አቤ ቶኪቻው
abeto2007@yahoo.com
በዛን ሰሞን በአንዱ ቀን አንዲት ሴት በጀሪካን ዘይት ይዛ ስትሄድ በመንገድ ላይ ታየች፡፡ የፀጥታ ሀይሎችም ተረባርበው በቁጥጥር ስር አዋሏት፡፡ ይህንን ዘይት ከየት አመጣችው…? እዛው መንገድ ላይ አነስተኛ ደረጃ ምርመራ ተደረገባት፡፡ በምርመራውም ከሱቅ እንደገዛች ታወቀ! ከየት ሱቅ…? ‹‹ምሪ›› ተብላ ወደ ባለሱቁ መምራት ግድ ሆነባት! ይህ ዛሬ የሆነ ነው፡፡ ነገ ደግሞ እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ህፃን ልጅ ‹‹ጮርናቄ›› (ብስኩት) እየበላ መንገድ ላይ ይታያል፡፡ ‹‹ጮርናቄው›› ዘይት በዝቶበታል፡፡ ‹‹ይህንን ጮርናቄ በዚህ ሁሉ ዘይት የጠበሰው እንዝላል ማነው…?›› ልጁ ከየት እንደገዛ ይመራል፡፡ የተመራበት ሰውም ጮርናቄውን ማን እንዳበሰለው ይመራል፡፡ አሁንም የተመራበት ይመረመራል፡፡
አንድ ወዳጄ ባደረሰኝ የ‹‹ዛሬ›› ገጠመኝ እና ሌላ ወዳጄ በነገረኝ የ‹‹ነገ›› ትንቢት ጨዋታችን ተጀመረ!
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ!? ሁሌም ‹‹አለሁልህ›› እንዲሉኝ ያድርጎትማ! ጤና፣ ኑሮ ወዘተ እንዴት ነው… ‹‹የወዘተን ነገር እንኳ ተወው!›› ካሉኝ ወዘተ ውስጥ ያሉት ስኳር፣ ዘይት እና ታክሲ ናቸው ማለት ነው፡፡
እኔ የምለው ‹መንግስት የነካው ነገር ሁሉ አይባረክ!› ብለው የረገሙ አንድ የሀይማኖት አባት አሉ እያለ ሰዉ የሚያወጋው እውነት ነው እንዴ…? ኧረ የሰይጣን ጆሮ አይስማ! ሲጀመርስ የኛ መንግስት ምን የሚያስረግም ስራ ሰርቶ ያውቅና ነው!? እርሱ ቅዱስ ሆኖ ሳለ እንደምን ይረገም ዘንድ ይሆናል!? (ድንቄም እቴ! ቅድስና ያላችሁ ልቦና ይስጣችሁ!)
ሚያዝያ ወር መጀመሪያው አካባቢ አንድ በእድሜም በስልጣንም የገዘፉ ሰው በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ነበር፡፡ (ይቅርታ እርሳቸውን የሚያኽል ሰው በቴሌቪዥን ‹መስኮት› ማለት ግዝፈታቸውን ማኮሰስ ስለሆነ በቴሌቪዥን ‹ሳሎን› ተከስተው ነበር፡፡ ብለን እናሻሽልና እንቀጥል!) እንዲህም አሉ! ‹‹ለፋሲካችሁ አታስቡ በርካታ ቁጥር ያለው ዘይት መንግስት እያስገባ በመሆኑ በየደጃፋችሁ እናደርሳችኋለንና ሃሳብ አይግባችሁ!›› አሉን፡፡ በርካቶች በሁዳዴው የፆሙት ዘይቱንም ቅቤውንም ስለነበረ፣ የባለስልጣኑ መግለጫ ፈንጠዝያን ፈጠረላቸው፡፡ ትንሽ እናጋን ካልን ደግሞ በዚህ የደስ ደስ ድግስ የደገሱ፣ ፅዋ ያጋጩም ነበሩ!
