Sport: ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) በወቅታዊው የኢትዮጵያ እግርኳስ ጉዳይ ይናገራል – “የተዘራው ነው የታጨደው”

May 27, 2014

ከገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

ጨዋታው አክራ ላይ ነበር እንዴ? – የ2006 የእግር ኳስ በጀት መዝጊያችን እንዴት ነበር? – የተዘራው ነው የታጨደው

አመቱን እንዴት ጀመርን?እንዴት እያገባደድን ነው ?የሚለውን ነገር ስናይ አታውቁትም ብዬ ሳይሆን ለማስታወስ ነው የምነግራችሁ፡፡ዘንድሮ ያደረግነው ኢንተርናሽናል ውድድር እንዴት ነበር?፡፡ከሀገር ውጭ ያለውን ትተን አዲስ አበባ ያደረግነውን ጨዋታ ስናይ ጥቅምት 3 ከናይጀሪያ 2ለ1 ተሸነፍን አመቱን በዚህ ጀመርን፤በክለብ ደደቢት በቱኒዝያው ሴፋክሲያን 2ለ1፤መከላከያ በኬንያው ሊዮፓርድ 2ለ1፤ወጣት ቡድን በደቡብ አፍሪካ 2ለ0፤ሴቶቹ በጋና 2ለ0 ተሸነፉ፡፡እዚህ በዚህ አመት ደጋፊው ሽንፈት የሚጎነጭበት አመት ተብሎ በስፖርት ካላንደር የሰፈረ ይመስል አንድም ማሸነፍ ጣልቃ ሳናስገባ በመደዳ እየተሸነፍን እዚህ ደረስን፡፡የሚገርመው ‹‹ማች እናድርገው…››አይነት ሁሉም ሽንፈት ሁለት ጎል ነው ማለቂያው፡፡በዚሁ አመት በደርሶ መልሱ ዘጠኝ ጨዋታ አድርገን ዘጠኙንም ተሸነፍን፡፡ ያገባነው ሶስት ሲሆን የተቆጠረብን 18 ግብ ነው፡፡ ክረምት ነው፡፡ የበጀት መዝጊያ ነው፡፡የ2006 የአዲስ አበባ ውጤታችንን ስናይ ይሄን ይመስላል፡፡ሂሳባችን አወራርደን ትርፍና ኪሳራችን ይሄን ሲመስል ጉዳዩ ደግሞ በረጅም አመት የሄድንበትን ደካማ ውጤት እዚህ ድረስ ተከትሎን የበለጠ እያዳከመን እንደመጣ ያሳያል፡፡ እየተበለጥን የምንሸነፈው በአጨዋወት ስህተት እንደሆነ እየታወቀ አሰልጣኞቹ ‹‹ብንሸነፍም ከዚህ ነገር አንወጣም›› የሚል እልህ ያለበት ነገር ይመስላል፡፡ ይህ ነገር እነሱን(ሙያቸውን)እንዲሁም ሀገርን እየጎዳ በተጨማሪም የስፖርት ቤተሰቡን ሞራል እያናጋው እንደመጣ ልብ የተባለለት አይመስልም፡፡…………
እሁድ እለት ወጣት ቡድናችንና ከሀገር ውጭና እንስቶቹ በሜዳችን ግብ ሳይስቆጥሩ ተሸንፈው ወጡ፡፡በተለይ እንስቶቹ አክራ ላይ እየተጫወቱ ያለ ይመስል ነበር፡፡ ጋና ኳስ እስከዚህም ናቸው(የኛመጥፋት እነርሱን አጎላቸው) ግን በቅብብል በለጡን፡፡የምዕራብ አፍሪካ ቡድን እንዲህ በኳስ ያውም በሜዳችን በልጦ ማሸነፉ ያልተለመደ ነው፡፡

