ወጣቱ ኢትዮጵያዊ አለም አቀፍ ተሸላሚ ለመሆን የወገኖቹን ድምፅ ይፈልጋል፡፡ ኤስ ኦ ኤስ በኢትዮጵያ ብቻ በ7 ከተሞች የህፃናት መንደሮችን በመገንባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላጅ አልባ ህፃናትን የሚረዳ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ታዲያ በዓለም ዙሪያ በድርጅቱ ያድጉ ከነበሩ ህጻናት ራሳቸውን ችለው ለሌሎችም ለመትረፍ የቻሉ ወጣቶችን በማወዳደር በየጊዜው ይሸልማል፡፡ ሽልማቱንም የሚያደርገው በኤስ ኦ ኤስ ድህረ¬-ገፅ ላይ በሚደረግ የህዝብ ምርጫ ሲሆን የዘንድሮው ኢትዮጵያዊ እጩ ሰኢድ ኑርዬ ነው፡፡ ሰኢድ ኑርዬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በርሃብ፣ በሱስና ጉስቁልና ሂወቱን ይመራ የነበረ ወጣት ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት በከተማ ውስጥ የልብስ ስፌት ሱቅ በመክፈት በ38 ዓመቱ የተዋጣለት ባለሀብት ለመሆን የቻለ ወጣት ነው፡፡
ሰኢድ ከራሱ አልፎ በስሩ ችግረኛ ወጣቶችን በማሰልጠንና የራሱን ተሞክሮ ለሌሎች ኢትዮጰያዊ ወንድሞቹ በማካፈል ላይም ይገኛል፡፡ እ.ጎ.አ 1981 ኤስ ኦ ኤስን ከመቀላቀሉ አስቀድሞ ሰኢድ በጊዜው በሰሜናዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ከተነሳው ድርቅ ከተረፉት ውስጥ ነው፡፡
ከዚያም በኃላ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በተለያዩ ሱሶች ተጠምዶ የድህነት ኑሮን ሲገፋም ቆይቷል፡፡ በኤስ ኦ ኤስ በተሰጠው የልብስ ስፌት ሞያ ስልጠናና ከስልጠናው በኋላ በተሰጠችው የስፌት መኪና በመነሳት አሁን ባለ 2 የልብስ ስፌት ሱቅና በስሩም 4 ሰራተኞችን ቀጥሮ ለማሰራት የቻለ ታታሪ ወጣትም ሆኗል፡፡ ሰኢድ በጥንካሬውና በአላማ ፅናቱ ለሌሎች ወጣቶችም ተምሳሌት ለመሆን የቻለ ወጣት በመሆኑ ነው ከ8 አለም አቀፍ ተፎካካሪዎቹ ጋር ለሽልማት የታጨው፡፡ በድረ ገፅ በሚሰጠው ድምፅ እስካአሁን ከኢትዮጵያ አነስተኛ ድምፅ ነው የተሰጠው፡፡ ሰኢድ ኑርዬ የሀገራችን ወጣቶችን በመወከል ለሚያደርገው ውድድርም ድጋፋችንን ልንሰጠው ከቻልን ሊያሸንፍ የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡
ሰኢድ ኑርዬን ለመምረጥ የሚያስችለውን ሊንክም እነሆ :-
http://www.sos-childrensvillages.org/about-sos/hermann-gmeiner-award-2014