ፋሲካው መጣ ነገር ግን ዘይቱ አልመጣም፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹ሰውየው ዋሽተውን ይሆን?›› ሲሉ ጠረጠሩ፡፡ ሌሎችም ‹‹ሰውየው ሊዋሹ እንኳ ቢፈልጉ እድሜያቸው እሺ ብሎ አያስዋሻቸውም›› ሲሉ ተከላከሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ከተማዋ እና መላ ሀገሪቱ በዘይት ልትጥለቀለቅ ነው ተብሎ መግለጫ ተሰጥቶ፤ ነገርየው ግን የተገላቢጦሽ ሆነና ከፋሲካውም በኋላ ዘይት ብርቅ መሆን ብቻ ሳይሆን ዘይት ድርቅም ሆነና በገበያው ላይ ጠፋ! ኦሳማ ቢላደን የታሰሰበትን ያኽል አሰሳ ከደከሙ በኋላ ዘይትን ያገኙ ጥቂቶችም የመጣው ይምጣ ብለው ጨክነው አንድ ሌትር ዘይት በሰባ አምስት ብር ይገዙ ጀመረ፡፡ ሰባ አምስት ብር ለማውጣት የአቅም ማነስ የያዛቸው ደግሞ ለበርካታ ሰዓታት በመንግስት ሱቆች መሰለፍ ግድ ሆነባቸው፡፡ (የመንግሰት ሱቅ ተብሎ የተገለፀው ቀበሌ ነው) በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ አሽሟጣጮች ‹ሰላማዊ ሰልፍ ላማረው ዘይት ግዛ በለው!› የሚል ተረት መተረት የጀመሩት፡፡
አሁንም ቴሌቪዥናችን ከአባይ ዜና ሰዓት በተረፈች ሰዓቱ በርካታ ሌትር ዘይት ወደ ሀገሪቱ እየገባ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እሰይ! ምቀኛን ደስ አይበለው እና አሁን ‹‹ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንዬ›› እንደነገረን ከሆነ፤ (ምን ነካኝ እንደተጠራጣሪ ሰው ‹ከሆነ› እላለሁ እንዴ…! መሆኑማ አይቀርም) ብቻ እየመጣ ያለው ዘይት የዘይት ችግራችንን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን እንደ አባይ ካልገደብነው በስተቀረ የዘይት መጥለቅለቅ ሁሉ ሊያስከትል ይችላል!
አባይ… ካልኩ አይቀር… ትንሽ ስለ አባይ፤
እኔ የምለው እኒያ ‹‹የተከበሩ›› ሼክ የአባይን ግድብ ‹‹ከቨር አደርጋለሁ!›› የሚሉት መቼ ነው? ስንት ምስኪን የመንገድ ንጣፍ ድንጋይ (ኮብል ስቶን) ሰራተኛ ሁላ ጮክ ባለ ድምፅ ‹‹ድሮ አባይ ማደሪያ የለውም ግንድ ይዞ ይዞራል! ይባል ነበር፡፡ አሁን አባይ ማደሪያ አግኝቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባሉን መሰረት እኛ እናሳድረዋለን! የወር ደሞዜን እሰጣለሁ! ቦንድም እገዛለሁ! በጉልበቴም እገዛ አደርጋለሁ! ባጣ ባጣ ለአባይ ዘራፍ እላለሁ!›› እያሉ ሞራል እየሰጡ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ለበርካታ ችግሮቻችን ‹‹ከቨር አደርጋለሁ!›› እያሉ ቃል በመግባት ቃላቸውን ሲመግቡን የነበሩት ታላቁ ሰው ዛሬ ድምፃቸውን ማጥፋታቸው የግብፅ ጊዚያዊ መንግስት ምርጫ አድርጎ ዋና መንግስታቸው እስኪመሰረት እጠበቁ ነው? ወይስ በዲዛይን ግምገማው ውጤት ሱዳን እና ግብፅ በግድቡ እንደማይጎዱ እስኪረጋገጥ ነው? ወይስ ደህና አይደሉም ይሆን እንዴ? ውይ ከክፉ ይሰውራቸው ኧረ!
ለነገሩ አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ እርሳቸው ‹‹እኔ ከቨር አደርገዋለሁ!›› ካሉት ነገርየው ቆሞ መቅረቱ ነው፡፡›› እነዚህ አንዳንዶች ምሳሌ ጥቀሱ ሲባሉም ‹‹የቅዱስ ጊዮርጊስን ስታድየም ግንባታ ‹በኔ ይሁንባችሁ እኔ ከቨር አደርገዋለሁ!› ብለው ይኽው ስንተኛ አመቱ ቆሞ ቀርቷል፡፡›› ይላሉ፡፡ እንደነዚህ ግለሰቦች አስተያየት ከሆነ ድሮውንም ሰውዬው ‹‹ከቨር አደርጋለሁ!›› የሚሉት የሚዲያ ‹‹ከፈሬጅ›› (ሽፋን) ለማግኘት ነው እንጂ እንደማይሆንላቸው አጥተውት አይደለም አሉ! ብቻ ግን ሆነም ቀረ እኔ ግን በበኩሌ አነጋገራቸው ብቻ እንኳ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ቢያደርጉትም ባያደርጉትም ‹‹ከዚህ በኋላ ያለውን እኔ ከቨር አደርገዋለሁ!›› ሲሉ አነጋገራቸው ራሱ ደስ ይለኛል፡፡ አሁንም የአባይን ጉዳይ ብቅ ብለው ‹‹ከዚህ በኋላ ያለውን ለኔ ተዉት እኔ ከቨር አደርገዋለሁ!›› ቢሉልን ደስ ይለኛል፡፡
ይህንን ጉዳይ ያወጋሁት አንድ ወዳጄ ምን እንዳለኝ ያውቃሉ? ‹‹እውነትህን ነው እርሳቸው ብቅ ብለው ‹ከዚህ በኋላ እኔ ከቨር አድርጋለሁ!› ቢሉ ጋዜጠኛውም ከተደጋጋሚ ዘገባ ቴሌቪዥናችንም በአባይ ዜና ከመጥለቅለቅ ትድን ነበር!›› ሲል ተናገረ፡፡ (ይቅር ይበለው ወይስ ይቅር አይበለው?)