…..እነርሱ ብዙ ኳስ ቶሎ ቶሎ ያገኙ ነበር፡፡ ኳሱ ነጥቀውን ሳይሆን እኛ እየጠለዝን በነጻ የምንሰጣቸው ነው ፡፡እኛ የምንሰጣቸው ደግሞ ስለማንይዘው ነው፡፡የማንይዘው አሰልጣኙ የመረጠው አጨዋወት ይሄን ማድረግ ስለማያስችል ነው፡፡የተበለጥነው በልጆቹ ችሎታ ማነስ አይደለም፡፡ልጆቹ ይችላሉ ነገር ግን የኛን ልጆች ችሎታ ማዕከል ያደረገ ስልጠና ያለመሰጠቱና ስልጠናውን ተከትሎ የተመረጠው አጨዋወት ለጋና የተሻለ ብልጫ እንዲይዝ ስላመቸው ነው፡፡በተለይ ከእረፍት በፊት እኛን ሜዳችም ላይ አስገብተውን ነበር የያዙት፡፡ ተመልካቹ ‹‹ወጥታችሁ ተጫወቱ›› ቢልም በምን ይውጡ?፡፡መውጫቸው በአሰልጣኛችን ተነጥቋል፡፡ከፊት አንድ ሰው ነው ያቆምነው፡፡ረሂማ ብቻ፡፡እርሷ በሁለት ተከላካይ ተይዛ በረጅሙ እየተጣለላት ማምለጫ አጣች፡፡ብቻ ለብቻ ስንገናኝ እነርሱ እንደሚበልጡ እየታወቀ በሁለት ተጨዋች ለተያዘች ልጅ እንዴት በሚጣል ኳስ እንጠቀማለን?ኳሱ በረጅሙ ሲጣል የወደቀውን ቀድሞ ለመውሰድ በፍጥነት መሮጥ ያስፈልጋ፡፡ ኳሱ ከመጣሉ በፊት እነርሱ ቀድመው እንደሚያገኙት እየታወቀ በረጅም መጣሉ አስገራሚ ነበር፡፡ለረሂማ በረጅም ይጣልና ስትነጠቅ ጋናዎች ከረሂማ ጀርባ ተደራጅተው ነበር የሚመጡት፡፡ ምክኒያቱም በረሂማና በኛ አማካይ መካከል ርቀት ነበር፡፡ርቀቱን የፈጠረው የተመረጠው ነገር ነው፡፡ቡድናችን በትሬኒንግ ላይ የሰሩትን ነው ሜዳ ላይ ያሳዩት ፡፡የተዘራው ነው የታጨደው፡፡የልጆቹን ችሎታ መነሻ ያደረገ ነገር ቢዘራ ኖሮ እሱ ሲታጨድ ምርት ይኖረው ነበር፡፡አሁንግን አጨዋወቱ እንክርዳድ ሆኖ……

……ሰልጣኙ በተለያየ ጊዜ በኢንተርናሽናል ውድድር ይሄን አጨዋወት አይቶታል አዲስ አበባ ላይ እንኳን በሶስት መስክ ታይቷል፡፡ በክለብ በ1995 ጊዮርጊስን ይዞ በሩዋንዳው ራዮን እዚህ 3ለ1 ተሸነፈ፡፡ተበልጦ፡፡ በብሄራዊ በ1996 በማላዊ 3ለ1 ተሸነፈ ፡፡ተበልጦ፡፡በሴቶች 2ለ0 ተሸነፈ፡፡ተበልጦ፡፡ሶስቱንም ጨዋታ አዲሰ አበባ ላይ በተመሳሳይ ብልጫ ሲሸነፍ የያዘውን ስልጠና መርምሮ መፍትሄ ሊወስድ ይገባል፡፡አሰልጣኙ ምንም ምክንያት ማቅረብ የለበትም፡፡ማለት ያለበት‹‹ይሄ አጨዋወት አያዋጣም ስለዚህ ወደ ሚያዋጣው መሄድ አለብኝ››ማለት አለበት፡፡ይሄን ካለ ወደ ለውጥ ይመጣል፡፡ እራሱንም አሻሽሎ ቡድኑንም ከውርደት ያተርፋል፡፡ለሽንፈት ምክንያት ከተደረደረ ግን ነገም ይሄን ነገር እንደምናይ ጥርጥር የለውም፡፡….የእሁዱን ሽንፈት እንርሳና ለመልሱ ምን እናድርግ ወደሚለው ነገር ብንሄድ ይሻላል፡፡ለመሆኑ አሰልጣኙ ምን አስቧል?፡፡ተጨዋች ለመቀየር?እሁድም ተጨዋች ቀይሮ አስገብቶ ለውጥ የለም፡፡ለጊዜው አሰልጣኙ በመረጠው አጨዋወት ስላልቻለ እድሉን ለልጆቹ ይስጣቸው እነርሱ በሚችሉት መንገድ ይጫወቱ፡፡

