቡ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

የደረሰባቸውን ተጨማሪ በደል መግለጽ ያልፈለጉት ተዘራፊዎች፣ የተንቀሳቀሱበት ጉዳይ ሕገወጥ ቢሆንም ገንዘቡ ሁለት ሚሊዮን ብር በመሆኑ ያዋጣናል ወዳሉትና የመጀመሪያው የሕግ ማስከበሪያ ቦታ ወደሆነው ፖሊስ ማምራታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሆኑትን ሁሉ ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡት ተዘራፊዎቹ፣ የዘራፊዎቹን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲገልጹ በፖሊስ ሲጠየቁ፣ መሣሪያ የያዙና ፈርጣማ አቋም ያላቸው መሆናቸውን  በዝርዝር ማስረዳታቸውን ምንጮች አክለዋል፡፡

ጉዳዩን ይዞ ሁለት ሚሊዮን ብር ዘርፈው የጠፉትን ግለሰቦች እያፈላለገ ነው የተባለውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም፡፡

Previous Story

ጎንደር – ክፍል ሦስት (ሥርጉተ ሥላሴ)

Next Story

መንግሥት የፈረመው ስምምነት ጥራት የሌላቸው የቻይና ምርቶች እንዲገቡ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ

Go toTop