እነዛ አርቲስቶቻችን ራሱ እንደ አምልኳዊ ስርአት እዛው አባይ ድርስ ሄደን ቃል ካልገባን ሞተን እንገኛለን ብለው ያን ሁሉ ወጪ ካስወጡ በኋላ ምነው ድምፀቸው ጠፋሳ! ወይስ ቃል የገቡት ከዛ በኋላ ምንም ትንፍሽ ላይሉ ነው!?
ወዳጄ… ስለ አባይ ጉዳይ ገና ወደፊት ብዙ የምናወጋው ይኖረናል! አሁን ግን ቀጥታ ከአባይ ወደ ስኳርና ዘይት እንሳፈራለን! መሳፈር ስንል ግን በቅድሚያ ታክሲን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ እርሱ ይቅደማ!
ከዕለታት በአንዱ ሰኞ በርካታ የታክሲ ሾፌሮች የስራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፡፡ አንዳንዶች ‹‹አድማውን ስፖንሰር ያደረገው መንግስት ነው!›› ሲሉ ተደምጧል፡፡ መንግስት በበኩሉ በሆዱ የዚህ አድማ የክብር ስፖንሰሮች ‹‹የሻቢያ ነጭ ለባሽ ሀይሎች ናቸው!›› ሳይል አይቀርም፡፡ እኔም የመንግስት ልጅ እንደመሆኔ መጠን ይህንን ጠርጥሬያለሁ፡፡ በአድማው ዕለት በርካቶች ከሰራ እና ከትምህርት ገበታቸው የመቅረታቸውን ያኽል፤ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች በርካቶች በስራ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ እነዚህኞቹ በየቀበሌው ቀበሌ ቀበሌ የሚጫወቱ ወጣቶች እና ሴቶች ሲሆኑ በየመንደሩ የቆሙትን ታክሲዎች ታርጋ እየመዘገቡ እና ‹‹ወዮልህ!›› እያሉ ‹‹ያስቦኩበት›› ጣታቸውን ‹‹ስትራፖ›› ይዟቸው ውለዋል አሉ! የታክሲ ሾፌሮች አድማ ባደረጉበት እለት የተወሰኑ ታክሲዎች ደግሞ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደ ‹ንብ› ሲሰሩ እንደዋሉም ታይቷል፡፡ እደግመዋለሁ ‹እንደ ንብ!› በነገራችን ላይ ከዚህ ከታክሲ ጋር ተያይዞ ከተባሉ ነገሮች በሙሉ ሳልወድ በግዴ ያሳቀችኝ በአንድ ጋዜጣ ላይ የወጣች አንድ ፅሁፍ ናት፡፡ ምን ትላለች መሰልዎ ‹‹የታክሲ ስምሪቱ ነገር ከቂጥ ቆርጦ ፊት ላይ የመለጠፍ አይነት ነው!›› ሰዉ እንዴት ተናጋሪ ሆኗል ጎበዝ! የሆነ ሆነ አሁን የታክሲ ስምሪቱ አለም የለምም በማይባል ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ከኛም የበላለጡ የመንግስታችን አድናቂዎች፣ ‹‹የታክሲ ስምሪቱ ለእያንዳንዱ ነዋሪ ሰርቪስ የመመደብ ያኽል ነው!›› ሲሉ ቢያሞካሹትም፤ ሌሎች ጨለምተኞች ደግሞ ዘይት ስኳር እና ሌሎችን ያጠፋ የመንግስት እጅ ታክሲዎችንም እንዳያጠፋ እንሰጋለን እሉ ይገኛሉ፡፡
ኧረ ወዳጄ የስኳርን ነገር ሰምተዋል? በዛ ሰሞን አንድ ወዳጄ በአንድ ሻይ መጠጫ ቤት ውስጥ ሻይ አዝዞ መጣለት፡፡ ስኳር ሲጨምር የሻይ ቤቱ ባለቤት በርቀት እየተከታተሉት ነበር፡፡ አንድ ማንኪያ አደረገ፣ ዝም አሉት፣ ሁለተኛ ጨመረ፣ አናታቸውን እያሻሹ ፀጥ አሉት ሶስተኛ ማንኪያ ሲሰነዝር ተደብቀው ሲከታተሉበት ከነበረው ጥግ ወደ ወዳጃችን ተንደርድረው እየመጡ ‹‹ሶስተኛ ማንኪያ ልትጨምር? ምነው የኔ ልጅ ጡር አትፈራም ግፍ አይሆንብኽም በዚህ ጊዜ ለአንድ ብርጭቆ ሻይ ሶስት ማንኪያ? ስለመዳኒያለም በቃ! ስለ መዳኒያለም በቃ!›› ብለው ቢማጠኑት ጊዜ ወዳጃችን ሊጨምር ያሰበውን ሶስተኛ ማንኪያ ስኳር እየመለሰ ‹‹ስኳር የወደድኩት እኔ ምስኪኑን ሳይሆን ያስወደዱትን ስለመዳኒያለም ‹‹በቃ!›› ቢሏቸው አግዞት ነበር!›› ሲል አስተያየት ሰጥቶ ለርሳቸው ሲል ያለወትሮው በሁለት ማንኪያ ስኳር ሻይ ጠጣ፡፡ ይህ ወዳጄ አለቅጥ ሲያጋንን ምን አንዳለን ያውቃሉ ክፉ ቀን ሲወጣ አንዷን ማንኪያ አሟላለሁ!