አሰልጣኙ ባለፈው ከካሜሮን እና ከናሚቢያ ጋር ጎል ባለማስቆጠራቸው የአጨራረስ ችግር ነው ብለው መግለጫ ሰጡ፡፡ነገር ግን ችግሩ የአጨራረስ አይደለም የአጀማመር ነው፡፡ አጨራረሱ የአጀማመሩ ውጤት ነው፡፡ አጀማመሩ በረጅም ኳስ ከሆነ አጨራረሱ የተቦጫጨቀና በግርግር ነው የሚሆነው፡፡ አጀማመሩ በጥለዛ እንደሆነ አይተናል፡፡ በጥለዛ የተጀመረ አጨራረሱ እንዴት ነው የሚሆነው፡፡ አጨራረሱን ለማሳመር አጀማመሩን በቡድን ስራ ውስጥ ማሰገባት ነው፡፡ አጀማመሩ በጥለዛ በመሆኑ አጨራረሱ ረሂማን መንገድ ላይ አስቀራት፡፡ አጀማመሩ በረዳት ቢሆን አጨራረሱ ላይ 6 እና 7 ሰው ጎል ጋር ስለሚደርስ ለማስቆጠር ብዙ አማራጭ አለው፡፡

1 ተመልካቹን ኑ ና ደግፉን ይላሉ፡፡ ሊደግፍ መጥቶ የጋናን ሀይለኛነት አምኖ በሀገሩ ተበልጦ ሲወጡ በማየቱ ‹‹ለዚህ ነው የጠሩን?›› አይነት በብሽቀት ነው የወጣው፡፡ለነገሩ ባይጠሩትም ተስፋ ሳይቆርጥ እየደገፈ ነው፡፡ግን ቢያንስ ቢሸነፍም በጨዋታ መብለጥ የሚችልበትን ነገር አላዘጋጁለትም፡፡ይሄ ስልጠናና ስልጠናውን ተከትሎ የተመረጠው አጨዋወት ሁሌም እኛን የሚያዋርድ መሆኑ እየታወቀ በዚህ መንገድ ሰርተው ኑ ና ደግፉን ብሎ መጥራት ተገቢ አይደለም፡፡

2 ፌዴሬሽኑ በቂ ጊዜ ሆቴል አስቀምጧል ፡፡ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ አዘጋጅቶለታል፡፡ሁሉን ነገር አሟልቷል፡፤ይሄ ባይሟላ ኖሮ ለሽንፈቱ እንደ ችግር ይነሳ ነበር፡፡ድጋፍ ሳይደረግም ተደርጎም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡የሚገርመው ሶስቱም ጨዋታ አንድም ግብ አላስቆጠረም፡፡ ሁለቱን እዚህ መጫወቱን አትርሱ፡፡270 ደቂቃ ተጫውተው ግብ ያለማስቆጠራቸው ውሏቸው እኛ ሜዳ እንደነበረ፡፡እዚያው ውለው እዚያው የሚያድሩ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡

3 በዚሁ እለት ወጣት ቡድኑ በደቡብ አፍሪካ ተሸንፎ ወጣ ጨዋታውን በሬድዮ ተከታተልኩ‹‹የደቡብ አፍሪካ አጥቂዎች አልፈው መጡ …አደገኛ ነው …ሳቱ››እንዲህ እያለ ጨረሰ፡፡ቡድኑን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ያሰራው ባሪቶ ነው፡፡ጨዋታውን የሚያስተላልፈው ጋዜጠኛ‹‹ባሪቶ በረጅም እንዲጫወቱ ነው የመከሩት››እያለ ሲናገር ነበር፡፡አዲስ አባባ ላይ ሴቶቹ በረጅም ተጫወቱ ፡፡ደቡብ አፍሪካ ላይ በረጅም ተጫወቱ ፡፡ሁለቱም ኳሶች በደቡብ አፍሪካና በአዲስ አበባ አየር ላይ ይተያዩ ነበር(ሀይ !!እንዴት ነው…ፒስ ነው…አይነት)፡፡ባሪቶን በወጣት ቡድን ረጅም ኳስ ካየነው፡ለብሄራዊ ቡድም ይሄው ነገር እንደሚጠብቀን ማወቅ አለብን፡፡አሁን ስለብሄራዊ ቡድን ማሰብ አለብን፡፡ እዚሁ ሜዳ በጭቃ ላይ ነው አልጀሪያን የምንገጥመው፡፡የኛ ተከላካይ ለአልጀሪያ አማካይ በረጅም ይሰጥና…በነጋተው መግለጫ ላይ አማካይና አጥቂው አልተናበበቡም…ታክቲካል ዲስፕሊን አልነበሩም….