የምር ግን ወዳጄ ስኳር እንኳ አሁን ትንሽ ይሻላል መሰለ፡፡ የዘይት ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ በሀገራችን ኑግ የሚመረተው የኑግ ዘይት እስከ አንድ መቶ አስር ብር ድረስ እተሸጠ መሆኑን ሲሰሙ ‹‹ኑግ… ኑግ… ኑግ ይሄ የምናውቀው ነው ወይስ ሌላ?›› በሚል ግር ያስብላል፡፡ ቴሌቪዢኑም፤ ባለስልጣናቱም ዘየት በሽ ነው እያሉ ‹‹ሞልቷል በሀገሩ ሞልቷል…›› የሚለውን የጋሽ ጥላሁን ዘፈን ቢጋብዙንም እውነታው ደግሞ ‹‹እኔስ ውሸቴን ነው…›› የሚለውን የሚኒሊክ ወስናቸውን ዘፈን የሚየስታውስ ነው!
በመጨረሻም
አማን ያሰንብተን!
የዘይት ነገር… ወይስ
Latest from Same Tags
የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ108 ሚሊዮን በላይ ደረሠ
(ዘ-ሐበሻ) በአለም ባንክና መሠል አለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ሳምንት ይፋ የሆነው መረጃ የኢትዮጵያን ህዝብ ብዛት ከ108 ሚሊዮን በላይ አድርሶታል። በዚህ መሠረት ኦክቶበር 22 ቀን
ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ የለም!
February 25, 2018 ጠገናው ጎሹ ሰሞኑን በአገራችን የሆነውና እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ እውነታ ሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቅንበት እጅግ ፈታኝ ( ወፌ ቆመች ሲባል መላልሶ የመውደቅ
ሲግኒቸር ተዘጋ
(ዘ-ሐበሻ) ሲግኒቸር ለብዙ ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ነው፡፡ እንኳን ለኢትዮጰያዊያን በሙሉ ለአዲስ አበቤውም ቢሆን ባዕድ ነው፡፡ ኧረ ለአራት ኪሎው መንግስትም ባዳ ነው፡፡ ሲግኒቸር የታደሉ ባለስልጣናትና ልጆቻቸው እንዲሁም
![](https://amharic.thehabesha.com/wp-content/uploads/2013/07/bulcha_demeksa.jpg)
በኦነግ ምክንያት የታሰሩ የኦሮሞ ወጣቶችም ይፈቱ | ቡልቻ ደመቅሳ
ኦነግ “ኦሮሞ ነፃ መውጣት አለበት” ብሎ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ሲታገል፣ የረገፉና የታሰሩ ወጣቶች ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም እስከ አሁን በእስር ቤት የሚማቅቁ ቁጥራቸው አያሌ ነው፡፡
![](https://amharic.thehabesha.com/wp-content/uploads/2018/01/84403.jpg)
የሻምቡ ጀግና የኦሮሞ ልጆች ፋሽስት ወያኔን በቃሪያ ጥፊ አጩለውታል!
ከአቻምየለህ ታምሩ ወያኔ የኦሮሞና የአማራን ግንኙነት «መርህ አልባው ግንኙነት» በማለት ያወገዘበት የስራ አስፈጻሚ ኮምቴ መግለጫ ቀለም ሳይደርቅ የሻንቡ ልጆች «አንድ ነን! መቼም አንለያይም! «የኦሮሞ