እሁድ እለት እንስቶቹ እንዴት ለመጫወት፤ምን ለማድረግ እንደፈለጉ ሳይታወቅ ሲነጥቁና ሲነጠቁ ጨርሰዋል፡፡ ቡድናችን በእንቅስቃሴ ጋናን መቋቋም አልቻለም፡ጋና አስቸጋሪ ሆኖ አይደለም ፡፡እነርሱ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለገባን እኛነታችን አጣን፡፡እዚህ ውስጥ ልጆቹን ያስገባው ደግሞ አሰልጣኙ ነው፡፡የኛ ልጆች ከሜዳ መውጣት አልቻሉም፡፡እኛ ሜዳ ላይ ተከምረው ጨረሱ፡፡ስብሰባ ለማድረግ የተከማቹ ይመስላል፡፡ለአጥቂዎቹ የሚለካው በረጅም ኳስ ሲሆን የሄደው ኳስ አድራሻ አልነበረውም፡፡በካሜሩን የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደዚህ ነበር የተበለጡት፡፡ አሰልጣኙ ከካሜሩኑ ጨዋታ በኋላ ለሚዲያ ሲናገሩ‹‹ የናሚቢያ ቀን ጥሩ ነበሩ የካሜሩን ቀን ግን ምን እንደነካቸው አላውቅም››አሉ፡፡‹‹ የካሜሩን ቀን ምን እንደነካቸው አላውቅም››የሚለው አሁንም ልዩነቱን መረዳት ያለማውቅ ነው፡፡ካሜሩን እኮ ናሚቢያ አይደለም፡፡የደቡብ አፍሪካ ቡድኖች ለኛ አስቸጋሪ አይደሉም፡፡ወንዶቹም ደቡብ አፍሪካ አካባቢ ያሉትን ይቋቋማሉ፡፡ምዕራብ አፍሪካ ግን ይቸግረናል፡ አጥቂዋ ረሂማ በሶስት ተከላካይ ተይዛ በረጅም እየተጣለላት ስትቸገር ነበር፡፡የኛ ተጨዋቾች ከምዕራብ አፍሪካ ተጨዋቾች ጋር ብቻ ለብቻ ሲገናኙ ችግር እንዳለ እየታወቀ በሶስት ተከላካይ ተይዛ ምን እንድታደርግ ነው የተፈለገው?፡፡ የካሜሩን ቀን ረሂማ ሲጣልላት መቸገሯ እየታወቀ አሁንም ይሄ ሳይታረም የጋና ቀን መደገሙ አሁንም ችግሩን አላወቁም፤ መፍትሄውም እጃቸው ላይ የለም ፡፡ ለመልሱም ጨዋታ ይሄንኑ ስለሚያሳዩን(የአዲስ አበባውን ጨዋታ በፍላሽ አክራ ላይ ወስደው…..) በጊዜ ሊታረም ይገባል፡፡ቡድናችን ባለፈው አመት ታንዛንያን አሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ፡፡በጣም በዙ መሻሻል እንዳለ ተነገረን፡፡ወደ ውድድሩ ሲገባ ግን ታንዛንያን ወይም ታንዛንያ መሰል አልገጠመንም፡፡ከኛ ጋር የተመደቡት ሶስቱም የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ናቸው፡፡እንዴት እንደተበለጥን አይተናላ ዛሬም እዛው ነገር ውስጥ ስለጠበቅናቸው ለሽንፈት ተዳረግን፡፡…….ጋናን በዚህ አጨዋወት ስንገጥም እንደማይቻል ከጅምሩ ይታወቃል፡፡ለምሳሌ ብቻ ለብቻ እነርሱ የተሻሉ እንደሆነ አሰልጣኙ እያወቁ ረሂማ ብቻዋን ሆና ሲጣልላት ነገሩን ተቀብለው ይሄን ሂደት አስቀጥለዋል፡፡ የኛ ልጆች በግል ችሎታቸው ጥሩ ናቸው፡፡ ከምዕራብ አፍሪካ ጋር ሁሌም የምንገጥመው እኛ ባለን ነገር ሳይሆን እነርሱ ጥሩ በሆኑበት ነው፡፡እኛ ጋር ያለውን ነገር በስልጠና አሳድገን ብንገባ ምን ክፋት አለው?፡፡ልጆቹ በጉልበት አልቻሉም፡፡ለጉልበት የሚሆን ነገር ሰርቶ በዚህ ጥሩ ካልሆንን ይሄንን የጉልበት ስራ በሌላ መተካት ነው፡፡ነገር ግን የመጣው አሰልጣኝ ሁሉ አካል ብቃት ላይ ጥገኛ ሆኖ ልጆቹ ብልጫ ሲያስወስድባቸው ነው የሚታየው፡፡ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድናችን በነናይጀሪያና ካሜሩን ሲበለጥ የአሁኑ አሰልጣኝ‹‹የቡድናችን ችግር አካል ብቃት ነው›› ብለው ነበር፡፡እነሆ እርሳቸው ቡድኑን አሁን ተረክበው በአካል ብቃት ሰርተው በአካል ብቃቱ ተበልጠው ነበር የታየው፡፡ አሰልጣኙ እሁድ እለት ልጆቹ ብልጫ ሲወሰድባቸው የአጨዋወት ለውጥ ሳይሆን የግለሰብ ለውጥ በማድግ መፈትሄ ለመፈለግ ሲሄዱ ነው የታየው፡፡እንቀስቃሴው ቢስተካከል ተጨዋቹም በጥፋት አይቀየርም ነበር፡፡የሚሰሩት ትሬኒንግ ጨዋታን የሚወክል አይደለም፡፡ጨዋታን የሚወክል ቢሆን ተጫዋቾቹ ባልተቸገሩ ነበር፡፡እየጠለዙ ሲያሻሙ ነው የጨረሱት፡፡

በማሻማት ውስጥ እነርሱ ተጠቃሚ መሆናቸው በተደጋጋሚ እየታየ ከዚህ ውስጥ መውጣት ይገባቸው ነበር ፡፡ማሻማት እውቀት አይደለም ፡፡ግምት ነው፡፡ ከተሻማ ወይ አገኛለሁ አለበለዚያ አላገኝም፡፡ ግን በመሻማት ውስጥ በጉልበት የተሻለው ሁሌም ተጠቃሚ ነው፡፡የተሻማን ኳስ በዝላይ ወይም የወደቀውን ሮጦ ለማግኘት ፍጥነት ፤የተገኘውንም ለመጠቀም ብቻ ለብቻ ሲገናኙ ጉልበት ያስፈልጋል እናም ማሻመት ዋና ጠላታችን ስለሆነ በተቻለ አቅም ከማሻማት መውጣት ይገባቸው ነበር ፡፡

የሉሲዎቹ አሰልጣኝ በወንዶች በክለብና ብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው ኢንተርናሽናል ውድድር ክፉኛ ብልጫ እየተወሰደበት ታይቷል፡፡ይሄ አጨዋወት ወንዶቹ ጋር እንዳላዋጣ ከታዬ ሴቶቹ ጋር ምን ያደርጋል?፡፡ለምሳሌ አሰልጣኙ በ1994 ጊዮርጊስን ይዞ የኡጋንዳን ክለብ አሸንፎ ነበር፡፡ይሄው ቡደን ያሸነፈበትን አጨዋወት ይዞ በቀጣዩ በቱኒዝያው ኤቷል ደ ሳህል ስምንት ግብ ተቆጥሮበታል፡፡መሸነፉ ችግር የለውም፡፡ግን ምንም ተስፋ ያለው ነገር ማሳየት አልቻለም፡፡ሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ ጋር በዚህ አጨዋት አስቸጋሪ እንደሆነ ተምረውበታል፡፡እንደማያዋጣ ዳሰዋል፤ አሽትተዋል፤ ቀምሰዋል፤አይተዋል፡፡አሰልጣኙ ውጭ ሀገር ኮርስ የወሰዱት በ1972 ዓ.ም ነው(መስኮብ) 34 አመት ከዚህ ስልጠና ጋር ቆይተዋል ለብዙ ጊዜ እድል ተሰጠውቷቸው አይተውታል፡፡ ልዩነቱን እንዴት እንዳልተረዱት ግልጽ አይደለም፡፡ ከዚህ ካልተወጣ ለመጪው አስር አመትም የይሄንኑ እንደሚያሳዩን ጥርጥር የለውም፡፡

…..አሰልጣኙ ትላንት ከጨዋታው በኋላ በሚዲያ ሲናገሩ እንደሰማሁት‹‹አማካዩና አጥቂው ያለመናባባቸው ፤ያለመገናኘታቸው ለሽንፈቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አደርጓል››በሚል አማካይና አጥቂውን ተጠያቂ በማድረግ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ተጫዋቹን የመረጠው ያሰለጠነው፤ያሰለፈው፤እንዲህ ተጨወቱ ብሎ ያዘዘው አሰልጣኙ ስለሆነ ሌላ ቦታ ሳይኬድ ሀላፊነትን ሙሉ ለሙሉ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ የሚገርመው የዛሬ አስር አመት አሰልጣኙ የያዘው ብሄራዊ ቡድን በማላዊ በሜዳው 3ለ1 ሲሸነፍ‹‹አማካይና አጥቂው ባለመቀናጀታቸውና አንዳንድ ልጆች የተሰጣቸውን ሀላፊነት ባግባቡ ባለመወጣታች ተሸንፈናል››አሉ፡፡ ዛሬም የዛሬ አስር አመት አማካይና አጥቂው ባለመቀናጀታቸው ተሸነፍን የሚል ነገር ማድመጡ ያን ያህል አመት-፡

ተመሳሳይ አጨዋወት፤
ተመሳሳይ ስልጠና ፤
ተመሳሳይ አለመቀናጀት፤
ተመሳሳይ ምክኒያት
፤ተመሳሳይ ውጤት
ተመሳሳይ ስህተት

የዛሬ አስር አመት ከማላዊ ጋር ተከላካዩ በረጅም ያወጣል የባለጋራ ተጫዋች አድራሻ የሌለውን ኳስ ያገኝና በዚያ መጥቶ ግብ አስቆጠረ፡፡ዛሬም ተከላካዩ በረጅም ያወጣል በዚህ ኳስ ጥቃት መጣ፡፡ተከላካዩ በረጅሙ ለብቻዋ ላለች ረሂማ ከሰጠ ግንኙነቱ በረሂማና በተከላካዩ ነበር፡፡አማካይ ላይ ያሉት ኳስ በአናታቸው አልፎ ወደ ረሂማ ሲሄድ አንጋጠው ያዩ ነበር፡፡አማካዩ ምንም ተሳትፎ ስላልነበራቸው ወደ ቤት ቢሄዱም ችግር አልነበረውም፡፡ ተቆርጠው ወጥተዋል፡፡ግንኙነቱ በተካላካዩና በአጥቂዋ በመሆኑ ስራ ፈት ነበሩ(ልምምዱ አማካይና አጥቂውን የማገናኘት ሳይሆን የመነጣጠል እንደነበር ሜዳ ላይ ታይቷል)….ይሄን ግንኙነት ያበጀው ደግሞ አሰልጣኙ ነው፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለበት ይሄን ነገር ያዘዘውን እንጂ ስራውን የተገበረው(ልጆቹ)መሆን አይገባም፡፡ ይሄ አጨዋወት ብልጫ እንደሚያስወስድባቸው ልጆቹ ቢያውቁም የአሰልጣኝ ትዕዛዝ በመሆኑ ከመተግበር ውጭ ምንም አማራጭ የላቸውም፡፡አሰልጣኙ ከኋላ በረጅም ለአጥቂ ሲጥሉና የተጣለው ሲበላሽ እያየ ‹‹ተው››እንኳን ሲል አይታይም፡፡ያንን ነገር ሲደጋግሙት ይሄ ነገር እንደተስማማውና በዚህ ነገር የሚመጣውን ሽንፈት አምኖ የመቀበል ያህል ነበር የሚመስለው፡፡
አሁን ሁሉም ነገር ታይቷል ወደራሳችን ማየት ይገባናል፡፡ካለበለዚያ የተበላሸው ሰዓት ጉዞውን ይቀጥላል፡፡

እንደማጠቃለያ

አሰልጣኙ በማህበራዊ ድረገፅ ብዙ አሰልጣኞች ተጠቃሚ በመሆን ይወያያሉ ግን ማንነታቸውን ደብቀው ነው፡፡ ፊት ለፊት የሚወያየው ስዩም ነው፡፡ ይህን በማደረጉ ለልሎቹ እንደ ምሳሌ ነው፡፡ የሱ ትልቁ ችግር ስህተቱን አውቁ ወደ ለውጥ አለመሄዱ ነው፡፡ ለስዩም እንደምክር አይነት‹‹ይሄን አጨዋወት ተምረህ ሰርተህበት አይተሃል፡፡አንተንም እጀ ሰባራ አድርጎሃል፡፡ የሀገርም ውጤት ተበላሽቷል፡፡ የያዝከው ስልጠና ትክል ነው፡፡ግን ሰው ይፈልጋል፡፡አንተ የጋና አሰልጣኝ ብትሆን የያዝከው አጨዋወት ሊተገብሩልህ የሚችሉ ልጆች እዚያ ስላሉ ውጤት ታመጣበታለህ ፡፡፡ነገር ግን ያለሀው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የኛ ልጆች ያንተን ስልጠና ወስደው ከምዕራብና ሰሜን ጋር ሲገናኙ ልዩነቱን ስላየህ ከዚህ አጨወወት ውጣና ትምህርቱንም ላስተማሩህ ሰዎች መልሰህ የኛ ተጨዋች መነሻ ባደረገ መልኩ አሰልጥን፡፡ ያኔ በኔ ይሁንብህ ለውጥ ታመጣለህ ፡፡አንተም ተጠቅመህ ሀገርንም ታኮራለህ…ምርጫው ያንተ ነው …ካለበለዚያ…..››

Previous Story

የአባቶች ስንብት ከጋዜጠኛ (ተመሰገን ደሳለኝ)

Next Story

ከጎዳና ተዳዳሪነት ወጥቶ በልብስ ስፌት ሥራ ኑሮን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ ዓለማቀፍ ተሸላሚ ለመሆን የሕዝብ ድምጽ ይፈልጋል

Go toTop